የስልጠና አቅሞችና የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ሂደት

 

 ዘመናዊ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት ከፍተኛ ስራ ይጠይቃል፡፡ ይህን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወንና ብቁ የሰዉ ኃይል ለማፍራት ብቃትና ዘመናዊነት የተላበሱ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ ሰፊ ጊዜ፣ ብዙ ሃብት፣ ብቃት ያላቸው አሰልጣኞች፣ መምህራን፣ የትምህርት መሰረተ-ልማትና መርጃ ቁሳቁሶችም ያስፈልጉታል፡፡ በየደረጃው በሚካሄደው ትምህርትና ስልጠና የሚሳተፉ ብቁ፣ አካላዊና የስነ-ልቦናዊ ዝግጁነትን የተላበሱ ሰልጣኞች የመመልመልና የማብቃት ስራውም እንዲሁ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

እነዚህን ወሳኝ ግብዓቶች በማሟላት ዘመናዊ ሰራዊት መገንባት የሃገራችንን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ ባለፉት ዓመታት ልዩ ልዩ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ገንብቷል፡፡ ስርዓተ ትምህርት በመቅረጽ፤ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን በመገንባት፤ መርጃ መሣሪያዎችንና መሰረተ ልማቶችን በማሟላት እንዲሁም የመምህራንንና አሰልጣኞችን እውቀት፣ ክህሎትና አስተሳሰብ በመገንባት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡

በዚህ ጽሁፍ ተቋሙ የተሰጠውን ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ በብቃት ይወጣ ዘንድ የተከተለውን የስልጠናና ትምህርት አቅጣጫ እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችንና ልምዶችን ለመቃኘት ተሞክሯል፡፡ ከዚህ አኳያ ጽሁፉን ለማዳበር ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው ይትባረክ ቀደም ሲል በትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ የትምህርትና ስልጠና ጥራትና ዕድገት መምሪያ ኃላፊ ሙያዊ ማብራሪያ ስለሰጡን ከወዲሁ እያመሰገንን፤ የቃለ ምልልሱ ይዘት ለንባብ በሚመች መልኩ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ንባብ፡፡

የዘመናዊ ሠራዊት አቅም መገንቢያ መንገዶች

ተከታታይነቱንና ተመጋጋቢነቱን የጠ በቀ ትምህርትና ስልጠና የዘመናዊ ሰራዊት አቅም መሰረት ነው፤ የሚከና ወንባቸውም ልዩ ልዩ መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው ተቋማዊ ስልጠና ነው፡፡ ይህ ዓይነት ስልጠና እያንዳንዱ የሰራዊት አባል ወደ ተቋሙ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በየደረጃው በየማዕረግና ኃላፊነቱ መጠን በየማሰልጠኛ ጣቢያዎች መደበኛ ስልጠና የሚያገኝበት ተቋማዊ ስልጠና (Institutional Training) በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ስልጠና አባላት ለኃላፊነታቸውና ለስራቸው የሚመጥን መደበኛ አካላዊ ግንባታ፣ የስነልቦናና የአስተሳሰብ ዝግጁነት ማሳደጊያ ስልጠና ያገኛሉ፡፡

ሁለተኛው የስልጠና ዓይነት በየሠራዊት ክፍሎች እንደየግዳጃቸው ባህሪይ የሚደረግ ስልጠና ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የስራ ላይ ስልጠና (On-Job Training) በሚል ይታወቃል፡፡ ይህ የስልጠና ዓይነት አንድ የሠራዊት አባል ወይም አመራር በስራው ላይ እያለ የተሰጠውን ስራና ኃላፊነት በላቀ ደረጃ ለመፈፀም አዳዲስ ሀሳቦችን፣ አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ማወቅና መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ የስራ ላይ ስልጠና ነው፡፡ ስልጠናው የተዋጊውን ኃይል ስልታዊና ቴክኒካዊ አቅም ያሳ ድጋል፡፡ አመራሩ ሁሉንም የውጊያ አቅሞችና ሃብቶች አቀናጅቶ የመምራትና ግዳጅን የማሳካት ጥበብም እንዲያበለፅግ ያስችለዋል፡፡ እንዲሁም የውጊያ ድጋፍና የአገልግሎት ድጋፍ ሰጪ ስታፍ ሙያዊ ክህሎት እንዲያጎለብት ያደርጋል፡፡ ጄኔራል መኮንኑ እንዳብራሩት፤ ሰራዊቱ የሚ ሰጠውን ግዳጅ በተሻለ አፈፃፀም እንዲወጣ ያስችለዋል፡፡ ™በእውቀት፣ በክህሎትና በአስተሳሰብ የዳበረ ሰራዊት መገንባት የሚያስችል የስልጠና ዓይነት ነው∫ ብለዋል፡፡

ሶስተኛው የስልጠና ዓይነት ራስን በሂደት የማሳደግ ስልጠና (Self-Development Training) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህ የስልጠና ዓይነት ከውስጥ የሚመነጭ የራስ ተነሳሽነትን ይሻል፡፡ የሰራዊት አባ ሉም ሆነ አመራሩ በራሱ ተነሳሽነት የራሱን አስተሳሰብ፣ እውቀትና ክህሎት በሂደት ለማሳደግ ይሠራል፤ ጥረትም ያደርጋል፡፡

በአራተኛ ደረጃ የሰራዊት አቅም የሃ ገራችንና የተቋሙ የትምህርት ፖሊሲና ስትራቴጂ በሚፈቅደው መሠረት በትምህርት ይገነባል፡፡ የአካዳሚክ ትምህርት የሠራዊቱ አባላት በትምህርት ግዳጃቸውን ለመፈፀም የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት እንዲገነቡ ያግዛል፡፡

በዚህ መሰረት የመከላከያ ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት በትምህርትና ስልጠና ሰራዊቱን የማዘመን ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ከመነሻው ልዩ ልዩ ማሠልጠኛ ማዕከሎችን በመገንባትና አቅማቸውን በማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ተቋማቱን ለሚሰጣቸው የማሰልጠን ተልዕኮ ብቁ የማድረግ ተግባርም ተከናውኗል፡፡ ይህም ከፍተኛ ጊዜ፣ ሃብትና እውቀት የፈሰሰበት በመሆኑ ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአካዳሚክ ትምህርት ደረጃ ትምህርቱ የሚሰጥበትን አደረጃጀትና አቅሙን የመገንባት ስራ ተከናውኗል፡፡ ይህ በመከናወኑም ተቋሙ በውስን ተቋማት ከማሰልጠን ወጥቶ፤ የመሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ፣ የእጩ መኮንን ማሰልጠኛ አካዳ ሚዎችና ኮሌጆች እንዲሁም የልዩ ልዩ ወታ ደራዊ ሙያዎች ማሰልጠኛ ተቋሞች ባለቤት ሆኗል፡፡ በየደረጃው የትምህርት እርከን በርካታ አሰልጣኞችና መምህራንንም አፍርቷል።  

በተለይም ተቋሙ ፕሮፌሽናል ሰራዊት የመገንባት ጥረቱን በማጠናከር በ1988 ዓ/ም የመከላከያ ዩኒቨርስቲን አቋቁሟል፡፡ በዚህ ስርም የጤና ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ኮሌጆችን በመክፈት የሰ ራዊቱን የጤና ዝግጁነት በማጎልበት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በብቃት የመጠቀም፣ የማሻሻልና የመፍጠር ዕው ቀትና ክህሎት እንዲዳብር የተቀናጀ ጥረት ተደርጓል፡፡ በመሆኑም በመደበኛና ተከታታይ የማስተማር ሂደት በእነዚህ ልዩ ልዩ የጤናና የኢንጂነሪንግ ትምህርት መስኮች በከፍተኛ ዲፕሎማ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪና በዶክትሬት ደረጃ በርካታ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል፡፡

በአሁኑ ጊዜም ኮሌጆቹ የስልጠና አቅማቸውን በማሳደግ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ በመደበኛ ዲግሪ በ23 የትምህርት መስኮች እንዲሁም በድህረ ምረቃ በ24 የትምህርት ፕሮግራሞች እያስተማረ ይገኛል፡፡ የጤና ሳይንስ ኮሌጅም በ13 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ2 የሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በ5 የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ፕሮግራሞች በማስተማር ላይ ነው፡፡

ተቋሞቹ በእነዚህ የትምህርት ፕሮግራሞች የመከላከያን የሰው ሃብት እውቀትና ክህሎት ከማሳደግ ባሻገር የወዳጅና ጎረቤት ሃገሮች ሰራዊቶችን በማስተማር ወታደራዊ ትብብር እን ዲጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም መከላከያ በእነዚህ የትምህርት መስኮች ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችንና ምሁራንን በማፍራት ተዋጊው ሃይል ስኬታማ ግዳጅ እንዲወጣ ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ የውጊያ ድጋፍና አገልግሎት ድጋፍ ሰጪ ስታፍ ክፍሎችም የሰራዊቱን ግዳጆች በሚፈለገው ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት በመደገፍ ግዳጆቹ ስኬታማ እንዲሆኑ መተኪያ የሌለው ድርሻ እየተወጡ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተለይም በትምህርቶቹ የተገኘው እውቀትና ክህሎት የተቋሙን ሃብት በሃገር ውስጥ በራስ ሙሉ አቅም በአግባቡ በመጠገን፣ አሻሽሎ በመስራትና በማጣጣም እያበረከተ ያለው ሚና ወጪ በመቀነስ ረገድ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል፡፡

 ስለሆነም ቀደም ሲል ትምህርትና ስልጠናው በወዳጅ አገሮች ድጋፍ ከመስጠት ወጥቶ በሂደት ሙሉ በሙሉ በራሱ የውስጥ አቅም እንዲከናወን አስችሏል፡፡ እንደመምሪያ ሃላፊው ገለፃ፤ በአሁኑ ጊዜ ትምህርትና ስልጠና የሚካሄደው በተቋሙ ባለሙያዎችና አሰልጣኞች ነው፡፡ የስርዓተ ትምህርት ቀረፃው፣ የማስተማሪያ መጽሃፍትና ሁሉም ነገሮች የሚዘጋጁትና የሚሰጡት በራስ አቅም ሆኗል፡፡ ™ይህም ትልቅ ተቋማዊና ሃገራዊ እምርታ ነው∫ ባይ ናቸው፡፡ ለቀጣይም በዘርፉ ጠንካራ መሠረት ተጥሏል፡፡ ለወደፊት የሚደመርና የሚሻሻል ሊኖር ይችላል፡፡ ዕውቀትና ክህሎት እየዳበረ መቀጠል ስላለበት በጥናት ላይ የተመሰረቱ የስልጠና ሂደቶች ይኖራሉ፡፡ በመሆኑም የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ግዳጆች መሠ ረት ያደረጉ ስርዓተ ትምህርቶችና ማስፈፀሚያ ሠነዶች በተሻለ ደረጃ የማዘጋጀት ብቃት በተቋሙ ውስጥ ተገንብቷል፡፡

ተቋማዊ የስልጠና ደረጃዎች

በተቋሙ በየደረጃው ትምህርትና ስልጠናዎች ይካሄዳሉ፡፡ አባሉም ሆነ አመራሩ በየደረጃው የሚሠለጥንባቸው የስልጠና ተቋማት ተገንብተዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ መሰረታዊ ወታደር የመሰረታዊ ውትድርና ከተከታተለ በኋላ ባለ ሌላ ማዕረግና ሌሎች ማዕረጐች ሲጨምር ያደጉና የበለፀጉ ስልጠናዎች እየተሰጠው አቅሙን እያጐለበተ ይቀጥላል፡፡ ለዚሁ የሚያገለግል ስርዓተ ትምህርት፣ ማስተማሪያ መጻሕፍትና መርጃ ቁሳቁስ የሚዘጋጁት በተቋሙ በራሱ ባለሙያ ነው፡፡ የዕጩ መኮንኖች ስልጠናም እንዲሁ የራሱ ሂደት አለው፡፡ የመጀመሪያው የዕጩ መኰንን ስልጠና ከተከናወነ በኋላ የሻምበል፣ የሬጅመንት፣ የብርጌድ እስከ ስታፍ ኮሌጅ ደረጃ ትምህርትና ስልጠና ያገኛል፡፡

ሰራዊቱ በየደረጃው እየተማረና እየ ሰለጠነ በብቃት የሚመራበትና የሚ ሠራበት አሠራር ተዘርግቷል ማለት ነው፡፡ ይህን ለማዳበር የትምህርትና ስል ጠናው ጥራት የሚጠበቅበት አደረጃጀት ተፈጥሮ እየተሰራበት እንደሆነ ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው ያስረዳሉ፡፡ የስልጠና ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ስርዓት ተመቻችቶ እየተሠራ ነው፡፡ ይህን ድጋፍና ክትትል በማሰልጠኛ ማዕከላት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የስልጠናው ሂደት በዋና መምሪያ ደረጃም ክትትልና ቁጥጥር ይደርግበታል፡፡ እንዲሁም ከስ ልጠና ማዕከላት የሰው ኃይል በማግኘት ተጠቃሚ የሆኑ የሠራዊት ክፍሎች ጋርም በመገናኘት የስልጠናው ጥራት በስራ ላይ ውጤታማነት ይለካል፡፡ ተመርቀው የውጡ አባላትና መኮንኖች በስራ ገበታቸው ላይ የሚፈጥሩት ልዩ ውጤትና መልካም ተፅዕኖ ይገመገማል፡፡ በአንፃሩ የሚታዩ እጥረቶችም እየተፈተሹ ስልጠናዎችን ለማሻሻል በግ ብአትነት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

ስለዚህ በተቋም ደረጃ የትምህርትና ስልጠና ሂደቱ በርካታ አቅሞች መገንባቱን ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው ያረጋግጣሉ፡፡ ™በራሱ አቅም የመስራት ሂደት ዳብሯል∫ ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ የትምህርትና ስልጠና ሂደቱ በርካታ ዓመታት የተሸጋገረና በርካታ የአሰለጣጠን እውቀት፣ ክህሎትና ልምድ የተገኘበት ቢሆንም፤ አሁንም የስልጠናውን ጥራት ለማስጠበቅና ለማሻሻል በርትቶ መስራት እንደሚጠበቅ ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው አብራርተዋል፡፡

   የስልጠናው ውጤታማነት

የስልጠናና ትምህርት ውጤታማነት በልዩ ልዩ መንገድ ሊለካ ይችላል፡፡ ከተቋሙ አኳያ ብቁ ተዋጊ ሃይልና ባለሙያ እንዲሁም አመራር በማብቃት የስልጠናው ይዘትና ደረጃው ይለካል፡፡ ሰራዊቱ በተቋሙ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በአግባቡና በሚፈለገው ደረጃ በመወጣቱ መለካት ይችላል፡፡ ዋነኛው መለኪያውም ይኸው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የመከላከያ ሰራዊቱ በሃገር ውስጥ፣ በአህጉርና በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የአኩሪና ገናና ስም ባለቤት ነው፡፡ ውጤታማና የድል ሰራዊት ነው፡፡ ውጤት የብዙ ግብአቶች ውጤት ቢሆንም፤ ስልጠና የማይተካ ሚና ያበረክታል፣አበርክቷልም።  ከዚህ በተጨማሪ የተቋማችን ትምህርትና ስልጠና ባለው የተፈላጊነት ደረጃ ውጤታማነቱ ይለካል፡፡ የተቋሙ ማሰልጠኛዎችና ኮሌጆች የወዳጅና ጐረቤት ሃገሮችን ሰራዊቶች በማ ሰልጠን ተፈላጊነታቸው ጨምሯል፡፡ ከዚህ አኳያ የሌሎች ሃገሮች የስልጠና ፍላጐት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ይህ ፍላጐት የጨመረው የተቋሙ ማዕከላት የማሰልጠን ደረጃ በጐ ተፅዕኖ እየፈጠረ በመሆኑ ነው፡፡ በሌሎች ሃገሮችም ተፈላጊና ተመራጭ መሆን መቻል የስልጠና ጥራቱን የበለጠ ለማስጠበቅ እንዲሠራ አቅም ይሆናል፡፡ ጠቃሚና በተግባር ስራ ላይ የሚውል የተሻለ አቅም ለመገንባትም ይረዳል፡፡ በአጠቃላይ በተቋሙ እየተጐራረሰ የሚሄድ ከታችኛው እስከ ላይኛው አመራር ድረስ የሚሰለጥንበት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ ይህን ተከታታይነቱንና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ መፈፀምና ማስፈፀም አንዱና ትልቁ የስልጠናና ትምህርት ውጤታማነት መለኪያ እንደሆነ ብርጋዴር ጄኔራል  ዳኛቸው ያረጋግጣሉ፡፡

የአሰለጣጠን ሂደቱና ኘሮፌሽናሊዝም

በሰራዊት ደረጃ ኘሮፌሽናል ማለት በመመሪያ፣ ደንብና አሰራር አማካኝነት የሚሰራ ማለት ነው፡፡ ስራውን ውጤታማ በሆነ መንገድና በተሻለ ጥራት ማከናወንም ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ፍሬ ሀሳብ ሰፋፊ ፍቺዎች ይኖሩታል፡፡ ከራሳችን ሁኔታ አኳያ የተቋሙ የስልጠና ሂደት ሠራዊቱን ዘመናዊና ኘሮፌሽናል በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መጥቷል፡፡ ™የግዳጅ አፈፃፀሙም አኩሪ ነው∫ የሚሉት ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው፤ ከዚህ አኳያ በርካታ አብነቶችን ማውሳት እንደሚቻል ያብራራሉ፡፡

ለምሳሌ በቅርብ ዓመታትና በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን የተከሰተውን አለመረጋጋት ለማስወገድ ሰራዊቱ ግዳጆች ተቀብሎ ኘሮፌሽናል በሆነ መንገድ የማረጋጋት ስራ እየሰራ ነው፡፡ ሰራዊቱ የህዝባችንን ህይወትና ንብረት ደህንነት በመጠበቅ ስኬታማ ግዳጅ እየተወጣ ነው፡፡ ሰራዊቱ በአግባቡ የሰለጠነና የተገነባ በመሆኑ፤ ሰላምና መረጋጋቱ እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው፡፡ የተከሰቱ አለመረጋጋቶችን ሙያዊ ብቃት በተሞላበት መንገድ እያረጋጋ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በህዝቦች ዘንድ ያለው ተዓማኒነትና ተቀባይነት እየጨመረ ነው የመጣው፡፡

ወታደራዊ ኘሮፌሽናሊዝም ዓለም አቀፍ ይዘት አለው፡፡ ስለዚህ ሙያዊ ክህሎቱ እን ዲሁም ቴክኖሎጂው ከሃገር በቀል እውቀትና እሴቶች ተጣጥሞ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ™ሙያው በተጠና ሁኔታ ሃገራዊ ባህሪይና እሴት ሊላበስ ይገባል∫ ይላሉ ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው፡፡ ስለዚህ የሌሎች ሃገሮች ወታደራዊ ስልጠና ሳይንሶችን፣ እውቀቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ከሀገራችን ተጨባጭ ፍላጐትና እሴቶች ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡

ተቋማዊ ሪፎርምና የስልጠናው ሚና

ሃገራችንና ተቋሙ ከፍተኛ የሪፎርም ለውጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ተቋሙ የጀመረው የመዋቅር ማሻሻያ ውጤታማና አብሮ የሚጓዝ ስልጠና ይሻል፡፡ ከዚህ አኳያ በተቋሙ የተደረገው ሪፎርም የአደረጃጀት ለውጥ አምጥቷል፡፡ ከዚህ በፊት ሻምበል፣ ሬጅመንት፣ ወዘተ እያለ አደረጃጀቱ ይሰራበት ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሻምበል፣ ሻለቃ፣ በርጌድ፣ ወዘተ የሚል አደረጃጀት እየተዘረጋ ነው፡፡ ስለዚህ የተቋሙ የስልጠናና ትምህርት ስርዓተ ትምህርት ይህንን አደረጃጀት ማጠናከር የሚችል መሆን ይገባዋል፡፡ አፈፃፀሙም ይህን መሠረት ያደረገ እንደሚሆን መምሪያ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ስራዎችም ተጀምረዋል ይላሉ፡፡ ከታች ጀምሮ እየተጎራረሰ የሚሄድና ሪፎርሙን ወደ ተግባር በማሸጋገር ስኬታማ ግዳጅ ለመወጣት የሚያግዝ የስልጠና አካሄድ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

በመግስት የሪፎርም ፍላጐት መሰረት አዳዲስ የሠራዊት አቅሞች እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ባህር ኃይል፣ የስፔስና የሳይበር አውዶች ይፈጠራሉ፡፡ የዕጩ መኮንን ስልጠናም በቀጥታ ከትምህርት ቤቶች በሚመጡ ተማሪዎች የሚሰጥበት ስልጠና ይጀመራል፡፡ ስለዚህ የተቋሙ የስልጠናና ትምህርት ሂደቱ እነዚህን ወታደራዊ መስኮች በሚመግቡ መልኩ ያከናውናሉ፡፡ ሃገራችን አዳዲስ ወታደራዊ አቅሞችና ተቋማት እየገነባች ስለምትቀጥል አዳዲስ የትምህርትና ስልጠና አቅጣጫዎች ተግባራዊ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

የስልጠና ሂደቶቹ እጥረቶች

ሃገራችን የረጅም ጊዜ የጦርነት ታሪክ አላት፤ የአኩሪ ተጋድሎ ባለቤትም ነች፡፡ በዓለም ላይ በኩራት የሚጠቀሱና የምንኮራባቸው ትልልቅ ጦርነቶችንም አካሂዳለች፤ የአድዋ ድል ዋነኛው ነው፡፡ ልዩ ልዩ ጦርነቶችንም ከአሸባሪዎች ጋር አድርጋለች፡፡ ይህንንም በአሸናፊነት ተወጥታለች፡፡ ይህ በጣም የዳበረ ወታደራዊ ተሞክሮ ሃገር በቀል ሀብት ነው፡፡

ከዚህ አኳያ እነዚህን ተሞክሮዎች በስልጠና የምንጠቀምበት ዘዴ ቢኖርም፤ በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ አይደለም፡፡ በሳይንናዊ መልኩ ተጠንቶ ለራሳችንም ለሌሎችም የዳበረ ተሞክሮ ሆኖ የሚሠራበት የሰለጠነ አካሄድ መፈጠር ይኖርበታል፡፡

እንደ ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው ማብራሪያ፤ በሰራዊቱ ውስጥ በልዩ ልዩ ግጃጆች ተሰልፈው የተዋጉና ግዳጆችን መርተው ድል የተቀዳጁ አባላትንና አመራሮችን ተሞክሮ በተወሰነ ደረጃ በስልጠና የመጠቀም ልምድ ቢኖርም፤ የሚያረካ አይደለም፡፡ እነዚህ አዛዦችና አባላት ተሞክሯቸውንና እውቀታቸውን በመጽሐፍ ጽፈው ማስተማሪያ የስልጠና ግብዓት የማድረጉ ልምድ በሃገር አቀፍና በተቋሙ ደረጃ ክፍተት ይስተዋልበታል፡፡ ስለዚህ በዚህ መልክ ብዙ መሰራት እንደሚገባው ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የውጪ ወታደራዊ ተሞክሮዎችን ከሃገር በቀል እውቀቶችና ልምዶች ጋር በማጣጣም ስልጠናዎችን ማዳበር ይጠይቃል፡፡ በወታደራዊ ትብብሮችና አጫጭር ስልጠናዎች የሚገኙ እውቀቶችንና ልምዶችንም በዚህ መልክ በመጠቀም የሰራዊቱን ዘመናዊነት ከፍ ማድረግና ለትውልድ እንዲወራረስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የሰራዊቱ አሰልጣኞች በተጨባጭ ግዳጅ በመወጣትና በመምራት የራሳቸው እውቀትና ልምድ ስላላቸው ስልጠናውን የበለጠ ያጐ ለብተዋል፡፡ ይህም ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን እውቀት ተከታታይነት ባለው ትምህርትና ስልጠና ማሳደግና ተነሳሽነት መገንባት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የሰራዊቱ የሰው ሃብት ልማት ከሠራዊቱ ዕድገትና ግዳጅ ጋር ተጣጥመው እንዲሄዱ የጋራ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።  የማዕረግ እድገቱና ሃላፊነቱ በየደረጃው ከሰራዊቱ ስልጠናና ትምህርት ጋር እየተመጋገበ እንዲሄድ እየተደረገ ነው፡፡ በየማዕረግ እር ከኑ የቆይታ ዓመታት ስላሉ፤ በእነዚህ ጊዜ ያት ሰራዊቱ በስራ ላይ ስልጠና አቅሙን እን ዲያጐለብት እየተደረገ ይቀጥላል፡፡

ይህን የበለጠ ለማሣካት ሁሉም ማሰልጠኛዎችና ኮሌጆች በራሳቸው ሁኔታ ማደግ አለባቸው፡፡ ™አንዱ ሌላውን መተካት ስለማይችል፤ አንዱ ለሌላው መሰረት እየጣለ እየተመጋገቡ ማደግ አለባቸው∫ ብለዋል ብርጋዴር ጄኔራል ዳኛቸው፡፡ በዚሁ መሠረት ተቋማቱ በመሠረተ ልማት፣ በሰው ሃብት፣ በስርዓተ ትምህርትና ማስተማሪያ ግብዓቶች እንዲሁም በአሰልጣኞችና መምህራን እየዳበሩ ይቀጥላሉ፡፡ ይህን ማሳካት ከተቻለ፤ የተቋሙ የትምህርትና ስልጠና ሂደት ሰራዊቱ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን እያሳካ እንዲቀጥል ያስችለዋል፡፡ ሃገራዊ ፍላጐቱን እያሳካ ተወዳዳሪና ተመራጭ ሆኖ እንደሚቀጥል ያደርገዋል

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!