የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ስብዕና አስተምህሮ

ሀገራችን ለህዝቦች ህልውና መጠናከርና ህይወት መሻሻል እንደ ሻማ በወላፈኑ የቀለጡና ፍጹም ቤዛ የሆኑ እጅግ ብልህ፣ ቆራጥና ታታሪ ወጣቶችን አምጣ ወልዳለች። ኮትኩታም አሳድጋለች። የእነዚህ ልጆቿ መልካም ስብዕናና ውለታ የለውጥና የብልጽግና ብርሃን ፍንትው አድርጓል። የድህነትን ሰንሰለት ለመበጣጠስ፣ የሰው ልጆችንም መከራ ለማበስ ታላቅ አቅም ሆኗል።

ታዲያ የዚህ መልካም ስብዕና አስተምህሮት ዘመን ይሻገራል፤ ከአድማስ አድማስ ይናኛል። ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የዚህ አኩሪ ትውልድ ታላቅና አርአያ መሪ ናቸው። ህልፈተ-ህይወታቸው፣ መስዋዕትነታቸው በሀገር አቀፍና በዓለም -አቀፍ ደረጃ ለአምስተኛ ዓመት እየታሰበ ነው። ይህን ስናደርግ የዚህን ታላቅ መሪ አብነታዊ ማንነት በየፈርጁ  በመተንተን ላቅ ያለ ትምህርትና ልምድ መቅሰም ይገባል። ይህን የምናደርገው የታላቁን መሪ መስዋዕትነት ከማሰብ ባሻገር የድህነትና ኋላቀርነትን ሰንሰለት በጣጥሰን ለመጣል ትልቅ ግብ ስለሰነቅን ነው።

ይህን ህያው ግብ ዳር ለማድረስ የታላቁ መሪን ሁለንተናዊ ዘመን ተሻጋሪ መልካም ስብዕናዎች መለስ ብሎ መቃኘት አሁንም ሆነ ለወደፊት የበለጠ እንድንበረታ ያደርገናል። የትግሉ ጉዞው ልዩ ልዩ መሰናክሎች ሲገጥመው ትውልድ በጥበብ  መሰናክሉን ተሻግሮ በመታደስ ድል መጨበጥ እንደሚቻል ይቀሰቅሰዋል። ስለዚህ ይህ ጽሑፍ በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ስብዕናዎች ላይ ማተኮሩ አሁንም ካለፈው ትውልድ ለመማር የትግሉን መስመር አጥብቀን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለመበጣጠስ ያለንን ዝግጁነት ያረጋግጣል።

ታላቁ መሪ ለህዝቦች ልዕልና ህይወታቸውን  የሰጡ መሪ

የታላቁ መሪ ህልፈተ-ህይወት ሀዘናቸው መበርታቱ ምክንያታዊ ነበር። አለኝታ፣ መኩሪያና መመኪያ መሪያችንን በድንገት ሞት ሲነጥቀን ከነበረን ሩቅ ግብና ተስፋ አኳያ ያስደነግጣል። ታላቁ መሪ የኢትዮጵያ ህዝቦችን የህልውና አደጋ ተንትነው ከዚህ አደጋ የሚወጣበትን ዘላቂ መፍትሔ በመተግበር ጣፋጭና አርኪ የአመራር ዘመን አሳልፈዋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች የነጻነት ትግል ፋኖዎች ናቸው። የአይበገሬነት፣ የነፃነት ተምሳሌት። የአፍሪካውያን የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ብርሃን ናቸው። ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያውያን እጅግ አዛኝ፣ ሩህሩህና ደጋግ ህዝቦች ናቸው። በጋራ ተሳስቦና ተከባብሮ የመኖር ጠንካራ እሴት ባለቤት፣ በማንአለብኝነት የማንንም ጥቅምና ህልውና የማይነኩና ጨዋ ህዝቦች ናቸው። ከቀያቸው መልካም የጉርብትና እሴት ይቀዳል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ኩሩና የነፃነት ተምሳሌት ህዝቦች ባለፉት ሥርዓቶች ህልውናቸው በተለያየ መንገድ አደጋ ተጋርጦበት ቆይቷል። ሥርዓቶቹ የዚህ ህዝብና ሀገር ህልውና በጥረቱና በስኬቱ ከፍ ያለ ማማ ላይ እንደወጣ እንዲቆይ ማድረግ ተስኗቸዋል። ይልቁንም በእርስ በርስ ጦርነት እየተበላሉ ኢትዮጵያ የጦርነት፣ የድርቅና የረሃብ ተምሳሌት ወደ መሆን ወረደች። ታላቅ የሥልጣኔ ማማ ላይ የነበረው ህዝባችን ልዩ ልዩ ሀብቶቹና ጸጋዎቹ ደጁ ላይ ሞልተው ተመጽዋች ሆነ፤ በረሃብና በቸነፈር እንደ ቅጠል ረገፈ።

ታላቁ መሪ በአፍላ ወጣትነታቸው ይህን ሥርዓት ተፋልሞ በመጣል የህዝቦችን ተስፋ የሚያለመልም ሥርዓት ለመገንባት ሲነሱ እጅግ ቁርጠኛ መሪ እንደሆኑ ያረጋግጣል። የህዝቦችን ልዕልና መመለስ እጅግም ብልህነትንና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። የሚመጣውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመቀበል መዘጋጀታቸውንም ያስተምራል።

የተፈጸመውም እውነታ ይኸው ነው። አቶ መለስ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ልዕልና ወደነበረበት ክብርና ሞገስ ለመመለስ ለትጥቅ ትግሉ ስኬት ጣፋጯን የወጣትነት ህይወታቸውን አበርክተዋል፤ ታግለው ሺዎችንም አታግለዋል። የትግሉን መስመር እያነጠሩ የበረሃውን ህይወት ተጋፍጠዋል። ትግሉ ዕለታዊ ድሎችን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ግቡን እያለመ መሰናክሎችን ሁሉ በዘላቂ የህዝቦች ህልውና ግንባታ ግብ እየተጠገነና እየተስተካከለ የህዝባዊ ድል ባለቤት ሆነ- ግንቦት 20።

የታላቁ መሪ መልካም ስብዕናና ሀገራዊ አሻራ ከድል በኋላም እጅግ እየተጠናከረ ነው የመጣው። የትጥቅ ትግል ድል አንድ ምዕራፍ እንጂ የህዝቦችን ህልውና በዘላቂነት የሚያረጋግጥ የድል ምዕራፍ እንዳልሆነ እርግጥ ነው። ስለሆነም አቶ መለስ በህዝቦች የነቃ ተሳትፎ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መገንባት በዚህ ጠንካራ ሰነድ አማካኝነት ዴሞክራሲያዊ፣ ልማታዊና አስተማማኝ ሠላም የነገሰበት ሥርዓት እንዲመሠረት ቁልፍ የመሪነት ሚና ተጫውተዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ዋነኛ የህልውና አደጋ ከውስጥ የመነጨ መሆኑን በመተንተን በብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ተሳትፎና መፈቃቀድ አዲሲቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትገነባ ታግለዋል።

ታላቁ መሪ የኢትዮጵያ ህዝቦች ክብር በዘላቂ ልማት እንዲጠበቅ ታላላቁን አቅደው በቁጭት በማስፈጸም አርአያ ናቸው። ከድህነት በላይ ክብርን የሚጎዳ አዋራጅ እንደሌለ አበክረው አስተምረዋል። ስለዚህ ከቁጥ ቁጥ አሠራር በመውጣት ድህነትን የሚያስታግሰውን ሳይሆን የሚፈውሰውን ልማት በማስፈጸም የልማት ጀግና መሪ ነበሩ። ስለሆነም አይደፈሩም የተባሉ ፕሮጀክቶች በጋራ ጥረታችንና በውስጥ ሀብታችን እየተገነቡ ነው።

ከዚህ ባሻገር አቶ መለስ የኢትዮጵያ ህዝቦች ክብር በዲፕሎማሲያዊ መስክ እንዲጎመራና እንዲቀጥል ሠርተዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ሥርዓቶች ቢለዋወጡባቸውም ለአፍሪካ የነፃነት ትግል ያደረጉት አስተዋጽኦ ጸንቶ የኖረ እንደሆነ በአደባባይ ሞግተዋል። ኢትዮጵያውያን የአፍሪካ የነፃነት ትግል አባቶች ናቸው። የክፉ ቀን መጠጊያ ያላቸውን አልባሽና አጉራሽም ናቸው። ስለዚህ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሆና መዝለቋ ስጦታ ሳይሆን ለመልካም ውለታዋ የሚገባ እንደሆነ በመከራከር የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በአዲሰ አበባ በዘመነና በተደራጀ መልኩ እንዲጠናከር ታግለዋል። ለህዝቦች ልዕልናና ክብር በቁርጠኝነት መታገል ይሏል እንዲህ ነው። መከበርና መኩራት በህዝብና በሀገር ነው። ህዝብ ሲደሰት፣ በነፃነቱ ሲመካ፣ በዕድገትና ብልጽግናው ተሳስቦ ሲኖር፣ በዘላቂ ሠላሙ ህይወቱ ስትለመልምና ተስፋ ያለው ህይወት ሲመራ ያኮራል። ለዚህ በጎ ሥራ ህይወትን መስጠት፣ ያውም ዕንቁ ጣፋጭ የሆነችውን የወጣትነት ህይወት ለህዝቦች ክብርና ልዕልና ማዋል ታላቅ አስተምህሮት ነው።

አቶ መለስ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ በህዝቦች ያላሰለሰ ድጋፍና ይሁንታ የድህነትና ኋላቀርነትን ሰንሰለት በጣጥሶ እንዲቀጥል ሙሉ ህይወታቸውን ሰጥተዋል። የሥርዓቱን አቅጣጫ ጠቋሚ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመንደፍ፣ በማስረጽና በቁረጠኝነት በማሰፈጸም አርአያነቱ ላቅ ያለ አመራር ሰጥተዋል።

በተለይም ሥርዓቱ በውስጥና በውጪ ፀረ-ሠላምና ፀረ-ልማት ኃይሎች አደጋ በተጋረጠበት ወቅት የህዝቦችን ህልውና የማስጠበቅና ወደነበረበት ልዕልና የመመለስ ዓላማ ሰንቀው አኩሪና የሚመኩበት አመራር ሰጥተዋል። በመሆኑም ሥርዓቱ ከገጠሙት ፈተናዎች እየተማረ ህዝብን አቅፎ እነሆ የህዝቦችን ጥቅምን ደህንነት አስጠብቆ ቀጥሏል።

የመለስ ትውልድን የመቅረጽ ሚና

የኢትዮጵያ  አዲሱ ትውልድ የህይወት ጉዞ ባለፈው ትውልድ የትግልና የህይወት ጉዞ ላይ መመስረቱ ግድ ነው። የኋላው ከሌለ የፊቱ ሊኖር አይችልምና። አዲሱ ትውልድ ቢፈጠር እንኳ አበው ያለፉበትን ውስብስብ ህይወትና ፈተና ካላወቀና ካልተማረበት የህይወት ጉዞው የተዋጣለት ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ሀገራችን ኢትዮጵያ በአበው አኩሪ የመሪነት ትግል፣ በደም አሻራ የተገነባች ሀገር ነች። በቅርቡ የታሪክ ምዕራፋችንም የኢትዮጵያ አያሌ ወጣቶች ይህን ልማታዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍጹም ሠላም የነገሰበት ሥርዓት ለመገንባት እጅግ መሪርና ውስብስብ ትግል አካሂደዋል።

ታዲያ ታላቁ መሪ ኢትዮጵያን በመሩባቸው ዓመታት አዲሱ ትውልድ ይህን ታሪኩን እንዲያውቅ አኩሪ ሥራ ሰርተዋል። ወጣቱ በአያሌ ሰማዕታት የተገኘውን ሥርዓት ጠብቆ የራሱን አሻራ እያሳረፈ እንዲያጠናክረው ሠርተዋል። በልዩ ልዩ መድረኮች በመገኘት ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የመከላከያ ሠራዊቱ የሀገራችንን ህዝቦች ህልውና ለማረጋገጥ የየድርሻቸውን እንዲወጡ፣ የድህነትን ተራራንም በዕውቀት ገፍተው እንዲጥሉ አታግለዋል።

በትግልና ከማንኛውም ነገር በመማር ያካበቱትን ዕውቀትና የአመራር ጥበብ በመጠቀምም በተለይም ወጣቶች አፍላ ዘመናቸውን ህዝብንና ሀገርን በሚያኮራ፣ የራስንም መንፈስ በሚያረካና በሚጠቅም በጎ ሥራ ላይ እንዲያውሉት በሚዲያና በቀጥታ መድረክ አስረጽዋል። ወጣቱ ትውልድ እያንዳንዱን ሁኔታ በሰከነ መንገድ ማየት፣ ፣ ራሱንና ህዝብን የሚጠቅም መፍትሔ የማመንጨትና ወደ ተግባር የመለወጥ ብቃት መላበስ እንደሚገባውም አስረግጠው አስተምረዋል። ወጣቱ ውድ ጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀም፣ ይህችን ሀገር በዕውቀት ላይ ተመስርቶ እንዲመራና ከማንኛውም አደጋ እንዲጠብቅም ዕውቀትና የአመራር ጥበብ ለግሰው ታላቅ ኃላፊነት አሸክመውታል። በተለይም  ታላቁ መሪ ወጣቱ በህይወት ዘመኑ “ህዝቤና ሀገሬም አደረጉልኝ ሳይሆን ክብራቸውን የሚያስቀጥል ምን ውለታ ዋልኩላቸው” የሚል መንፈስ እንዲላበስ ቀርጸውታል። በመሆኑም ይህ ወጣቱ ወገኑን የማገልገል ስብዕና እንዲላበስ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ግንባታም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ወጣቱ ተመጽዋችነት የውርደት ማቅ መሆኑን ተገንዝቦ በላቡና በደሙ ሀገራዊ አስተዋጽኦም  እንዲያበረክት ወሳኝ የልማት ትጥቅ አስታጥቀውታል።

የታላቁ መሪ ትውልድን የመቅረጽ ሚና አድማስ ተሻጋሪ ነው። ትውልዶች በበጎም በመጥፎም ስብዕናቸው ሊቀረጹ ይችላሉ። በተለይም ግሎባላይዜሽን ሁለቱንም ሊያስታጥቅ ይችላል። ዓለም- አቀፍ ሚዲያው የአፍሪካን ጠንካራ ባህልና እሴት ሰብሮ ለመግባትና የራሱን ርካሽ ሸቀጥ ለማራገፍ ይፍጨረጨራል። ሌት ተቀን አፍሪካን የድህነትና የኋላቀርነት፣ የሁከትና የጦርነት ተምሳሌት አድርጎ ይስላታል። አንዳንድ ጭፍንና ደፋር ሚዲያዎችም አፍሪካውያን ራሳቸውን መሆን የማይችሉ፣ ደካሞችና ማሰብ የማይችሉ አድርገው ያራግባሉ።

ይህን በተመለከተ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በአፍሪካ ራስን የመቻል አስተሳሰብ እንዲነቃቃ የማለዳ ወጋገን ሆነዋል። ኢትዮጵያ ማንም አለሁሽ ሳይላት አድዋ ላይ የነጮችን የበላይነት ቅስም ሰብራለች። የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት ነች። ኢትዮጵያ ሟርተኞች እንዳሰቡት ሳይሆን ከርስ በርስ ጦርነት ወጥታ ሀገር በቀል ፖሊሲና ስትራቴጂ በመተግበር በተከታታይ ለስምንት ዓመታት  ያሀል ባለ ሁለት አሃዝ  ዕድገት አስመዝግባለች።

ስለዚህ አቶ መለስ አፍሪካ ራሷን መሆን እንደምትችል፣ በጽናት መቆም እንደሚገባት፣ በአፍሪካ ህብረትና በታላላቅ ዓለም - አቀፍ መድረኮች ታግለዋል። አፍሪካ የራሷ የልማትና የዴሞክራሲ መርሆዎች መፍጠር መገንባትና መተግበር እንደሚገባት አስርጸዋል። የአፍሪካ ሀብት፣ ዕውቀትና ጉልበት አፍሪካን በማልማቱና በማበልጸግ ላይ መዋል እንዳለበት ሞግተዋል። አፍሪካ የምዕራባውያን ሸቀጦች ማራገፊያ ሳትሆን የልማትና የኢንዱስትሪ እምብርት መሆን እንደምትችል ይፋ አድርገዋል። በተለይም  ታላቁ መሪ ምዕራባውያን አፍሪካውያንን በዕለት እርዳታ በመሸንገል ዕድገታችንን ለማቀጨጭ የሚያደርጉትን ድብቅ ሴራ ገትተው መሠረተ-ልማቷን የሚያሳልጥ ትብብርና ድጋፍ ላይ ቢሰሩ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አፍሪካንም ሙሉ በሙሉ ከተረጂነት ማውጣት እንደሚቻል በኢትዮጵያ ውስጥ ተጨባጭ የአመራር ተሞክሮዎችና ውጤቶችን በማረጋገጥ አስመስክረዋል።

አቶ መለስ ምዕራባውያን በቅድመ ሁኔታዎች የታጀሉ የብድርና እርዳታ ሥርዓታቸውን በማስተካከል አፍሪካን በመሠረታዊነት የሚለውጥ የልማት አቅጣጫም እንዲከተሉ ተሟግተዋል። ኒዮ ሊበራሊዝምና ታላላቅ የገንዘብ ተቋማቱ የአፍሪካን ጥቅም በታላላቅ ኩባንያዎቹ ሰንጎ የራሱን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያደርገው መፍጨርጨር የማያዋጣ፣ የጋራ ጥቅምንም የማያስጠብቅ ሥርዓት እንደሆነም አቶ መለስ በስመ ገናና የአሜሪካና የአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች በመገኘት አስርጸዋል። አፍሪካ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትነገባ መተባበር የዓለም መርህ ሊሆን እንደሚገባም በትንታኔያቸው አሳውቀዋል።

ስለዚህ አቶ መለስ አፍሪካ በራሷ ቀዳሚ ተሳትፎና ህብረት የልማት ትስስሯን ማጠናከር፣ የሠላም ችግሮቿን መፍታትና ዘላቂ የልማት ስትራቴጂዋን መንደፍና መተግበር እንደሚገባት አዲስ የመለወጥ አስተሳሰብ ገንብተው አልፈዋል። ይህ የአቶ መለስ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትንታኔ አያሌ አፍሪካውያንን ለለውጥ አነሳስቷል። በመሆኑም የራስን ብቃት ፈልጎ የማግኘትና ማንኛውንም ችግር በሀገር በቀል ዕውቀቶችና እሴቶች የመፍታት ልምድም እየዳበረ ይገኛል። በልዩ ልዩ መስኮች የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የአፍሪካን ሠላም በማናጋት ዕድገቷን በማቀጨጭ ያለውን ጫና የመተንተንና የመገንዘብ ልምድ እየዳበረ መጥቷል። ለምሳሌ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና በሱዳን ያሉ ችግሮችን በአፍሪካውያን አቅም የመፍታት ጥረቱ ተጠናክሯል።

ይህ የክቡር አቶ መለስ ሳይንሳዊ ዕውቀትና ትንታኔ ዓለም - አቀፍ ተከታዮችን አፍርቷል፤ አድናቆትንም አትርፏል። የዛሬ አምስት ዓመት በሥርዓተ- ቀብራቸው ታላላቅ የዓለም መሪዎች ጥቁር ለብሰው በሙሉ ልብ የአቶ መለስን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችና ዓለም - አቀፍ መልካም ተጽዕኖ ፈጣሪነት በአደባባይ መስክረውታል።

እነዚህ ታላላቅ ሰዎች የአቶ መለስ ምጡቅ ስብዕናና አስተሳሰብ ድንበርና ጠረፍ የማይከልለው፣ ዘርና ብሔር፣ ዕድሜና ፆታ፣ ሃይማኖትና እምነት፣ ቦታና ጊዜ የማይገድበው ለሰው ልጆች ሁሉ መፍትሔ እንደሆነ በይፋ አረጋግጠዋል።

በአጠቃላይ መለስ ለሰው ልጅች ምቾት ታላቅ ሥራ የሰሩ፣ ለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታቸው የተፋለሙ በዴሞክራሲያዊና ተራማጅ አስተሳሰብ ህዝብና ሀገር የመሩ ወደ ዕድገትና ብልጽግናም ያደረሱ መሪ ናቸው።

ታላቁ መሪ ስብዕናውን ለወጣቶች ለማስታጠቅ ዘወትር የሚያነብ፣ ከተሞክሮ የሚማር፣ ያወቀውንም በተግባር የሚተረጉም የምጡቅ ስብዕና ባለቤት ነበር። ታላቁ መሪ በዚህም አያሌ ጠንካራ አመራሮችን፣ ታታሪ ወጣቶችንና ጀግና የመከላከያ ሠራዊት አባላትን አፍርቷል።

ይህ በዚህ እንዳለ አቶ መለስ ራሱ በተቀዳጃቸው ዕውቅናዎች የሴቶች ብቃት እንዲጎለብት የፈጠረው መልካም ተጽዕኖ ምንጊዜም ሲታወስ ይኖራል። ታላቁ መሪ ዓለም - አቀፍ ዕውቅናውን ከግል መኩሪያና መድመቂያ በዘለለ ተጠቅሞበታል። ለምሳሌ ያራ ፋውንዴሽን መለስ ላበረከተው አህጉራዊና ዓለም - አቀፋዊ የመሪነት ሚና ዕውቅና በመስጠት እንደሸለመው ይታወቃል። ይሁን እንጂ አቶ መለስ ሴቶች ባለፉት ሥርዓቶች ድርብ ድርብርብ ጭቆና የተጫነባቸው መሆናቸውን በማመን ሽልማቱን ሴት ተማሪዎችን በዕውቀት ለማትጋት እንዲውል ወስነዋል። መለስ’ ሴቶችን ማስተማር ትውልድን ማስተማር ነው’ በሚል ብሂል በአዎንታዊ እርምጃ ሴቶችን የማትጋትና ወደ መሪነት የማውጣት ጥረቱ ፍሬ እንዲሰጥ ከፍተኛ ሥራ ሰርቷል።

በመሆኑም መለስ ሴቶች በሀገራችን ልዩ ልዩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመሪነትም ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ቁርጠኛ አመራር አበርክቷል። መለስ በሀገራዊ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አመራር ከመስጠት ባሻገር በግል የሴቶች ህይወት እንዲሻሻል ያበረከተው አስተዋጽኦ በሁሉም መስክ የሴቶች ተሳትፎ እንዲበረታታ አስችሏል።

ታላቁ መሪ በማንኛውም ቦታና አጋጣሚ ተደማጭና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪ

አቶ መለስ ከግንቦት 20 ህዝባዊ ድል በኋላ የተረጋጋችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ታትረዋል። በተለይም ሠላሟ በህዝቦች ተሳትፎ ታጅቦ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን በእጅጉ ሠርተዋል። የኢህአዴግ ሠራዊት  የሽግግሩ መንግሥት ሠራዊት በሆነበት ወቅት በልዩ ልዩ መድረኮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየተገኘ የሠራዊቱን ሚና በግልጽ በማስረጽ ላቅ ያለ አመራር ሰጥተዋል። የሀገራችን ህዝቦች ወደ አዲስ የለውጥና የልማት ምዕራፍ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሸጋገሩ ሠራዊቱ ጠንካራ የሠላም ኃይል መሆን እንዳለበት አስተምረዋል። ድሉ በአያሌ ጀግኖች ሰማዕታት የተገኘ በመሆኑ የሰማዕታት አደራ ተጠብቆ የህዝቦችን ደህንነትና ጥቅም እያረጋገጠ እንዲጠናከር ከፍተኛ የአመራር አሻራ አሳርፈዋል።

በየግዳጆቹ ስፍራ እየተገኘ ህዝብን የያዘ ኃይል የድል ባለቤት እንደሚሆን አስርጸዋል። ምንጊዜም ሠላም በህዝቦች እጅ ውስጥ ከሆነች እየተጠናከረች እንደምትቀጥል አስተምረዋል። አቶ መለስ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣  እንዲሁም እጅግ ጸጥታው አስጊ ነው በተባለው ሶማሊያ በአካል እየተገኘ የሠራዊቱን ሞራል ገንብተዋል። ለስኬቶቹና ይህን በማረጋገጥ ሂደት ለተከፈለው መሰዋዕትነትም ታላቅ ክብር ሰጥተዋል። ይህ በመሆኑም ሠራዊቱ በየጊዜው ከባድ የኃላፊነት ስሜት ሰንቆ ተደራራቢ ድልና ስኬቶች አስመዝግቧል። አቶ መለስ የሠራዊቱ አመራሮች ወታደሮቻቸውን የሚመሩበትን መልካም ስብዕና፣ ጥበብና ብልሃትም በማስረጽ በማንኛውም ፈታኝ ወቅት መርተው ተዋግተውና አዋግተው ድል የሚጨብጡ በርካታ አዛዦችንም አፍርተዋል።

በተለይም የኤርትራ መንግሥት ዳር ድንበራችንን በወረረበት ወቅት አቶ መለስ ምሽግ ድረስ በመግባት የሰጡት አመራር በየትኛውም ፈታኝ ወቅትና ቦታ ተገኝቶ የስኬት መንገድን የሚያመላክት አቅም የሚጨምርና ሞራል የሚገነባ መሪ መሆናቸውን አረጋግጧል።

አቶ መለስ በልዩ ልዩ ወታደራዊ ፍልስፍናዎችን እየቀመሩና እያተቡ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ብቁ ወታደራዊ አመራር ለመፍጠር በትጋት ሠርተዋል። የሠራዊታችን ህገ-መንግሥታዊ መሠረት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን ለማጠናከርና ራሱንም ተጠቃሚ ለማድረግ ያለውንም ፋይዳ በተከታታይ ዓመታት አስተምረዋል። እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱ የተገነባበትን ዓላማ በማስረጽ ሠራዊቱ ላመነበት ህገ-መንግሥታዊ ዓላማ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጠናከር ሳያወላውል ህይወቱን እንዲሰጥ የአቶ መለስ መልካም ተጽዕኖ ወደር የለውም።

ከዚህ ባሻገር አቶ መለስ ከህዝብ ተፈጥረው የህዝቦች ችግር ልባቸውን ሰብሮ የሚሰማቸው ታላቅ መሪ ነበሩ። ፖሊሲና ስትራቴጂዎቻቸው ገጠር ድረስ ገብተው ለውጥ ማምጣታቸውን ይከታተላሉ። የአርሶ አደሩን ድምጽ ለመስማት በርካታ የገጠር ቀበሌዎችን ዳሰዋል። በደስታቸው ፊታቸው ሲፈካ፣ በብሶታቸው ደግሞ ፊታቸው ሲጠቁርና ልባቸውም ሲነካ አይተናል፤ ከዚህ ባለፈ የአርሶ አደሮቹ የትግል ጽናት፣ መንግሥትን የመደገፍ፣ የመተቸትና የመምከር ጥረት እንዳይደበዝዝ አደራ አስታጥቀው ይመለሳሉ። መፍትሔ ለሚሹም አስቸኳይ ጥያቄዎች የሚጨብጥ ተስፋ ይሰጣሉ። የገቧቸውን የአመራር ቃል መተግበራቸውንም ያረጋግጣሉ። ከህዝብ አብራክ ወጥቶ ህይወትን ለህዝብ ህልውናና ጥቅም መስጠት እንዲህ ነው።

በአጠቃላይ የታላቁ መሪ መልካም ስብዕና አስተምህሮት ጥልቅና ሰፊ ነው። ከህዝብ መፈጠራቸው ታላቅ ኃላፊነት እንዳስታጠቃቸው ያምናሉ። ስለሆነም ሙሉ ህይወታቸውን የህዝቦችን ህልውናና ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ፋይዳ ላይ አውለውታል። ህዝባችን የድህነትን ተራራ በዕውቀት፣ በራሱ አቅምና ሀብቶቹ ታግሎ እንዲጥለው ላቅ ያለ አመራር ሰጥተዋል። ወጣቶች በዕውቀትና በሰከነ አዕምሮ ህዝባዊ አደራ ተቀብለው ሀገር የመምራትና የመለወጥ ኃላፊነት እንዲሸከሙ ተጽዕኖ ፈጥረዋል።

    ህዝቡ የመንግሥት ዋነኛው አቅም በመሆኑም የመንግሥትን ጥረት በመደገፍ፣ እጥረቶቹን በመተቸትና አመራሮቹንም በመሄስ ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጉልህ ድርሻ ተወጥተዋል። ከዚህ ባሻገር አቶ መለስ ዘመናዊና ህገ-መንግሥታዊ ሠራዊት በመገንባት ሂደት ወታደራዊ ንድፈ-ሃሳብ፣ ዶክተሪንና የአሠራር መመሪያዎች በመንደፍ ሠራዊቱ ግልጽ ዓላማና ተልዕኮ ይዞ ህገ-መንግሥታዊ ሚናውን እንዲጫወት ጉልህ አመራር ሰጥተዋል። እንዲሁም በየትኛውም የግዳጅ ቀጣና በመገኘት የሠራዊቱን ሞራል ገንብተዋል። ለድልና ስኬቶቹ ዕውቅና በመስጠትም ሠራዊቱ ባበረከተው አስተዋጽኦ እንዲኮራ ተልዕኮውንም አጠናክሮ እንዲቀጥል ታላቀ አሻራ አሳርፈዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!