ከሀገራችን ሴት ዳኞች

ዋና ዳኛ ስምረት ባንቱ፤

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የእግርኳስ ስፖርታዊ መድረኮች ላይ አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዳኝነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ዳኞች በሚሰጡት የሜዳ ላይ ውሳኔዎች ውዝግቦች አይጠፉም፣ ከእግርኳስ ጨዋታ ወዳዱ ማህበረሰብ በሚሰነዘርባቸው ትችቶች፣ ከአሰልጣኞችና ተጨዋቾች በሚነሱባቸው ተቃውሞዎች፣ ሜዳ ላይ በምትንከባለለዋ ኳስ በሚገጥማቸው ንክኪና አስቂኝ እንቅስቃሴዎቻቸው ብዙዎችን የሚያስደምሙ ትዕይንቶች ናቸው፡፡አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ትዕይንት ጎራ ተሰላፊ ሆነው የሚስተዋሉት ደግሞ ወንዶች ዳኞች ናቸው፡፡ ሴት ዳኞች በቁጥር አናሳ በመሆናቸው ለዚህ ድርጊት ተጋላጭ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሴት ዳኞች እጥረት በዓለም ላይ የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ይሁን እንጂ ወደሀገራችን ስንመጣ የፆታ ስብጥር ክፍተቱ ጎልቶ ይታያል፡፡ከጥቂት አመታት ወዲህ ለውጦች እየታዩ ቢሆንም በዳኝነቱ ውስጥ በስፋት የተሰማሩት ወንዶች ናቸው፡፡ምንም እንኳን የስፖርት ዳኝነት በቴክኖሎጂ መታገዝ ቢጀምርም ለስፖርቱ ውበትና ድምቀት ግን የዳኞች ሚና ቀላል እንዳልሆነ ይነገራል ፡፡

እንዲህ ስለእግርኳስ ስፖርት ዳኝነት ማንሳታችን በሀገራችን ሴት ዳኞች የት ናቸው?የሚለውን ማንሳት ፈልገን ነው፡፡በዚሁ ዙሪያም ከዳኛ ስምረት ባንቱ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ዳኛ ስምረት ባንቱ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ጉርድ ሾላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፌዴራል ዳኛ፤ ዋና ዳኛ ናት፡፡ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በዳኝነት ስራ ላይ ተሰማርታ በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ በሀገራችን የስፖርቱ ዘርፍ የራሳቸውን አሻራ ጥለው ለማለፍ ከሚፈልጉ ባለ ተስፋዎች አንዷ ሆና ትጠቀሳለች፡፡

ከዳኝነት በፊት

በልጅነት ሯጭ መሆን ነበር ፍላጎትዋ፡፡የፈለገችውን ባታሳካም ከስፖርቱ አልራቀችም፡፡በድንገት ወደ ዳኝነቱ ሙያ መጣሁ የምትለዋ ስምረት፤ ለዳኝነቱ መሠረት የሆናትን እንዲህ አጫውታኛለች፡፡የሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ስፖርት ትጫወት ነበር፡፡በወቅቱ በእግር ኳስም ሆነ በሌሎች የስፖርት አይነቶች የሚሳተፉ ሴቶች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነበር፡፡ማህበረሰቡም ሆነ ቤተሰብ አያበረታታም፡፡እርሷም ተፅዕኖውን ተቋቁማ እንጂ ከቤተሰቧ ፍቃድ አላገኘችም፡፡ልክ እንደ እርሷ ቤተሰባዊ ተጽእኖ ስር ከነበሩ ሴቶች ጋር በድብቅ እየሄደች ትሰለጥንና ትጫወት እንደነበር በማስታወስ በጥረቷ ዳኝነት ደረጃ ላይ መድረሷን ትገልፃለች፡፡

የዳኝነት ሙያ አጀማመር

በአንድ ወቅት በእራሷ የግል ጉዳይ ወደምትኖርበት የቀበሌ አስተዳደር ትሄዳለች፡፡በቀበሌው የማስታወቂያ መለጠፊያ ሰሌዳ ላይ ለዳኞች ስልጠና መዘጋጀቱን የሚገልፅ ጽሁፍ ታነባለች፡፡ከተመዝጋቢዎች አንዷ ሆና ስልጠናውን ወሰደች፡፡ስልጠናው ለዳኝነት ያበቃኛል ብላ አልነበረም፡፡ግን አጋጣሚው የሙያው ባለቤት አደረጋት፡፡

ዳኝነት ከሴትነት ጋር

ወደ ዳኝነት ሙያ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ ከትንንሽ ጨዋታዎች እስከላይኛው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ረዳትና ዋና ዳኛ በመሆን መርታለች፡፡ሙያ መዳኘት ቢሆንም፡፡እንደሚያዝናናትና እንደሚያስደስታት ትናገራለች፡፡ሁልጊዜም ቢሆን ነጻነት ተስምቷት ትሰራለች፡፡ሴት በመሆኗ የተለየ ነገር አልገጠማትም፡፡ በዳኞች ላይ የሚሰነዘሩ ጉርምርምታዎች ሳይበግሯት ሙያዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች፡፡

ስምረት በሜዳ ላይ ለሚገጥማት ስድብና ዛቻ ቦታ አትሰጥም፤ ይልቁንም ትችቶች ሲበዙ ያጠነክራል ትላለች፡፡ዳኛ ከመሆኗ በፊት በዳኞች የሚሰጡ የሜዳ ላይ ውሳኔዎች ወገንተኝነት ይታይበት ነበር ብላ ታምናለች፡፡ እርሷ የሙያው ባለቤት ከሆነች በኋላ ግን ፍጹም የተሳሳተ አመለካከት እንደነበር መገንዘቧን ትናገራለች፡፡ከሁሉም ወገን የሚቀርቡትን ቅሬታዎች ያለ መሰልቸት ታስተናግዳለች፡፡ እንደ ስምረት እምነት የዳኝነጥ ስራ ታጋሽነት ጎልቶ የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ይህንን ከግምት ያላስገባ ሰው ለዳኝነት ዝግጁ አይደለም፡፡ እርሷም የተለያዩ እንቅፋቶች ቢገጥሟትም በትግስት ማጣት ምክንያት እደማትሸነፍ ተናግራለች፡፡በተለይ ሴት መሆኗ የዳኝነቱን ስራ ተስፋ እንዳያስቆርጣት ሁሌም አርአያ የሆኗትን ትመለከታለች፡፡ዳኛ ስምረት በሙያዋ ጥንካሬዋን ይዛ እንድትቀጥል እንመኝላታለን፡፡