ታላቁ መሪ ስለ ሠራዊታችን ከተናገሩት

“የመከላከያ ኃይላችን በአቅም ግንባታ ጥረቶች ውስጥ የሰው ኃይል ልማትን እንደዋነኛ ተግባር በመውሰድ በተለያዩ ዘርፎች በሳይንስ፣ በምህንድስና እና በሌሎችም ከፍተኛ ሙያተኛ የመከላከያ ኃይል አባላትን በማሠልጠን ረጅም ርቀት ተጉዟል።”

ተቋሙ የራሱን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስፈልጉ ሙያተኞችን ከማፍራቱም ባሻገር፣ በጀመርነው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚጫወቱ ሙያተኞች ማፍራት ችሏል።

*ታላቁ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2003 ዓ.ም የመከላከያ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የህክምና ዶክተሮችን ባስመረበት ወቅት የተናገሩት።

     በኢፌዴሪ መከላከያ ውስጥ ሰፊ የትምህርትና የሥልጠና ተቋማትን በማስፋፋት በወታደራዊ ሙያው የተካነ፣ መልካም ሥነ-ምግባርና ህዝባዊነትን የተላበሰ፣ የሚሰጠውን ግዳጅ በአኩሪ ብቃትና ጀግንነት ለመወጣት የተዘጋጀ ሠራዊት የመገንባቱ ሥራ ቁልፍ ተግባር ሆኖ ቀጥሏል።

     “ሠላምና ፀጥታ ለደፈረሰባቸው አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ፈጥኖ በመድረስና የተጣለበትን የሠላም ማስከበር ግዳጅ በአኩሪ ሁኔታ በመወጣት ከፍተኛ የህዝብ አመኔታን ያተረፈ ምስጉን ሠራዊት ባለቤት ለመባልም በቅተናል።

     የኢፌዴሪ አየር ኃይላችን የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ የውጊያ መሣሪያዎችና አውሮፕላኖችን የሚጠቀም በመሆኑ በዘርፉ ከሚታየው ፈጣን ዕድገት ጋር በተገናዘበና ኢኮኖሚያዊ አቅማችን በሚፈቅደው መጠን ሁለንተናዊ ብቃቱን ማሳደግ ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር አየር ኃይል ግዳጁን በላቀ ብቃት ከመወጣት ባሻገር፤ በማሠልጠን የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማጎልበት፣ ወጪን በመቆጠብና ልማቱን በመደገፍ የደረሰበት የዕድገት ደረጃ የሚያኮራ ነው።

     “የኢፌዴሪ አየር ኃይል ከራሱ አልፎ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ድጋፍ በማድረግ የጀመረው ሥራ የመከላከያ ተቋማችን በሀገሪቱ የልማት ጥረት ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው የተቀየሰውን አቅጣጫ የተከተለ በመሆኑ አርአያነቱ የጎላ ነው።

     *ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በ2004 ዓ.ም የኢፌዴሪ አየር ኃይል በበረራና በቴክኒክ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን አባላት ባስመረቀበት ወቅት በስፍራው ተገኝተው ያሰሙት ንግግር

     የመንግሥትና የህዝባችን ፍላጎት ጦርነት አይደለም። ነገር ግን ጦርነትን ማስቀረትና በአስተማማኝ ሠላም ልማትን ማፋጠን ነው።  ይሁን እንጂ ሠላምን ስለተመኘነው ብቻ ዕውን አይሆንም።

     የሠላምና የልማት አጀንዳችንን ለማሳካት የመከላከያ ኃይላችን አማራጭ የሌለውና የመጨረሻ ምሽጋችን ነው።

     *ታላቁ መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሚያዝያ 25 ቀን 2002 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ አዛዥነትና መምሪያ መኮንንነት ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ መርሀ-ግብር ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች ባስመረቀበት ወቀት በስፍራው ተገኝተው የተናገሩት

     … እርስ በርሳቸው በመፋለም ላይ ያሉት ሁለት ሀገሮች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በስተቀር ማንኛውንም ሌላ ኃይል አናምንም ማለታቸው ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ መድረክ እያገኘች ያለችውን ተቀባይነትና የመከላከያ ኃይላችን ተዓማኒነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።…

       የአብዬ የሠላም አስከባሪ ኃይላችን የማይሆነውን እንዲሆን የማይታሰበውን እንዲፈጸም ያደረገው በህዝባዊነቱ ብቻ ሳይሆን ከህዝባዊነቱ በሚመነጭ ጀግንነቱም ጭምር ነው። ስምሪት ገና በአግባቡ ከመጀመሩ በፊት ነው ለከፍተኛ አደጋና መስዋዕትነት የተጋለጠው። ሌሎች ሠላም አስከባሪዎች እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እንዲሉ አደጋ ከመድረሱም በፊት አደጋ እንዳይደርስባቸው ከህዝብ ተገልለው በየካምፑ ተወሽቀው ነው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት። የሠላም አስከባሪ ኃይላችን ግን መራራ የመስዋዕትነት ጽዋውን ተጎንጭቶ ከህዝብ ተነጥሎ መኖር ስለማይሆንለት ራሱን በየዕለቱ ለከፍተኛ አደጋ እያጋለጠ ተልዕኮውን የፈጸመው። ተራ ጀብዱ ይህንን ለማስፈጸም በቂ አይሆንም። ይህንን ማድረግ የሚችለው ከህዝባዊነት የመነጨ የማይደርቅ ጀግንነት የተላበሰ ኃይል ብቻ ነው። ግንቦት ሃያን እውን ያደረገው ኃይል እንደዚህ አይነቱ ኃይል ነው የነበረው። ይህንን ኃይል የተካውና የአብዬን ተዓምር የፈጠረውም ኃይል እንዲህ ዓይነት ኃይል ነው።..

     በገድላችሁና በሥራ ውጤታችሁ ኮርተናል። ወዳጅና ጠላት ገድላችሁን በታላቅ አድናቆት ሲመለከት አይተንና ሰምተን ተመክተንባችኋል።…

     *ታላቁ መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 21ኛውን የግንቦት ሃያ የድል ቀን አስመልክተው ለአብዬ ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ለተሰማራው ሠራዊታችን ያስተላለፉት መልዕክት

 

ታላቁ መሪ መለስ የአባይን ወንዝ በተመለከተ ከተናገሩት

 

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እንዳትጠቀም ለማድረግ የሚያግድ ስምምነት ስለሌለ ሦስት የተለያዩ መሣሪያዎችን፣ ስትራቴጂዎችን ነበር የሚከተሉት። አንደኛው ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ግድብ ለመስራት የምትፈልገውን ብድርና ርዳታ እንዳታገኝ ከኢትዮጵያ የተሻለ ጂኦፖለቲካዊ አቅም ስላላቸው፤ ይህንን አቅም በመጠቀም ማደናቀፍ…. ስለዚህ በብድርና በዕርዳታ  አባይ ላይ ሥራ እንዳንሰራ ማድረግ አንዱ መሠረታዊ ስትራቴጂያቸው ነበር። ሁለተኛው ስትራቴጂ የነበረው ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ማተራመስ እና የኤርትራን መንግሥት በመደገፍና በአዝማችነት በማሳተፍ በአፍሪካ ቀንድ አንድ የጥፋት ግንባር ለመመስረት ተንቀሳቅሰዋል። አስተባባሪው ሻዕቢያ ነው። አንደኛው ጫፍ አል-ሸባብ ነው። የኢትዮጵያ ፀረ-ሠላም ኃይሎች የኪራይ ሰብሳቢዎች አንድ የጥፋት ኃይል ናቸው። አንድም የትርምስ ኃይል ሆኖ ሲሰለፍ በስተጀርባው ደጋፊና አስተባባሪ፣ አንድ ደጋፊ ብቻም አይደለም። ሌሎችም አሉ። አንዱ ደጋፊና አስተባባሪ ግብፅ ነው የነበረው።

                                                                                          *        *          *

ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ እስከያዝን ድረስ ቁርስና እራታችንን በመተው ጭምር በድህነት ላይ ከመዝመት ወደኋላ እንደማንል ያስመሰከረ ግድብ ነው።

                                                                          *         *           *

እየሰራን ያለነው ግድብ እናንተን የማይጎዳ አለመሆኑ እኛ ከምንነግራችሁ በላይ የእናንተን ሙያተኞች አምጡ፤ የእኛ ሙያተኛ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ሌሎችም ሙያተኞች ጨምረን እናጥናና የነሱን ሪፖርት እናዳምጥ” ነው እያልናቸው ያለነው። ሱዳኖች ይህንን ያውቃሉ። ምንም እንደማይጎዳቸው፤ ከግድቡም ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኙ ያውቃሉ። ስለዚህ ጥያቄም የላቸውም። በሱዳን ህዝብ ላይ የተሰራ የማሳመኛ ሰፊ ሥራም የለም። ስለዚህ ጉዳዩ ያለው ከህዝብ ጋር ነው። የግብፅ መንግሥት አሁን አሁን ግንዛቤ እየያዘ የመጣበት ሁኔታ አለ። ህዝቡም የተወሰነ ግንዛቤ እየያዘ የመጣበት ሁኔታ አለ።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!