የህልሜ ምስጢሮች የጉዞ ማስታወሻ

የኢትዮጵያውያንን የብረት አጥሮች በአካል ተገኝቼ ለመጎብኘት ፣ውሎ አዳሩን ታሪኩን በብዕሬ ላጣጥም ተጣድፍያለሁ ፡፡ሌሊቱን ሙሉ ሀሳብ ስፈትል የረባ እንቅልፍ አልተኛሁም፣የነጌሌ ቦረና፣የሞያሌና የቡሌ ሆራ ፋኖዎች ህይወት ፊቴ ድቅን እያለ ደስ በሚል የሀሳብ ምጥቀት ውስጥ ከቶኝ እንቅልፍ ነስቶኛል ፡፡

     ዕለተ ማክሰኞ መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር ፡፡ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ሰማይ  ገና አለመንጋቱን ተከትሎ ጨለማ ተላብሷል ፡፡ የሞባይሌ የማንቂያ ደወል ሲንጫረር ከቁም እንቅልፌ አነቃኝ፣ሳልሄድ ከሄድኩበት የጀግኖች አምባ ተመለስኩኝ፣ሀሳቤን ሰብሰብ ቀልቤን ገታ አድርጌ ምናልባት የዘነጋሁት ነገር እንዳይኖር በማለት ገና ሳይመሽ የሸከፍኳትን ሻንጣ ዳግም ፈተሽኳት ፡፡

    እስክሪቢቶዎቼ፣ማስታወሻ ደብተሬ፣መቅረፀ ድምፄና ፎቶ ካሜራዬ ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ሁሉም ሙሉ ሁሉ ዝግጁ ነው፡፡ጉዞ ወደ ጀግኖች መንደር መሆኑ እውን ሆናዋል፣ለረጅም ዓመታት በታሪክ ብቻ የማቃቸውን እነዚህ የጀግኖች አምባዎች ዛሬ በአካል በቦታው ተገኝቼ ልጎበኛቸው ፣ታሪኩንም ልዳስሰው የዓመታት ህልሜ ሊፈታ ቀን ተቆርጡዋል፡፡

    ጉዞ ቅኝት ብዬዋለሁ፣ጀግኖችን ማሸተት ፣ምግባረ ሰናዬችን መፈለግ እውነትን መፈለግ መሆኑን ልብ ይሏል ፡፡አልነጋም ገነ ከሌሊቱ አስር ሠዓት ከሰላሳ ነው፣ቢበዛ ለሁለት አስርት ቀናት እንደማንገናኝ ለቤቴ ነግሬያቸው ፣በሠላም ተመለስ፣ በሠላም ቆዩ ተባብለን ተመራርቀናል፡፡ምርቃት፣መተሳሰብ የኢትዮጵን ቤት የሚያቆም፣፣ሀገር የሚገነባ እሴት ነው፡፡

     እርምጃዬ ፍፁም ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር፣ይህንን ሳስብ ሁለት አስርት ዓመት ወደ ኋላ መለሰኝና የመሃንዲሶቻችን የፈንጅ አወጋገድ ጥበብ አስተወስኩኝ፡፡ የተኛውን ጎረቤት እንዳልረብሽ በራሴ የኮቴ ዜማዎች ታጅቤ ለደቂቃዎች በእግሬ ከተጓዝኩ በኋላ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ተገናኘን፡፡ቤላ የሚገኛው መስሪያ ቤታችን ደግሞ የረጅሙ ጉዟችን ፊሽካ የሚነፋበት ሥፍራ ነው፡፡

     አሁን ጉዟችን አሃዱ ብሏል፡፡በላ ዳብል ገቢና ወታደራዊ ተሽከርካሪያችን በአሽከርካሪያችን መሪነት ፀጥ ረጭ ያለውን የአዲስ አበባን ንጋት ለሁለት እየሰነጠቅን ወደ ደቡብ አቅጣጫ መክነፋችንን ተያይዘነዋል፡፡መልካም ጉዞ በለን፣አሜን ብያለሁ፡፡

     ሌሊቱ አለመንጋቱንና የትራፊክ መጨናነቅ አለመኖሩን ተከትሎ ሹፌሩ ያለ ምንም ከልካይ  በፍጥነት ይከንፋል፣በልብ ቋንቋ ሳንነጋገር አይቀርምና እንደሰማኝ ሁሉ ሳንነጋገር ተግባባን፡፡ልብ በል ከአንተ ጋርም አብሬህ ነኝ፣በልባችን እናወራለን ፡፡የትም ሳትሄድ በደቡብ በኩል ዝም ብለህ ተከተለኝ፡፡ ረቂቁ ጀግንነት ነፍስ ዘርቶ፣ሥጋ ለብሶ በገሃድ ከሚታይበት ከሀገር ቀንዲሉ ማደሪያ መዋያ ሆኜ የሠላም እውነትን፣ ህይወትን፣ውበትን  እየፈለቀቅኩ  እነግረሃለሁ፡፡

    ኢትዮጵያ ምስጢረ ብዙ ናትና እግረ መንገዴን በጎዳናው ግራና ቀኝ የማስተውለውን የህይወት ገፅታ ከድርሳናት ጋር እያወሃድኩ አጫውትሃለሁ፡፡ ከመዲናችን አዲስ አበባ ሀዋሳ፣ከዲላ እስከ ጉጂ፣ የሚያዛልቀኝን ታሪካዊ ጉዞ ወግና ባህልን፣ የጀግኖችን ውሎና ህዝባዊነት  እያጣቀስኩ  እነግረሃለሁ፣ ዝም ብለህ ተከተለኝ፡፡

     በእርግጥም የምነግርህ በተግባር የኖርከውንና እየኖርክ ያለውን ሊሆን ይችላል፡፡ዝዋይ አካባቢ ስንደርስ ፀሓይ ተወለደች፣ነጋ፡፡ብርሃኗን የፈነጠቀችበት የጎዳናውን ግራና ቀኝ ውበት ልነግርህ አልችልም፡፡ለክብሯ እስክስታ የምትወርድ ይመስላል፡፡ልገልፀው  የማልችለው  የራሱ  ቀለምና  ቅርፅ  አለው፡፡

    ወረሃ መስከረም በመሆኑ መልከዓ ምድሩ ሁሉ ልምላሜ እፀዋትን ተላብሷል፣ተፈጥሮ ሁሉ አስደመመኝ፣ ተደምሜም በሀሳቤ ጭልጥ  አልኩኝ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በየመንገዱ ግራና ቀኝ ሜዳማውን የእርሻ ማሳ የሸፈነው የጤፍ፣ የስንዴ፣የበቆሎና የማሽላ አዝርዕት ልብን ያማልላሉ፣ውስጤ በደስታ ሀሴት ተሞላ፣«የሚያጠግብ እንጄራ ከምጣዱ ያስታውቃል» አይነት ሆነና ነገሩ ሳልበላ ጠገብኩኝ፡፡

     ልቦናዬን እየገለጥኩ በሀሳቤ የማስተውለውን ሁሉ መክተቤን ተያያዝኩኝ፣ጎን ለጎን ምስሉንም በካሜራዬ  ማስቀረት ጀመርኩኝ፣በአንድ ዓይኔ ለስለስ ያለችውን የማለዳዋን ፀሓይ ፣በሌላ በኩል በረጅሙ እንደ ቬሎ የዘረጋችውን እግሮቿን ተከትዬ ልገልፀው የማልችለው ህብረ-ቀለማት በጨሌው ላይ እየተመላለስኩ በመመሰጥና  በመደመም  ሻሸመኔ ደረስን፡፡

     ልብ በሉ ከሞጆ በኋላ ላሉ ከተሞችና አካባቢዎች እንግዳ ነኝ፣ሰምቼ እንጂ መጥቼባቸው አላውቅም፡፡ «ለሀገሩ እንግዳ፣ለሠው ባዳ» ይባል የለ፣እኔ ግን ለሀገሩ እንግዳ እንጂ ለሰው ባዳ አይደለሁም፣እንዴት ብትሉኝ  መከላከያ ሠራዊታችን ከሁሉም ብሄር ፣ብሄረሰብና ህዝቦች የተወጣጣና ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ የተሰለፈ ትንሿ ኢትዮጵያ በመሆኑ የሁሉንም ብሄረሰቦች ወግ፣ ባህልና እሴት ከተላበሱ የቁርጥ ቀን ልጆች አንዱ በመሆኔ አዲስ እንደማይሆንብኝ  እምነቴ ነው፡፡

     ሻሼ ቁርሳችንን በላን ሻይ ቡናም ካልን በኋላ እግረ መንገዳችን ዓይናችን እስከ ቻለልን ድረስ ከተማዋን እየቃኘን ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ከጥቂት ደቂቃዎች ጉዞ በኋላ እንኳን ወደ ቢሻን ጉራቻ በደህና መጣችሁ የሚል ፅሑፍ ከፊትለፊታችን በትልቁ ይታያል፣ወደ ቀኝ ታጥፈን የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ መግቢያ በር ላይ ደርሰናል፡፡ማንን ፈለጋችሁ ለፍተሻ ይተባበሩን፣ የዕለቱ ተረኛ የጥበቃ አባል ጥያቄ ነበር፣የጥበቃ አባሉ ቀጥሎም የመከላከያ ሚዲያ መሆናችንን ካወቀና የያዝናቸውን ንብረቶች ከመዘገባቸው በኋላ እንድንገበ  ፈቀደልን፡፡

     ከዕዙ ኮማንድ ጋር ተገናኝተን ለምን እንደ መጣንና ፍላጎታችንን ካሳወቅናቸው በኋላ ዕዙ የያዛቸው የግዳጅ ቀጣናዎች እጅግ ውስብስብና ከፍተኛ የፀጥታ ችግሮች የሚስተዋልባቸው በመሆናቸው እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻመሆኑን  በአፅኖት  ነገሩን፡፡

    በመቀጠልም ስራችንን በየትኛው ቀጠና መጀመር እንዳለብን አቅጣጫ ከሰጡን በኋላ እዚሁ አርፈን በማግስቱ በሌሊቱ ምዕራፍ ሁለት ጉዟችንን እንዲንጀምር ተነገረን፡፡ በ1952 እደተቆረቆረች የሚነገርላትና የደቡብ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ርዕሰ መዲና የሆነችው ሀዋሳ ከመዲናችን አዲስ አበባ በ275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡    

በተፈጥሮ ፀጋዎቿ የታደለች፣ዜጎች ከሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ተሰባስበው ተጋብተውና ተዋልደው፣በመግባባትና በመቻቻል አብረው በአንድነት የሚኖሩባት ይህቺው ውብና ማራኪ የፍቅር ከተማ  የጉዟችን የመጀመሪያ ምዕራፍ ነበረች ማረፊያ ቦታችንን ከያዝን በኋላ ባለችን ሠዓት ዞር ዞር በማለት  ዓይናችን  እስኪደክም  ድረስ  ከተማዋን  መቃኘት ጀመርን፡፡

     ሀዋሳና ህዝቦቿ እንግዳ ተቀባይነታቸውና ሰው አክባሪነታቸው እንደ ግሌ ልዩ የደስታ ስሜትን ፈጥሮልኛ፡፡የቱሪስት መስህብ ከሆኑት የክልሉ ገፀ በረከቶች አንዱ የሆነው የሀዋሳ ሓይቅ ለከተማዋና አካባቢዋ ልዩ የሆነ ድምቀትና ግርማ ሞገስ  አላብሷታል፡፡ በአሳ፣ በአትክልት እንዲሁም  በፍራፍሬ  ምርት  የታደለች፣በዘንባባዎቿ  ያሸበረቀች  ውብ  ከተማ ፡፡

  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሆቴሎች፣ ሆስፒታሎችና  ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ስቴዲዮም የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች፣ ለበርካታ የአካባቢ ዜጎች የሥራ ዕድልን የፈጠረው ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎችም ልዩ ልዩ ፋብሪካዎች የመዲናዋና አካባቢዋ ውበትና ገፀ በረከቶቿ ናቸው፡

    እኛም የከተማዋን ግርማ ሞገስ፣የዜጎቿን እንግዳ ተቀባይነትና ሰው አክባርነታቸውን ከቃኘን በኋላ በጊዜ አረፍ ብለን ለሁለተኛው የጉዞ ምዕራፍ ለመዘጋጀት ወደ ማረፊያችን አቀናን ፡፡መልካም አዳር ተባባልን?አሜን ብያለሁ፡፡አሁን አስር ሠዓት ተኩል ሆናዋል፣አልነጋም፣ግን ደግሞ በዚህን ሠዓት ጉዞ መጀመራችን ግድ በመሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ለጉብኝት የሚመርጧት የቱርስት መዳረሻ የሆነችውን ሀዋሳን ዳግም እስክንገናኝ ቸር ሰንብቺ በማለት ተሰናበትናት፡፡

     በዕዙ የተመድበልን የእጀባ አባላት በሠዓታቸው በቦታው ተገኝተዋል፡፡ ምዕራፍ ሁለት ጉዟችን ተጀምሯል፣ የተረሳ ነገር የለም፣ሁሉም ሙሉ ሁሉም ዝግጁ፡፡ ሩጫችን ግስጋሴያችን ቀጥሏል፡፡

ሀዋሳን ለቀን ስንወጣ ዝናብ፣ጉምና ጨለመ ተደምሮ አካባቢውን ለመቃኘት ዕድል አልሰጠንም፡፡ ቱላ፣ ሞሪቾና ይርጋለም የመሳሰሉ ከተሞችን በጨለማ ውስጥ ሆነንአለፍናቸው፡፡ ከሰማይ ወደ ምድር እየተምዘገዘገ ሲወርድ የነበረው ዝናብና ይህንኑ ተከትሎ እንደ ጅራፍ የሚጋረፈው  ቁር ሌላ ፈተና ነበር የማለደዋ ፀሐይ እንድትወጣ የሁላችንም ጉጉት ነበርና አፖስቶ ከተማ  ስንደርስ ብርዳማውና ዝናባማው የአየር ፀባይ ቀስ በቀስ ለሙቀት ቦታውን መልቀቅ ጀምሯል፡፡

  ወታደራዊ ተሽከርካሪዎቻችን  እየከነፉ ነው፣ ለነገሩ መንገዱ በራሱ የሚያረጋጋ አይደለም ፣ብረር ብረር ይልሃል፣ ይመቻል፡፡የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩን ከሆነ ቀደም ሲል መንገዱ አባጣ ጎባጣ ከመሆኑ የተነሳ ተሽካርካሪ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር፣ መንግስታችን በሠላም ውሎ ይግባና ያ ታሪክ ተቀይሯል ይላሉ ፣ እውነትም ይመቻል፡፡ 

    ልብ በሉ በየመንገዱ ግራና ቀኝ በተለያዩ ዝርያ ባላቸው ዕፆዋት ልምላሜ የተላበሱና ጥቅጥቅ ባለ ደን ተሸፈነው የሚታዩ ሰንሰለታማ ተራራዎችና አልፎ አልፎ ሜዳማ ስፍራዎች እጅጉን ያስደምማሉ፡፡

    የእንሰት፣የፅድ፣የዋንዛ፣የቡና ብቻ የትኛውን ጠርቼ የትኛውን ልተው ሁሉም አጓጊና ለእይታ ማራኪ የዕፀዋት ዝርያዎች ናቸውና ተፈጥሮ ፀገዎቿን ያለስስት ያደለቻት ምድር ብላት ማጋነን አይደለም፡፡

     አፖስቶ ከተማ ደርሰናል፣ዲላ ሞያሌ የሚወስደውን መንገድ አስተቀኝ ትተን ወደ ግራ ታጠፍን፡፡ አለታ ወንዶ ስንደርስ ቁርሳችንን በላን፣ የጠጣነውን ቡና ውፍረት ልነግርህ አልችልም፣አለታ ወንዶን ካስተዋወቋት አንዱ ቡና መሆኑን ከአጠገቤ አንዱ ሹክ አለኝ፡፡

ምን እሱ ብቻ ከነገርኩህ አይቀር ከተማዋ በሲዳማ ዞን ሥር ከሚገኙ ወረዳዎች አንዷ ስትሆን ስድስት ቀበሌዎችን በውስጧ አቅፋለች፣በዚያ ላይ ደግሞ እንግዳ አክባሪነታቸውና ተግባቢነታቸውን ልነግሪህ አልችልም፣በጣም ደስ ይላሉ፡፡ነጌሌ ቦረና ደግሞ የጉዟችን መዳረሻ ናትና ሀገረ ሠላምና ቦሬ የመሳሰሉ ከተሞችን በበረራ እንዳለፍናቸው  የአፋራራን  ጠመዝማዛማ  የቆልቁለት  መንገድ  ታያይዘነዋል፡፡

   በእነዚህ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች በተሸፈኑ የጎዳናው ግራና ቀኝ  ስለ ህዝባቸው  ሠላም መረጋገጥና ስለ ሀገራቸው ሉዓላዊነት መከበር ምንጊዜም የህገ-መንግስቱ የመጨረሻ ምሽግና የሀገር ኩራት፣ መከታ የሆኑ የህዝብ ልጆች ከፊት ለፊታችን አልፎ አልፎ በተለያዩ ርቀቶች ልዩነት ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡ እያንዳንዷን  እንቅስቃሴ  በትኩረት  እየተከታተሉ ነው፡፡

     ከፊት ለፊታችን ስድስት ወታደሮችን በጀርበዋ የሸከፈችው ወታደራዊ ፓትሮል በከፍተኛ ፍጥነት በመክነፍ ላይ ትገኛለች፡፡ እኛም እግር እግሯን እየተከተልናት ነው፡፡ምክንያቱም ብዙ መራራቅም ሆነ ለአፍታ እንኳ መቆም አይቻልም፡፡

     እነዚህ ቀጠናዎች ሀገራዊ ለውጡ ያልተዋጠላቸው የታጠቁ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ለውጡን በማደናቀፍ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካትና የህብረተሰቡን ሠላም ለማናጋት የሚንቀሳቀሱበት ነው፡፡እየተደበቁም ድንገተኛ ጉዳች ለማድረስ የሚመላለሱበት አካባቢ በመሆኑ  በእነዚህ ቀይ መስመሮች ላይ ለሰኮንድ መቆም ማለት ፈንጅ  እንደ መርገጥ  ይቆጠራልና  ይህ  እንዳይሆን  ከፍተኛ  ጥንቃቄን  ይጠይቃል፡፡

   እነዚህ ተራ ሽፍቶች መንገዶችን በመዝጋትና ኑሯቸውን ለማሸነፍ የሚሯሯጡ ዜጎችን የመዝረፍና የመግደል ዓላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠንቅቀው የተረዱት እኒህ የሀገርና የህዝብ ባለውለታዎች በእነዚህ ቀጠናዎች በተጠንቀቅ መቆማቸው ታዲያ እኛ እያለን  የሚጠፋ ህይዎትና የሚዘረፍ የህዝብና የመንግስት ንብረት የለም የሚል ቀጭን መልዕክት ለጠለቶቻቸው  እያስተላለፉ  እንደሆነ  ተረደሁ፡፡

በተወዳጇ ድምፃዊ አስቴር አወቀ ውድድ--ውድድድ ዜማ፣በዝናቡ ቅላፄና በወፎች ዝማሬ፣በእኛ የደራ ሳቅና ጨወታ በመታጀም ነጌሌ ቦረና የ21ኛ ጉና ክ/ጦር ጠቅላይ መምሪያ ደርሰናል፡፡

     ወደ ውስጥ ከዘለቅን በኋላ የክጦሩ አጠቃላይ ግዳጅና ተልዕኮ ምንድነው?ይህንኑ ተልዕኮ ለማሳካት ምን ምን ተግባራት ተከናውነዋል በሚሉና በውጤቶቻቸው ዙሪያ ማብራዊያ እንድሰጡን ከ21ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ከኮሎኔል አብረሃም  ሞሲሳና ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

    እንደ ኮሎኔል አብረሃም ሞሲሳ ሲያብራሩ ይህ የክፍለጦሩ የግዳጅ ቀጣና ሠራዊቱ ከመግባቱ ቀደም ሲል ከፍተኛ የፀጥታ ችግሮች የሚስተዋሉበት፣የመንግስት መዋቅሮች ሙሉ ሙሉ የፈረሱበት፣ ምንም ዓይነት የመሠረተ-ልማት እንቅስቃሴዎች እንዳይካሄዱ የተዘጉበት ነበር፡፡

    በሌላ በኩል አመራሮች የሚገደሉበትና የሚታሰሩበት፣ዜጎች በሰላም ወጥቶ በሠላም ወደ ቤታቸው የማይመለሱበት፣ሀብት ንብረታቸው የሚዘረፍበትና የህክምናና ሌሎች የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን  የማያገኙበት አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ቀጣና ነው፡፡

የጉና አናብስቶች ህዝባዊ የሆነው ወኔና ጥንካሬያቸው ለችግሮች እንዲምበረከኩ አይፈቅድላቸውምና ፈታኙንና ውስብስቡን የግዳጅ ቀጣና ተቋቁመው ከተፈጥሯዊ መሰናክሎች  ጋር  በመጋፈጥ  ወደ ድል አምባ ከመገስገስ  ያገዳቸው  አንዳች  ነገር አልነበረም ።

      በአንጻሩ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካትና በህብረተሰቡ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተራ ሽፍቶችና ዘራፊዎች  ከህዝብ በመነጠላቸው መግቢያና መውጫ ጠፍቷቸዋል፡፡

      ለህዝብ ልእልና የቆሙ የጉና አናብስቶች የአካባቢው ህብረተሰብ ከምበላው እና ከሚጠጣው በማካፈል መረጃዎችን በመስጠት ከጎኑ ተሰልፈዋል። እስከ መጨረሻው ድረስም ከጎኑ አልተለዩትም።የወቅቱ የጉናዎች ገድል ይህ ብቻ አልነበረም፣በአኩሪ ታሪክ የታጀበ ፣በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ አንፀባራቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ዛሬም ድረስ በድልና በስኬት ደምቆ ቀጥለዋል፡፡

     የክፍለ ጦሩ የሠራዊት አባላት ወደ ግዳጁን በተረከቡ በአጭር ጊዜ ውስጭ ለሀገራዊ ለውጡ እንቅፋት ለመሆን የሚንቀሳቀሱትንና ለውጡ ያልተዋጠላቸውን ፀረ-ሰላም ሀይሎች የህዝቡን የእለት ተዕለት ሰላማዊ ኑሮ በማደፍረስ ለግል ጥቅማቸው ማስፈፀሚያ ይዞት የነበሩትን  በርካታ የዞኑ ወረዳዎችንና ቀበሌዎችን  የመቆጣጠር ተግባራትን በማከናወን  በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበዋል፡፡

      በመሆኑም  ፀረ-ሰላም ሀይሎች ህዝብን ከህዝብ፤ ህዝብን ከመንግስት የሚያጋጭ የአፍራሽ ቅስቀሳ እንዲሁም በተደራጀ መልኩ የዘረፋ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ ሲሆን ክ/ጦሩ የዚህ አይነት ተግባር በሚፈፀምባቸው  ቀጣናዎች  ሁሉ በመሰማራት ሰላም የማስፈን ተግባሮችን አከናውነዋል።

       የአካባቢው ሰላምና ድህነት በአካባቢው ህብረተሰብ መጠበቅ አለበት በሚል መርህ ህዝቡና ሰራዊቱ በመቀናጀት የአካባቢው ሰላም እንዲጠበቅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በመጫወት ላይም ይገኛሉ፡፡“ሽፍታን ለማጥፋት ሽፍታን መምሰል” በሚል ስልት በረሃማና ደን የበዛባቸውንአካባቢዎች ተሰግስገው የነበሩ ሽፍቶችን በማሳደድ ከጥቅም ውጭ ማድረግ ተችሏል።

      ሞተር ሳይክሎች፣ ልዩ ልዩ ዓይነት ያላቸው የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር አውለዋል፡፡ እንደ ኮሎኔል አብረሃም ማብራሪያ ሠራዊቱ ይህንን አኩሪ ገድል ሲፈፅም  የህዝባችን ድጋፍ ከፍተኛ ነበር፡፡ ህዝቡ ሰላምና ዲሞክራሲን ለማስፈን የነበራቸው ፍላጎትና እንቅስቃሴ እንዲሁም ፀረ-ሰላም ሀይሎች ከአካባቢው  እንዲጠፉ ሰፊ  የሆነ  ድጋፍ   በማድረግ  ረገድም  የነበራቸው  ጉጉት  ከፍተኛ ነው፡፡     

     በመሆኑም ሰላምን ከመፈለግ የተነሳ ከሚበሉት የእለት ጉርሳቸው እየቀነሱ ሰላም ከሌለ ኑሮ የለም ፤ ሰላም ከሌለ ንብረት የለም በማለት ለሠራዊቱ  ምግብና ውሃ ከማቀበል በሻገር ጠላት የሰፈረባቸው ቦታዎች በመጠቆም እንዲደመሰስ  የነበረው  ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

      በተጨማሪም ህብረተሰቡ ከሰራዊቱ ጋር በመቀናጀት ባካሄዱት ውይይቶች በርከት ያሉ የጠላት ሴሎችን በማጋለጥ በህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ  ከፍተኛ  ሚና ተጫውቷል። ነጌሌ ቦረና ህዝቦቸዋ ዛሬ የሠላም አየር መተንፈስ ጀምረዋል፡፡ዜጎች በሰላም ወጥተው የመግባት ህልማቸው እውን ሆነዋል፡፡ እኖም ነጌሌ ቦረናናን አካባቢዋን  በአካል ተገኝቼ የመጎብኘት ጉጉትና ፣የመቃኘት ምኞቴም ተሳካ ፣የዓመታት ህልሜም ተፈታ ፡፡----ሠላም፡፡