ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦቶዋ ለአሸናፊነት ይጠበቃሉ

የካናዳዋ ኦቶዋ በምታዘጋጀው ዓመታዊ የማራቶን ውድድር እንደ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች የነገሰ የለም። ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ሰባት መድረኮች ውድድሩን በበላይነት ማጠናቀቃቸው ነገ በሚካሄደው ፉክክር ቅድመ ግምቱን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ ባለው በዚህ ውድድር፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተጽዕኖ አሳዳሪ በመሆናቸው የውድድሩ ተመልካቾች የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለቡና በአንድ ድምጽ «ኢትዮጵያ» እያሉ ድጋፍ መስጠታቸው የተለመደ ትዕይንት መሆኑንም በድረገጹ አስነብቧል።

በሴቶች ውድድር የቦታው ክብረ ወሰን የተያዘው በአትሌት ትዕግስት ቱፋ ሲሆን፤ ይኸውም በ2014 የገባችበት ያስመዘገበችው 2:24:31 ነው። ከቀናት በፊት በተካሄደው የለንደን ማራቶን ስምንተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አትሌቷ በዚህ ውድድርም የምትሳተፍ ይሆናል። ስለ 2014ቱ ውድድር የተጠየቀችው አትሌቷ «አሸናፊ በመሆኔ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የማራቶን ውድድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ታሳትፌ ያሸነፍኩ መሆኑ ደግሞ ደስታዬን እጥፍ ያደርገዋል። ሁልጊዜ የማስታውሰው ድልም ነው» የሚል ምላሽ ሰጥታለች።

አትሌት ኮረን ጃለላ ከዚህ ቀደም በኦቶዋ ማሸነፍ የቻለች አትሌት ስትሆን፤ የትዕግስት ተፎካካሪ እንደምትሆንም ይጠበቃል። አትሌቷ ስለ ውድድሩ በሰጠችው አስተያየትም«ካናዳ ብዙ የሚወደድ ነገር ቢኖራትም የኦቶዋ ውበትና ነዋሪዎች ግን የተለዩ ናቸው። ባለፈው ዓመት የነበረው የአየር ሁኔታ ንፋሳማና ደመናማ በመሆኑ ውድድሩ ከባድ ነበር፤ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ከ1እስከ3 ያለውን ደረጃ በሴቶች በመያዝ ነበር ያጠናቀቅነው። በቦታው የነበረው ድጋፍም እጅግ የሚያስደስት ነበር፤ በተለይ በኢትዮጵያውያኑ ይደረግልን የነበረው ድጋፍ ውጤታማ አድርጎናል» ብላለች።

አትሌቷ ከ6 ዓመታት በፊት በተካሄደው የቶሮንቶ ማራቶን 2:22:43 የሆነ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ነበር ያጠናቀቀችው። በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊ ሆና ለማጠናቀቅም፤ ከባህር ጠለል በላይ ከ2500 ሜትር እስከ 2800 ሜትር በሆነ ሥፍራ በሳምንት 180 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን ገልጻለች። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ሌሎቹ አትሌቶችም በተመሳሳይ በቦታው ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንካራ ልምምድ ማድረጋቸውን ጠቁማለች። አትሌቷ እ.አ.አ 2015 የአገሯን ልጅ አትሌት አበሩ መርጊያን ሦስት ደቂቃዎችን በማሻሻል አሸንፋታለች። አበሩ ነገ በውድድሩ ላይ የምትሳተፍ መሆኑ በሁለቱ አትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

በወንዶች በሚካሄደው ውድድርም ኢትዮጵ ያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ፡፡ አትሌት ሰቦቃ ቶላ የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው መካከል ቀዳሚው ነው። አትሌቱ ከወራት በፊት በተካሄደው የቶሮንቶ ማራቶን ሁለተኛ በመሆን አጠናቋል። ሰቦቃ በ2012ቱ የዱባይ ማራቶን ያስመዘገበው 2:06:17 የግሉ ምርጥ ሰዓት ነው። እ.አ.አ በ2014 በአትሌት ጸጋዬ የማነ የተመዘገበው 2:06:54 ሰዓት የቦታው ክብረወሰን ቢሆንም፤ ሰቦቃ ባለው ምርጥ ሰዓት ታግዞ በቦታው አዲስ ክብረወሰን ሊመዘገብ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሏል።

ሰቦቃ ለአሸናፊነት ይጠበቅ እንጂ ተቀራራቢ ሰዓት ካለው የአገሩ ልጅ ሲሳይ ጂሳ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚገጥመው ቀድሞ ተገምቷል። «ሹሩቤ» በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው ሲሳይ በዚህ ዓመት በተካሄደው የዱባይ ማራቶን 2:08:09 በሆነ ሰዓት ነበር ያጠናቀቀው። 2:06:27 የሆነ ምርጥ ሰዓት ያለው አትሌቱ በኦቶዋ ማራቶን ሲወዳደር ይህ የመጀመሪያው ነው። አዱኛ ታከለም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2013 በተሳተፈበት የኦቶዋ ማራቶን ሁለተኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው። አትሌቱ በቦታው ልምድ ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ በ2014ቱ የፍራንክ ፈርት ማራቶን አሸናፊ የሆነበት ምርጥ ሰዓቱ 2:08:31 ለነገው ውድድር አሸናፊ ሊያደርገው ይችላል የሚል ቅድመ ግምት አስገኝቶለታል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!