የሠላም ማስከበር ስኬታማ ጉዟችን

ሀገራችን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታትን ጥሪ ተቀብላ የመጀመሪያውን ቃኝው ሻለቃ ሚያዝያ 1943 ዓ.ም በኮሎኔል ከበደ ገብሬ የኮሪያ ዘማች ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥነት መላኳ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት በኮሪያ ዘመቻ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሪ ምላሽ ከሰጠበት ከ1943 እስከ 1945 ዓ.ም በነበረው ተልዕኮ በሦስት ተከታታይ ዙሮች ዓለም-አቀፋዊ የሠላም ተልዕኮውን ተወጥቷል።

 ከወደ ኮንጎ አንድ እንግዳ ነገር ተሰማ። በባዕዳን ኃይል የሚደገፈው ቾምቤ  ቡድን ካታንጋን ገንጥሎ ለመውሰድ ግጭት ጀመረ።

በወቅቱ ኮንጎን ያስተዳደሩ ወይም ይመሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ፖትሪስሉሙምባ እና ፕሬዚዳንት ካላቡቡ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መሠረት የመንግሥታቱ ድርጅት እንዲታደጋቸው ጥሪ አቀረቡ።  ተልዕኮውን ከኮሪያ ለየት የሚያደርገው ኢትዮጵያ ከ30 ሀገሮች የተውጣጣውን ሠራዊት በዋና አዛዥነት የሚመሩ ጄኔራል መኮንን ማበርከቷ ነበር።

ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ ከግንቦት 1954 እስከ ሐምሌ 1955 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ኃይል ዋና አዛዥ ሆነው ሠርተዋል። እኚህ ጄኔራል መኮንን በኮሪያው ተልዕኮም በኮሎኔልነት ማዕረግ የሦስቱም ቃኘው ሻለቃ ዋና አዛዥ ሆነው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም-አቀፍ የጋራ ደህንነትና ሠላም የጸና አቋም እንዳላትና ዓለም-አቀፍ ህግና ሥርዓት አክባሪ ሠራዊትና አመራሮች እንዳሏት መታወጁን ከሚያመላክቱ እውነታዎች አንዱ የኃይል አዛዥነት ዕድል ማግኘቷ ብቻ ሳይሆን ራሷን ችላ በራሷ አዛዦች ተልዕኮዋን መወጣት የምትችል መሆኑ መታመኑ ወጥ ሠራዊት ማዝመቷ ነው። በዚህ መሠረት ከ1952 እስከ 1955 ዓ.ም አራት ጠቅል ብርጌዶችን በተከታታይ ልካለች።

የዓለም ሠላም ጉዳይ ኢትዮጵያንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከት መሆኑን በማመን በኢፌዴሪ ህገ-መንገሥት አንቀጽ 86 ላይ ´በሀገሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ ማድረግª በሚል በውጭ ግንኙነት መርህ ላይ ተደንግጓል። ሀገራችን በዓለም -አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተሳትፎዋ ለረዥም ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ተገቶ ከቆየ በኋላ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ የርስ በርስ ጦርነት በተከሰተባቸው፤ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በኮትዲቮዋር፣ በዳርፉር፣ በቻድ፣ በአብዬ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና በማሊ የተባበሩት መንግሥታተ ድርጅት የሠላም መርሆችና ባህሪያትን ተላብሶ ሠላምና መረጋጋት በመፍጠር በሚከሰቱ ቀውሶች ሠላማዊ ህዝቦችን ከሞት፣ ከስደት፣  ከሠላማዊ መብት ጥሰትና ከንብረት ውድመት ወዘተ. በመታደግ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን ሊፈታ እንደሚችልም አሳይቷል።

በሁለቱ ሱዳኖች መካከል ለዓመታት በተካሄደ የእርስ በእርስ ግጭት የበርካታ ንጹሓንን ደም ያፈሰሰውን ጉዳይ እልባት ለመስጠት የተባበሩት መንግሥታት የሠላም አስከባሪ ኃይል እንዲገባ መወሰኑን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ታሪክ አዲስ ክስተት ፈጥሯል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የአንድ ሀገር ሠራዊት በብቸኝነት የሠላም አስከባሪ ሆኖ ሲመርጥ ግን የኢትዮጵያ ሠራዊት የመጀመሪያው ነው።

ይህም የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ከሁሉም ሀገሮች የተውጣጣ የሠላም ማስከበር ኃይል እንዲገባ ሃሳብ ሲያቀርብ ሁለቱም ተፋላሚ የሆኑ ሱዳኖች የኢትዮጵያ ሠራዊት ካልሆነ በስተቀር የሌላ ሀገር ሠራዊት እንዲሰማራብን አንፈቅድም በማለታቸው ነው። ከምንም በላይ ግጭቱ የተከሰተባቸው ሀገራት የጎረቤት ሀገር የሠላም ማስከበር ሠራዊት ላይ እምነት ማሳደራቸው ሌላ ያልተለመደና ከዚህ በፊት ያልታየ ታሪካዊ ክስተት እንዲሆን አስችሎታል።

በእርግጥ የሁለቱ ሱዳን መንግሥታት ይህን የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ኢትዮጵያ በብቸኝነት ትወጣለች ብለው የጋራ እምነት ላይ የደረሱት ያለ ምክንያት አልነበረም። ኢትዮጵያ ለዓለም ሠላም መስፈን ያላትን ቁርጠኝነት በሚገባ ስለተረዱና የኢትዮጵያ ሠራዊት ዲስፕሊን እንዲሁም ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ስለሚያውቁና ግዳጁን ገለልተኛ በሆነ መልክ በብቃት የመፈጸም ቁርጠኛ አቋም ላይ መተማመን በመፈጠራቸው ጭምር ነው። ያለፉት የሠላም አስከባሪ አኩሪ ገድሎችን ስንቁ አድርጎ የያዘው ሠራዊታችን በአብዬ ግዛት ባካናወናቸው ሠላምን የማጠናከር ተግባራት በግጭት የወደሙ መንደሮችን መልሶ በማቋቋም ህዝቡ የሠላም አየር እንዲተነፍስና የተረጋጋ ማህበራዊ ህይወት እንዲኖረው ማስቻሉ የሁለቱን ወገኖች ልብ አሸንፏል።

ሠራዊታችን በተሰማራባቸው የሠላም ማስከበር ሀገሮች በሙሉ በተለመደው ህዝባዊ ባህሪው፣ ከኪሱ ገንዘብ አዋጥቶ የተቸገሩ፣ የተራቡና የታረዙ ወገኖችን ደግፏል። የህክምና አገልግሎት በመስጠትና ተፈናቃዮችን ከቦታ ቦታ በማጓጓዝ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ ጥበቃና ከለላ በመስጠትም የራሱን ድርሻ አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል። በጦርነቱ ወቅት የወደሙ መሠረተ-ልማት ተቋማትን መልሶ በመገንባት በእርግጥም ህዝባዊ ሠራዊት መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፤ ሠራዊታችን ባሳያቸው መሰል ህዝባዊ ባህሪያት የሀገራችን ሠላም ማስከበር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጠናከርና የተቀባይነት ደረጃም እያደገ እንዲሄድ አስችሎታል።

የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ከባድ ሚሽን ተብለው በተለዩ ተልዕኮዎቹ ላይ ማለትም ምንም ዓይነት መሠረተ-ልማት በሌለባቸው አስቸጋሪ የአየር ጸባይ ባላቸው አካባቢዎች ላይ በአነስተኛ የሰው ኃይል ሰፊ ቀጣና እንዲረከብ የሚደረገው ተልዕኮ በብቃት የመወጣት ልምድ በማካበቱ መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።

ለአብነት ያህልም በአፍሪካ ህብረት ሥር (አሚሶም) ከተሰማራው የአፍሪካ ሀገራት ሠላም አስከባሪ ኃይል መካከል የተልዕኮውን 62 በመቶ የሚሆነው የቆዳ ስፋት በኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ እንዲሸፈን መደረጉ አስቸጋሪ ተልዕኮዎችን በብቃት ለመወጣቱ ጥሩ ማሳያ ይሆናል።

የሠራዊታችን የሠላም ማስከበር ተልዕኮ አፈጻጸም ብቃቱ ከሁሉም ሀገራት በላይ ተመራጭ እንዲሆነ ስላስቻለው በአሁኑ  ወቅት ከ11ሺህ 500 በላይ የሠላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት በዓለም ቀዳሚውን ደረጃ ስትይዝ፤ ከዚህ አሃዝ ውስጥ 865 ያህል ሴቶች ናቸው። ይህም ሀገራችን ኢትዮጵያ በሴቶች ተሳትፎ በዓለም ቀዳሚውን ደረጃ እንድትይዝ ያስችላታል። እነዚህ አሃዞች ተደማምረው ሀገራችን እስካሁን ለዓለም ሠላም መስፈን ያሰማራቸውን የሠላም አስከባሪ ሠራዊቷን ቁጥር ከ110 ሺህ በላይ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቀማሉ።

ይህን የሠላም ማስከበር ተልዕኳችን ይበልጥ ለማጠናከር ሰፋፊ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ከዚህ በፊት የኮንተንጀት የሠላም አስከባሪ አሃድ በየዕዙ ማሠልጠኛ ወጥነት በሌለውና በተበታተነ ሁኔታ ይሰጥ ነበር።ከታህሣሥ 2009 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋመውና ስድስት ዙር አሰልጥኖ ያስመረቀው ይህ የኮንቲንጅት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሥልጠናው 80 በመቶው ግዳጅ ላይ ያተኮረ እንዲሁም 20 በመቶ መሠረታዊ የውትድርና ታክቲክ ሥልጠናዎች እንደሆነ መደረጉ ዓለም-አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ እንዲጠናከር እያደረገው ይገኛል።

በስታፍ መኮንንና በወታደራዊ ታዛቢነት ለሚሰማሩ የሠራዊቱ አባላት ሁለንተናዊ አቅም ይበልጥ ለማሳደግ ይረዳ ዘንድ ከሰኔ ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም-አቀፍ የሠላም ማስከበር ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አቋቁሞ ሥልጠናውን እየሰጠ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በተሰማራባቸው ተልዕኮዎች ሁሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአስተናጋጅ ሀገራት ህዝቦችና በዓለም ማህበረሰብ ከፍተኛ አመኔታና ክብር ዝና ከማግኘቷም በተጨማሪም የተፈላጊነት ደረጃዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።

ስለሆነም የኢትዮጵያ ሠራዊት በዓለም የሠላም ማስከበር ተልዕኮውን በስኬት፣ በዲስፕሊንና በታማኝነት በመፈጸም በዓለም ደረጃ የዓለም አምባሳደር ሽልማትና ሙገሳ ከማግኘቱም በላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትም በአፍሪካ ህብረትና በተመድ የቀረበለትን የሠላም ማስከበር ጥያቄዎች ተቀብሎ በብቃትና በመልካም አርአያነት በመወጣት ላይ በመገኘቱ የሠላም ተሸላሚ ሆኗል። ይህ ክብርና ምስጋና ለመላው ዓለም ህዝቦች ሠላም ክብር ህይወታቸውን ላጡ ሰማዕታት ይሁን መልካም የሠራዊት ቀን ይሁንልን፤ ሠላምና ድል ለሠራዊታችን።