ስኬታማው የውጭ ግንኙነታችን

 

ፈጣን የኢኮኖሚ ልማትን፣ የዴሞክራሲ ግንባታንና ሠላምን ማረጋገጥ ለአንድ ሀገር የህልውና ጉዳይ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። በመሆኑም መንግሥት ለህልውናችን ቁልፍ ለሆኑት ጉዳዮች ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥቷል። መንግሥት የተከተለው አጠቃላይ ሀገራዊ የፖሊሲ አቅጣጫም ይህንኑ መሠረታዊ እውነታ በሚገባ ያገናዘበ  እንደሆነ ይታመናል። ይህ ካልሆነ ግን የአንድ ሀገር ህልውና የደህንነት ስጋት ላይ መውደቁ የማይቀር ነው። ከዚህ አኳያ የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለሀገራዊ ህልውና ፋይዳ የሚኖረው የኢኮኖሚ ልማትን፣ ተልዕኮን፣ ዴሞክራሲንና ሠላምን የሚያረጋግጥ ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ሀገራችን ለከፍተኛ አለመረጋጋትና ተዳርጋ ህልውናችንና ደህንነታችን አስጊ ሁኔታ ላይ መውደቁ የማይቀር ነው።

በአሁኑ ጊዜም በሀገራችን ባለው ለውጥ የመጀመሪያ የተወሰደው ርምጃ ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነትና ለ20 ዓመታት የነበረው ቁርሾ እልባት ማግኘት የበሳል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የሚያመላክትና ቀጣናውን ከስጋት ነጻ ማድረግ መቻል እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር አንዱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ዕድገት አመላካች ገጽታ ነው።

የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ ያለው ሆኖ የተቀረጸ ነው። መሠረታዊ ይዘቱ ሥር-ነቀል የሆነ በውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲኖር የሚያስገድድ ነው።  በመሆኑም የተወሰደው ይህ ርምጃ የሀገራችንን ታሪክ የቀየረና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ በቀጣናውም ሠላም ያበሰረ ነው።

በመሆኑም አካሄዳችንን  ወደ ውስጥ በማተኮር የራሳችንን የቤት ሥራ በቅድሚያ እንድንሰራና ውስጣዊ ጉድለቶችን ከለየን በኋላ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው እነዚህ ክፍቶች ለሟሟላት እንዲያስችል ሆኖ ተቀርጿል።

የዚህ መነሻ ፖሊሲያችን የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በሀገራችን ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣን ልማት ማረጋገጥ ህዝቡ ከድህነት፣ ከድንቁርና እና ከኋላቀርነት ተላቆ የተመቻቸ ኑሮ እንዲኖር ለማድረግ ወሳኝ ነው።

የሀገራችን ህዝቦች እጅግ መሠረታዊ የሆነው ጥያቄ ድህነትንና ኋላቀርነትን ማስወገድ ነው። የፈጣን ልማት ጉዳይ የህዝቡን ኑሮ የማሻሻል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ህልውና የማረጋገጥ ጉዳይም እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣን ልማት ማረጋገጥ የህዝቡን ኑሮ በማሻሻል፣ ሀገራችንን በዴሞክራሲያዊነት ከፊት ለማምጣት ይረዳል።

የውጭ ግንኙነታችን ፍሬያማ፣ ጠንካራና ተሰሚነት ያለው እንዲሆን እና በዓለም መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን የዴሞክራሲ ሥርዓት በሀገራችን እውን እንዲሆን ማድረግ፣ የህዝቦችና የዜጎች መብቶች ተከብረው፣ መልካም አስተዳደር ሰፍኖ፣ ህዝባችን በተረጋጋ መንፈስ ሠርቶ እንዲኖር ማድረግ ሲቻል ነው። ይህም የዓለም  ሀገራት ለትብብር በራችንን እንዲያንኳኩ ተስፋ ይሰጣቸዋል። በአሁኑ ጊዜም ያለው የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ የዓለም ሀገራት ትብብራቸው እንዲጠናከር አድርጓል፤ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ተሰሚነታችን ከፍ እንዲልም አስችሏል። የዚህ ማሳያና መመልከቻ መነጽራችን የሚሆነው ደግሞ በፖሊሲው ውስጥ የሀገራዊ  ክብር ማስጠበቅ መነሻ መሆኑ ነው።

ሀገራዊ ክብራችንን  የሚጎዳ ፍላጎትና ግንኙነት ተፈጥሯል።በማለት ሀገራትን በወዳጅነት ወይም በጠላትነት የመፈረጅ አዝማሚያ በአንዳንድ ሀገራት ይታያል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በመደመር ስሌት ሁሉንም የቀጣናው ሀገራት ወደ ሠላም በመደመር ከፍ ወደ አለ የርሰ በርስ ግንኙነት ማድረስ ችላለች።

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር የምታደርገው ግንኙነት ሠላማችንን ለመጠበቅ የሚያስችለን ዓለማዊና አካባቢያዊ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ እስካሁን ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሚና ተጫውታለች፤ በቀጣይም የላቀ ሚና ትጫወታለች።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ   ህብረት (AU) እና  ከአባል ሀገራትም ሰፊ የፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች። ሀገራችን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ጠንካራና ጤናማ ነው።

 በአጭሩ ሀገራችን ከአፍሪካ ጠይቃ የምታጣው እና ተጠይቃ  የምትከለክለው ነገር የለም። የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት በዚህ በሀገራችን መገኘቱ የዚህ ውጤት ማሳያ ነው። በተጨማሪም ለከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት እየበቃን ሀገራችን የሌሎች ሀገራት ተወካይ ሆና በዓለም መድረክ ላይም እናገኛታለን። በሌላ በኩል የዚህ ማሳያ ደግሞ በተለያዩ የሠላም ማስከበር ግዳጆች ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ብቸኛ ተመራጭ ሀገር አድርጓታል።

   በተለያዩ የዓለም ፎረሞችና ስብሰባዎች ላይም የአፍሪካ ተወካይ ሆና መገኘቷ የተለመደ ሆኗል። ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ውስጥ ደግሞ አንዱ የሆነው ወታደራዊ ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው።

  የኢፌዴሪ መከላከያ ወታደራዊ ዲፕሎማሲ (ትብብር) ሥራዎች መነሻና መድረሻው ሀገራዊ ፍላጎትና ዓላማን መሠረት ያደረገ ነው። የሀገራዊ ፍላጎትና ዓላማ በኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ላይ በግልጽ በተቀመጠው መሠረት የደህንነታችን መጀመሪያም መጨረሻም ሀገራዊ ህልውናን ማረጋገጥ በመሆኑ፤ የሀገራችን ፍላጎት (National Interest) ልማትና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ ነወ።

ስለሆነም የፖሊሲውና ስትራቴጂው መነሻ በሀገሪቱ ህልውና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የሀገሪቱ ውስጣዊ ችግሮችና የአደጋ ተጋላጭነት እንደሆኑና ዋነኛ ትኩረቱም በሀገር ውስጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሆኖ ምልክታውን ወደ ውስጥ በማድረግ ካለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ሥራዎቹን ያከናውናል።

በመሆኑም የኢፌዴሪ መከላከያ ወታደራዊ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ሠላምና  ደህንነትን በማረጋገጥ ግጭቶችንና አለመግባባትን የሚያስወግድ የጦርነት ምንጭ የሆኑ ምክንያቶችን ለመቀነስ፣ ማንኛውንም ሁኔታ በሠላማዊ መንገድና በመቻቻል በመፍታት ሰጥቶ መቀበል በሆነው መርህ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያከብር መልክ የሚፈጸም ነው።

አስተማማኝ ሠላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ስንል በሀገራችን ሠላምና ደህንነት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በጎረቤቶቻችን፣ በአካባቢያዊና በአፍሪካ በሌላው ዓለም ግጭትን በማስወገድ ሠላማዊ እንቅስቃሴ ነው። ምክንያቱም በአፍሪካም ሆነ በሌላው ዓለም የሚፈጠር ግጭት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሌላኛውን ሀገራት መንካቱ ስለማይቀር ነው።

ለምሳሌ ብንጠቅስ እንኳ አፍሪካዊቷ ሀገር ሊቢያ መንግሥት አልባ መሆኗ የሽብርተኞች መናኸሪያ አድርጓል። ንጹሓን ዜጎቻችንን በሞት እንድናጣ አሰቃቂ  ግፍ እንዲደርስባቸው አድርጓል። በዚህ ነው የአንዱ ሀገር ሠላም የሌላው ሀገር ሠላም ነው የምንለው።

በአጠቃላይ መልኩ የኢፌዴሪ መከላከያ ወታደራዊ ዲፕሎማሲ (ትብብር) ከጎረቤት ሀገራት (ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች)፣ በአጠቃላይ አፍሪካ ሀገራት፣ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከአረብ ባህረ ሠላጤ ሀገራትና ከኤሽያ ሀገራት ጋር በሚያደርገው ወታደራዊ ትብብሮች ከሀገራችን ደህንነት አኳያ ያለው ፋይዳ እና ጠቀሜታን መነሻ በማድረግ ነወ።

ተቋሙ ይህንን አደረጃጀት ሲያስቀምጥ መሠረታዊ መርሆዎቹን በግልጽ አውጥቶ ነው። ለዚህም ያመች ዘንድ ዋና ዳይሬክቶሬት ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን፤ መነሻ መርሆዎቹም ተልዕኮን መሠረት ያደረገ አሠራርና አደረጃጀት መከተል፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ማስቀደም፣ የሰጥቶ መቀበል አሠራርን መከተልን በጋራ ጉዳይ ላይ በትብብር መሥራት የሚሉትን በመያዝ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ወታደራዊ ትብብሮችን እያካሄደ መጥቷል። ልዩ ልዩ ተግባራትንም ያከናውናል። የዳይሬክቶሬቱን ሥራዎች ከዚህ በታች በተናጠል እንመልከት።

የትብብር ስምምነትና ግንኙነት

መከላከያ ከውጭ ሀገራት የፀጥታ ተቋማት ጋር የስምምነት ሰነድ በማዘጋጀት ሰነዱም ዓለም - አቀፍ ህግንና የሀገራችንን ህልውና ያከበረ ሆኖ እንዲሁም የመከላከያን ፍላጎትና ግዳጅ ማዕከል ያደረገ ስምምነት እንዲፈጸም በማድረግ ስምምነቶችን መሠረት ያደረገ ሥራም እንዲሰራ  ክትትል ያደርጋል። ዋና ዋና የትብብር መስኮች ላይም በትኩረት እየሠራ ይገኛል። እነሱም የሠላምንና የደህንንት ትብብር ሲሆኑ፤ ከቀጣናው ሀገራትና ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር የምናደርጋቸው ስምምነቶችና ትብብሮች የአካባቢውን ደህንነት ለመጠበቅ የጎላ አስተዋጽኦ አላቸው።

ሌላው ደግሞ ሽብርተኝነትን በጋራ የመዋጋት ትብብር ነው። በዚህ ትብብርም  በዓለም  ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ በግንባር ቀደምትነት እየሠራች ትገኛለች። በሶማሊያ እየተደረገ ያለው ዘመቻም የዚሁ አንድ አካል ነው። በቅርቡ እንኳ በኬንያ የተከሰተውን የሽብር ጥቃት ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ጥቃቱን ማውገዛቸው በሽብርተኝነት ላይ ሀገራችን ያላትን አቋም የሚያሳይ ነው።

የልምድና ዕውቀት ሽግግር ትብብር እና የሥልጠና አቅም ግንባታ ትብብር ደግሞ ሌላኛው ነው። ይህ የትብብር መስክ የሠራዊታችንን አቅም ከፍ ለማድረግና የተማረ  (ዘመናዊ) ሠራዊት ከመገንባት አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው። አሜሪካ፣ እሥራኤል፣ ራሽያ፣ ህንድ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሠራዊታችንን አባላት ተቀብለው  እያሰለጠኑ ሲሆን፤ በ2010 ዓ.ም 155 የሠራዊት አባላት በ2011 ዓ.ም 107  ደግሞአባላትን ወደ ውጭ በመላክ አባላቱ  በውጭ ሀገራት በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች እንዲማሩ እየተደረገ ነው። ከዚህ አኳያ ወደ ሀገራችን በመምጣት ለወዳጅ ሀገሮች የሚሰጡ አጫጭር ሥልጠናዎችም የዚሁ አንድ አካል ነወ።

ከውጭ ሀገራትም የሚመጡ ሠልጣኞችንም ሀገራችን ተቀብላ ትምህርት ትሰጣለች። በ2010 ዓ.ም   349 የውጪ ተማሪዎች በሀገራችን በሚገኙ የሠራዊቱ ተቋማት እየተማሩ ሲሆን፤ በ2011 ደግሞ 164 የአፍሪካ ሀገራት ሠራዊት አባላት በመማር ላይ ናቸው።

ዋና ዳይሬክቶሬቱም የሀገራችን የሠራዊት አባላት በውጭ በሚያደርጉት የትምህርትና የሥራ ጉብኝት እንዲሁም የውጭ ሀገራት ዜጎች በሀገራችን በሚያደርጉት የትምህርትና የሥራ ጉብኝት በማስፈቀድና በማመቻቸት ተልዕኮውን ይወጣል። በልዩ ልዩ ጊዜያት የሚገኙ ልምዶችን በመቀመር በተቋም እየተካሄደ ላለው የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ያውላቸዋል።

በአጭር ጊዜ እንኳ የአየር ኃይልና የባህር ኃይል ግንባታ ትብብር የተጠናከረ እንዲሆን በልዩ ልዩ ሀገራት የልምድ ልውውጥ በማድረግም ከፍተኛ አቅምና ግብዓት ተገኝቷል።

ዓለም-አቀፍ አካባቢያዊ ጉዳዮች

በአካባቢያችን የምንገኝበት ቀጣና ብዙ የተረጋጋ የሠላም አየር የማይታይበት ብዙ ጊዜ ግጭት የማይጠፋበት በመሆኑ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቁ ኃይል ( East Africa Stand by Force) ተቋቁሟል። የዚህ ኃይል ማስተባበሪያ (Focal Point) በኬንያ የሚገኝ ቢሆንም፤ የሎጀስቲክ ቤዙ እና የኃይል ማዘዣው በአዲስ አበባ በማድረግ የመከላከያን፣ የፖሊስንና የሲቪል ተግባሮችን እንዲያስፈጽምና እንዲያስተባብር ተልዕኮ ተሰጥቶት በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል። በዚህም በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የተለያዩ ትብብሮች በማከናወን ላይም ይገኛል።

 በመዲናችን አዲስ አበባ በመገኘቱ ለሥልጠናም ሆነ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡ እንግዶች የተሳካ የሥራ ጊዜ እንዲኖራቸው የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በዓለም-አቀፍና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ዘርፈ ብዙ (Multilateral) ጉዳዮችን በማከናወን AU, IGAD, UN, EUእና የመሳሰሉት ላይ በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።

ሀገራችን በUN እና AU የሠላም ማስከበር ሥራ ላይ ቀደምት በመሆን የጎረቤት ሀገራትን ሠላም እያስጠበቀች ነው። ይህ ስኬት እንዲቀጥል ደግሞ ዋና ዳሬክቶሬቱ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል።

በአጠቃላይ ለሀገራችን  አነቃቂና ሥር-ነቀል በሆነ መልኩ በመጣው ለውጥ ማግሥት የተለያዩ ሀገራት ከሀገራችን ጋር የወታደራዊ ትብብር ሥራዎች ለመሥራት ጥያቄ እያነሱ ነው።

አብዛኛዎቹም የትብብር ሥራውን ለማከናወን ተስማምተው ወደ ተግባር ተገብቷል። በኢኮኖሚ፣ በድንበር ጉዳይ፣ የአካባቢያዊ ሠላም፣ ህገ-ወጥነትና ሽብርተኝነትን በመከላከል፣ ቅንጅታዊ አሠራር በመዘርጋት እና ዘመናዊ ሠራዊት በመገንባት ላይ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ ለወደፊትም በዚህ መስክ ሰፊ ፍላጎት እየተስተዋለ ነው።

በተቋሙ እየተካሄደ ያለው የሪፎርም ሥራ ውጤታማ እንዲሆን እና የታሰበለትን ግብ እንዲመታ እና ጠንካራ ሠራዊት መገንባት እንዲቻል የኢፌዴሪ መከላከያ ውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ተልዕኮዎቹን በብቃት እያከናወነ ይገኛል። ለወደፊትም ጥንካሬዎቹን ለማስፋት የበለጠ ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።