"ሠራዊታችን ወታደራዊ ቁመናውን አጠናክሮ ተልዕኮውን በሚገባ ይወጣል የሚል ዕምነት አለኝ"

 

የ2011 ዓ.ም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀንን አስመልክቶ ጋዜጣችን በሚያሳትመው ልዩ ዕትም ከመከላከያ ሚኒስትር ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ጋር ቆይታ አድርገናል። በቆይታችንም በተቋሙ እየተካሄደ የሪፎርም ሥራና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ውጋገን፡–የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር እያካሄደ ያለው የሪፎርም ሥራ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ኢንጂነር አይሻ፡– በመጀመሪያ ለኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን እንኳን አደረሰን። እንደሚታወቀው መንግሥት እየወሰዳቸው  ካሉት የለውጥ እርምጃዎች አንዱ አጠቃላይ የፀጥታ አካላት ላይ ሪፎርም ማድረግ ነው።

መከላከያ ደግሞ ይህንን የሪፎርም ሥራ እየሰሩ ካሉት ትላልቅ የፀጥታ አካላት ትልቁና ዋነኛው ነው። ይህ የሪፎርም ሥራ በተቋሙ ውስጥ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራ ነው። ከዚህ በመነሳት ተቋሙ እየሰራ ያለው የለውጡን አስፈላጊነትና ለውጡ ለምን እንዳስፈለገ፣ ከዚህ በፊት የነበሩት ጉዳዮች ምን እንደሆኑ የዳሰሰ ጥናት አድርጎ፣ ጥናቶቹን መሠረት በማድረግ ተቋሙ በነበሩት ችግሮች ላይ ከተስማማ በኋላ፣ እነዚህን ችግሮች እንዴት ማረምና ወደ ሪፎርም መግባት እንደሚቻል መግባባት ላይ ተደረሰ። በዚህም እራሱን የቻለ የሪፎርም ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ የተገባበት ሁኔታ ነው ያለው።

ስለዚህ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ራሱን የቻለ የሪፎርም ዕቅድ ተዘጋጅቶለታል። ዕቅዱ ደግሞ ከላይ እስከታች ምን መምሰልና ዕቅዱ እንዴት መመራት እንዳለበት፣ ምን ዓይነት ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚፈለግ፣ መቼ ምን እንደሚሰራ የሪፎርም ዕቅድ ለመምራት የሚያስችል ነው። ለውጡን በአግባቡ ለማስቀጠል ሪፎርሙ ተቋማዊ መምሰል ስላለበት እያንዳንዱ በተቋሙ ሥር ያለ የሥራ ክፍል ወይም አደረጃጀት እራሱን የቻለ ዕቅድ ከተቀመጡት ግቦች ተነስቶ እንዲሰራ ነው የተደረገው። በመጀመሪያ የተደረገውም እንዴትና በምን አግባብ ነው መሠራት ያለበት የሚለው መግባባት ከተደረሰ በኋላ የራሱ ዕቅድ ተዘጋጀለት። ዕቅዱ 11 ግቦች ያለው ዕቅድ ነው የተዘጋጀው።

እነዚህ 11ዱ ግቦች ሲመነዘሩ እያንዳንዱ የሥራ ክፍል አስፈላጊ ዝርዝር እቅድ እንዲያዘጋጅ ነው የተደረገው። ይኼም በከፍተኛ አመራሩ በኮሜቴ እየተመራ፣ በየጊዜው እየተገመገመ የትእንደደረሰ እየታየ አስፈላጊው የሆኑ ግብዓቶች እየቀረቡለት እንዲሰሩና አጠቃላይ ሪፎርሙ ተቋማዊ እንዲሆን፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት ሊመራባቸው የሚገቡ አሰራሮችና የአሰራር ሥርዓቶች እንዲኖሩት ስለሚያስፈልግ ሁሉም የሥራ ክፍል የሚያስፈለገውን ግብዓትና የአሰራር ሥርዓት በሚያጎለብት መንገድ እየተሰራ ነው ያለው። ዕቅዱ ያተኮረባቸው 11 የሪፎርሙ ግቦች አሉ። እነዚህም በመጀመሪያ የተቋሙን የለውጥ አደረጃጀት ማጠናቀቅ ነበር። አደረጃጀቱ ተጠናቆ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ምደባ  እየተደረገ ነው። ምደባው ደግሞ ብቃትን፣ ብሄራዊና የሴቶች ተዋፅኦን ያረጋገጠ የአመራርና የሠራዊት ምደባ ነው እየተደረገ ያለው እሱን እስከ ታች ለማውረድ እየተሰራ ነው ያለው።

ከዚህ በፊት 6 ዕዞች የነበሩት አሁን ወደ 4 ዝቅ ብሏል። አደረጃጀትም ተፈጥሮ ያልነበረ የሠራዊት እርከን እንዲጨምር ተደርጓል። እነዚህን የመሳሳሉ እየተሰሩ ነው ያሉት።

ሁለተኛው ከሠራዊት ቅጥር ጨምሮ እስከ ጡረታ ድረስ ዘመናዊ የሰው ኃይል ተቋሙ ሊኖረው ይገባል የሚል ነው። ይህም እንደ ትልቅ ግብ ተቀምጧል። ሥራውም በሰው ኃይል ሀብት ዋና መምሪያ እየተመራ ሁሉም የሥራ ክፍሎች ይህን እንዲተገብሩና የአሰራር ሥርዓቱ ወጥነት ያለው እንዲሆን  እየተሰራ ነው።

ሦስተኛው ፕሮፌሽናል ሠራዊት ለመገንባት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ወታደራዊ ንድፈ ሀሳቦችንና መመሪያዎችን የማዘጋጀት ሥራ መቀጠል አለበት ተብሎ እየተሰራ ነው። ይኼን ለማድረግ ቅድሚያ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ መከለስ ነበረበት።  በዚህም አዋጁ ተከልሶ በርከት ያሉ አዳዲስ የአዋጅ አንቀፆች ተካተውበት በአመራሩ ውይይት ከተደረገበት ብኋላ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ፀድቆ በኋላም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ፀድቋል። ከዚህ በመነሳት ድግሞ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ሥርዓቶች እንዲዘጋጁ እየተደረገ ነው። ደንቡም ወደ መጠናቀቁ ደርሷል። ሥርዓቱን ጠብቆ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል።

አራተኛው ሠራዊታችን ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ የሚወጣ ነው። ይህን ተልዕኮውን ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ መፈፀም የሚያስችለውን የሥልጠና ሥርዓት ለመዘርጋት ሀሳብ አለው። ይህም አንድ የትኩረት አጀንዳ ተደርጎ እንደ ትልቅ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው ያለው። ስለዚህ በዓለምና በአካባቢያችን ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ዝግጁነቱን ያረጋገጠ ሠራዊት መገንባት የሚያስችልና አሁን ካለው  በተሻለ ተፈትሾ ዘመናዊ የሥልጠና ሥርኣት ለመዘርጋት ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ ነው።

አምስተኛው ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የፋይናንስ፣ የግዢ፣ አሰባሰብ፣ የንብረት አስተዳደር የአወጋገድ የአሰራር  ሥርዓቶች ያስፈልጋሉ። እንደ ሀገር መመሪያዎች ደንቦችና አዋጆች አሉ። ከእነሱ የተከለሱ የመከላከያን ሥራ ሊመለከት በሚችል መልኩ ከስተማይዝ ተደርገው ተቋማዊ  የሆነ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ውስጣዊ መመሪያዎች እየተዘጋጁ ነው። ሥራቸው የተጠናቀቁትም አሉ።  እነዚህን መመሪያዎች ተጠቅመን ወጥነት ያለው የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት አጥፊዎችንም መጠየቅ የሚያስችል ነው። ይህም ራሱን የቻለ ኮሚቴ ተዋቅሮለት በደንብ በፋይናንስ ዘርፍ እየተመራ ያለ አንድ ትልቅ ግብ ነው። በርከት ያሉ አሰራሮች እየተፈጠሩ ነው። ወደ ሥራ ለማስገባትም ጊዜ የሚፈልግ ስለሚሆን ለሱ የሚመጥን አደረጃጀት እንዲኖር ይደረጋል።

ስድስተኛው ዘመናዊ የዕዝ ቁጥጥርና ወታደራዊ ትጥቅ፣ እንዲሁም በመረጃ የበላይነት መፍጠር ላይ ያተኮረ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ይፈልጋል። ስለዚህ በቴክኖሎጂ የተገነባ የመረጃ ሥርዓት የትጥቅ ዝግጁነትና ሌሎች የዕዝ የቁጥጥር ሥርዓቶች እንዲኖሩ ማድረግ እንደ ትልቅ ግብ ተወስዶ እየተሰራ ነው። ለዚህም ራሱን የቻለ፣ የራሱ ዕቅድ ያለው በከፍተኛ አመራር የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮለታል።

ሰባተኛው ወሳኝ የሆኑ ተግባሮቻችን በሚዲያና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የማሳደግ፣ የመጠቀም፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ ይላል። ስለዚህ ይህን ለማድረግ ራሱን የቻለ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተገነባ ካለው የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ ጋር ተያያዥ የሆነ አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ግብዓት ያለው የመረጃ ቋት ይለው ወደታች ወርዶ የሚገኝ የመረጃ ማዕከል እንዲኖር፣ እንዲሁም በመረጃና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ውጤታማና ቀልጣፋ አሰራሮች እንዲኖሩ የሚደረግ ነው። ዕቅዱም አልቆ ወደ ትግበራ ተገብቷል።

ስምንተኛው የሠራዊቱን ኑሮ ለማሻሻል ደስተኛና ሞራሉ የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል፣ እንዲሁም ሥነ_ ልቦናዊ ዝግጁነቱ የተጠበቀ  እንዲሆን ከመከላከያ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን የተጀመሩትን ቶሎ በማጠናቀቅና አስፈላጊ የሆኑትን በመስራት የራሱ ዕቅድ ውጥቶለት በየጊዜው እየተገመገመገመ እንዲሄድ የማድረግ ዕቅድም እንዲሁ ተይዟል።

ዘጠነኛ ከሠራዊቱ የሚሰናበቱ የሠ ራዊት አባላት ቀጣይ ህይወታቸው ምን መሆን እንዳለበትም ከወዲሁ በመገንዘብ የሪልስቴትመንት ፕሮግራሞች ያስፈልጋሉ። እሱንም በተሻለ መንገድ ለመሥራት በአደረጃጀት ደግፎ ባለቤት ኖሮት እንዲሰራ ለማድረግ ሲባል እራሱን የቻለ አደረጃጀት ተሰርቶለታል። ኃላፊም ተመድቦለታል። ሠራዊቱ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ሲለፋ ቆይቶ በሚሰናብትበት ወቅት ኑሮው ምን መሆን እንዳለበት በተጠና አግባብ ለመመለስ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ሊኖረን ይገባል። ይህም ከቅጥር እስከ ስንብት ያለውን ሂደት ሊሰራ የሚችል አደረጃጀት ንው። ቀጣይነት ያለውና  ባለቤት ያለው ነው።

ስለዚህ ሠራዊታችንን የሚቀላቀሉ አዳዲስ አባላት በፍላጎታቸው እርግጠኞች ሆነው ከአገልግሎት በኋላ የሚደግፋቸው አሰራር እንዳለ እንዲያውቁ እንዲሁም ተወዳጅ ተቋም እንዲሆን ስለሚያግዘን፣ ለሠራዊቱም ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆናል።

አሥረኛው የሠራዊታችንን ሞቢሊቲ የሚጨምሩ መሰረት ልማቶች ያስፈልጋሉ በሚል መንሻ አንድ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው። ሞቢሊቲው ፈጣንና በተፈለገበት ቦታ በወቅቱ መድረስ እንዲችል ተልዕኮውንም በሚወጣበት ጊዜም ደረጃውን የጠበቀ አስፈላጊ መሰርተ ልማቶች እንዲገነቡለት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ካንፖች እንዲኖሩት፣ የነባሮቹንም ደረጃቸው እንዲሻሻል ማድረግ ነው።

ይህን ለማሻሻል ተቋሙ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገዋል። ከየት ተጀምሮ ወዴት እንደሚኬድ የሚያሳይ የማሸጋገሪያ  የተጀመረውን ሪፎርም ወደ ትራስፎርሜሽን ለማሸጋገር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው ያለው። ይህን የሚሰራ ኮሚቴ አለ። በጥናት ላይ የተመሰረተ መቼ ምን እንደሚሰራና ተቋማዊ የሆነ መንገዳችንን የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ ይዘጋጃል።  በዚህ መልኩ ሪፎርሙን ተቋማዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ከታችኛው እስከ ከፍተኛው ያሉ የሠራዊት አባላትና አመራር መግባባት እየተደረሰበት የግንባታው አንድ አካል የውይይት አንዱ አካል እንዲሆን ይፈለጋል።

ስለዚህ ተቋማዊና ኢንስቲቲዩሽናል እያደረግነው ባለቤትነት ተሰምቷቸው ሠራዊቱም ምን እየተደረገለት እንደሆነ እያወቀ እንዲሄድ፣ የኢትዮጵያ ህዝብም ተቋሙ ምን እያደረገ እንዳለ እንዲያውቅ በሚዲያ የተደገፈ፣ ለህዝብ ግልጽ እየተደረጉ እንዲመሩ ይፈለጋል። በዚህ አግባብ ለመሥራትም አስፈላጊ የሚባሉ አደረጃጅቶች ተቀምጠዋል።

ውጋገን፡– ለውጡን ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚፈለገው ግብ ላይ ለማድረስ የተቋሙ ቁርጠኝነት እስከምን ድረስ ነው?

ኢንጂነር አይሻ፡– በነበረኝ አጭር ቆይታ ከየትኛውም ተቋም በቁርጠኝነት የሚገለጽ የሰው ሀብት እንዳለበት ነው ያገኘሁት። ስለዚህ ያስቀመጥናቸውን ግቦች በቁርጠኝነት ለመፈጸም በየደረጃው ያለው አመራር እያሳየ ያለው ዝግጁነት በጣም የሚደነቅ ነው። በአጭር ጊዜ ሰው ኢኒስቲቲዩሽናላይዝድ የሚሆን ይመስለኛል። ወደ ሲስተም የሚቀየር ነው የሚመስለኝ። ቁርጠኝነቱ ከነበረው ዝግጁነት ቶሎ የተወሰኑትን ሥራዎች ወደ ተግባር ለመቀየር ያለው ጅምር በጣም ጥሩ ነው።

ውጋገን፡– ተቋሙ እያካሄደ ባለው ሪፎርም 11 ግቦች እንዳሉ ተገልጿል። ግቦቹ ተቋሙን ጠንካራና ዘመናዊ ከማድረግ አኳያ ያላቸውን ፋይዳ ቢገልጹልን?

ኢንጂነር አይሻ፡– በዓለም ደረጃ ያሉ የመከላከያ ኃይሎች ወይም በሀገር ደረጃ ያለው የመከላከያ ኃይል ፍላጎት ከባባዊና ዓለማቀፋዊ ሁኔታውን ያገናዘበ በቴክኖሎጂ የታገዘ ኃይል ለማድረግ ይህ ሪፎርም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ይህን አስፈላጊነት ከላይ በገለጽኳቸው ዕቅድ በአግባቡ ተቋማዊ እያደረግን በሚመራበት ጊዜ የምንፈልገው የመከላከያ ሠራዊት ቁመና ይኖርናል ተብሎ እየተሰራ ያለ ስለሆነ ሪፎርሙ ለውጡን በአግባቡ ለመምራት ይሚያስችል ደረጃ የተቀመጠ ነው።

  ይህ ሲሆን በቴክኖሎጂ የዘመነ ጠንካራና ህዝባዊ አመኔታ ያለው ፕሮፌሽናል ሠራዊት ለመገንባት ያስችላል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም በሪፎርሙ ሠራዊቱና አመራሩ ተሳታፊ ይሆናሉ። ህዝብ እንደ ህዝብም እየተረዳው ይሄዳል። ስለዚህ በማናቸውም ሁኔታና ጊዜ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ግዳጁን ሊወጣ የሚችል የህዝብ አመኔታ ያለው፣ ፕሮፌሽናል የሆነ ሠራዊት መገንባት ይቻላል የሚል አቋም ተይዞ እየተሰራ ያለ ሥራ ስለሆነ እውነትም በተባለው አስተሳሰብ ባስቀመጥነው መንገድ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ዝግጁነቱም የሚኖረው አሰላለፍም የሞራል ብቃቱም በዛ ልክ ያድጋል ብዬ አስባለሁ።

ውጋገን፡– የመከላከያ የልማት ተቋማት ሀገራዊ የልማት እድገትን በማገዝ በኩል ምን አበርክተዋል?

ኢንጂነር አይሻ፡–በመከላከያ እጅግ ግዙፍ የሆነ የልማት ተቋማት አሉ። ተቋማቱ በርከት ያሉ ሥራዎችን ነው የሚሰሩት። የሚሰሯቸው ሥራዎች ለህዝብ ተደራሽ አይደሉም። ስለዚህ መታወቅ ያለባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። እጅግ በጣም ውስብስብ የሆነ የመሬት አቀማመጥ አካባቢዎች ላይ የሚስሩ ትላልቅ መንገዶች እየተስሩ ያሉት በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ነው። ዲዛይን የሚደረጉትም በመከላከያ ዲዛይን ድርጅት ነው። በርከት ያሉ ግብዓቶችም በመከላከያ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ይቀርባሉ።

ስለዚህ ሀገሪቱ እየሰራቻቸው ባሉት የመሰረተ ልማት ግንባታ ትልቁን ትልዕኮ እየተወጣ ያለ ተቋም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ የሚባሉ በኮንክሪት የሚስሩ መንገዶችን እየሰራ ያለው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ  ነው።

ሌሎች የተለያዩ የህንፃ ግንባታዎችንም ይገነባል፣ ለሠራዊቱ ግልጋሎት የሚሰጡ ካንፖችን፣ የገበያ ክፍተት ባለባቸው ሁሉ እየተገኘ በአግባቡ ሥራውን እየሰራ ያለ ተቋም ነው። እሱን አቅም አሟጦ የመጠቀም ጉዳይ ነው ከእኛ የሚጠበቀው። በአግባቡ ተመርቶ ፕሮጀክቶች በጥራት ተሰርተው፣ በተቀመጠላቸው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቁ መከላከያ እየሄደበት ያለው መንገድ እጅግ ብ አጣም ጥሩ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የኮንስትራክሽን ካንፓኒዎች በተሻለ ቁመና ላይ ያለ፣ የተሰጠውንም ፕሮጀክት በጊዜ የሚፈጽም ለዛው በጣም ከባድ በሆነ የመሬት አቀማመጥና የአየር ፀባይ፣ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚሰራው ነገር መታወቅ ያለበትና ሊቀጥል የሚገባ ነው። ስለዚህ ለሀገሪቱ ልማትና ዕድገት በእጅጉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ ያለ ተቋም  ነው _ የመከላከያ ክንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ። ሌሎችም ዘርፎች አሉ። እዚህ ሀገር በሌላ ተቋማት የማይመረቱ በመከላከያ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ በርከት ያሉ የጦር መሣሪያዎች ሌሎችም ምርቶች አሉ። ይህን እርሾ አስፍቶ ከሀገር ገበያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ፣ ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች ገበያ ሊውሉ የሚችሉ በቂ አቅም ያላቸው ቁርጠኛ አቋምና የሰው ሀብት ያላቸው ተቋማት ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ተቋማት በአግባቡ መጠቀም ይጠይቃል። ትልቅ አቅም እንዳለ ነው የሚያሳየው። አቅሙንም መንግሥት በአግባቡ እየተጠቀመ እንደሆነ ነው የተገነዘብኩት።

ሌላው ህዝቡንም ከመደገፍ አንፃር ስንመለከት ሠራዊታችን በሚገኝባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ባለው ጊዜ የአርሶ አደሮቻችንን ምርት በመሰብሰብ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ህዝባዊ በሆነ ተግባሮች ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው። ይህ ተግባሩ ህዝባዊነቱን የሚያሳይ ነው።

ውጋገን፡–7ኛውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀንን አስመልክተው መልዕክት ቢያስተላልፉ?

ኢንጂነር አይሻ፡– 7ኛው የኢፌዴሪ  መከላከያ ሠራዊት ቀን የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ሲከበር ´ህገ_ መንግሥታዊ ታማኝነትንና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለንª በሚል መሪ ቃል ነው። መሪ ቃሉ እጅግ በጣም ትልቅ መልዕክት አለው። ስለዚህ ከዚህ ስንነሳ በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ያለው ውስጣዊ የሠላም ሁኔታን  የማስጠበቅ ወደነበረበት ቁመና የመመለስ ሥራ በእጅጉ በሠራዊታችን የሚፈጸም ነው። ስለዚህ ሠራዊታችን እንደወትሮው ህዝባዊ አመኔታን ባገናዝበ መልኩ በየአካባቢው ብቅ ጥልቅ የሚሉ የሠላም መደፍረስ ሁኔታዎችን ሠራዊታችን በቁርጠኝነት እስካሁን እያደረገ ባለው አግባብ ቀጥሎበት ኢትዮጵያ ወደነበረችበት ሠላም የምትመለስበት ጊዜ እንደሚሆን ምኞቴ ነው።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተጀመረው የሠላም ሁኔታ ህዝባችን ሲጠብቃቸው የነበሩ የሠላም ጉዳዮች የተጀመሩት ጠንካራ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በዛው አግባብ ሠራዊታችን ደግፎ የሚጠበቅበትን ግዴታ እንዲወጣ ነው የማሳስበው። በተለይ ውስጣዊ ሠላማችንን ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረት እጅግ በጣም ፈታኝ ቢሆንም ሠራዊታችን ህዝባዊ ቁመናውን አጠናክሮ በመቀጠል ተልዕኮውን በሚገባ ይወጣል የሚል እምነት አልኝ። እንደሚወጣም እርግጠኛ ነኝ።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!