የክቡር ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መልዕክት!

 

 

እንኳን ለሰባተኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በሰላም አደረሳችሁ!

  እንኳን ለሰባተኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በሰላም አደረሳችሁ!

ሰራዊታችን ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ ሊያሳይ የሚችል አንድ ምሳሌ እንድጠቅስ ፍቀዱልኝ።  በጥንት ጊዜ አንድ የሃገር መሪ፤ አንድን ታዋቂ ወታደራዊ ባለሞያ ሠራዊታቸውን እንዲያደራጅላቸው ጠየቁት፡፡ ያ ወታደራዊ ባለሞያ ከሶስት ቀናት በኋላ አራት ነገሮችን ይዞ ወደ መሪው መጣ፡፡ አንበሳ፣ ንስር፣ ላምና ጉንዳን፡፡ መሪውን አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡ ™ከእነዚህ ከአራቱ ማንን የሚመስል ሠራዊት ላደራጅልዎ?∫ አለ። መሪው ጥቂት አሰቡና ™አራቱንም የሚመስል∫ አሉት፡፡

አንድ የመከላከያ ሠራዊት ሃገር በሰላም ሠርቶና ተኝቶ እንዲኖር የአንበሳ፣ የንስር፣ የላምና የጉንዳን ባህሪ ያለው እንዲሆን ይጠበቅበታል፡፡ ዊኒስተን ቸርችል ™ሌሊት በሰላም ተኝተን የምናነጋው እኛን ሊጎዱ የሚመጡትን ሁሉ ለመቋቋም ዘወትር ዝግጁ የሆኑ የሰራዊት አባላት ስላሉን ነው∫ እንዳሉት፡፡

አንድ የመከላከያ ሰራዊት እንደ አንበሳ የማይበገርና ጀግና መሆን አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ ወታደር መቼም ስለጀግንነት አይነገርም፡፡ ጀግንነት ጀብደኝነት አይደለም፡፡ ለምን? ማንን? እንዴት? እንደሚዋጉ ከማወቅና ከማመን የሚመጣ ቆራጥነት ነው ጀግንነት የሚባለው፡፡ ዓላማን ከማወቅና በዓላማ ከማመን የሚመጣ ጀግንነት በአነስተኛ መስዋዕትነትና ኪሣራ ድል ለማስመዝገብ የሚያስችለውን ጥበብ ነው ጀግንነት የምንለው፡፡ የአንበሳ ጀግንነት ጥበባዊ ጀግንነት ነው፡፡ አንበሳ ወደ ዋሻው ሲሄድ አዳኞች እንዳይደርሱበት በጅራቱ ዱካውን ያጠፋዋል ይባላል፡፡ ጥበባዊ ጀግንነት ይሄ ነው፡፡ ™የሚሞትለት ምክንያት የሌለው ሰው የሚኖርበትም ምክንያት የለውም∫ እንዳለው ማርቲን ሉተር ኪንግ፤ ጥበባዊ ጀግንነት - በምክንያት መኖርና ለምክንያት መሞት ነው፡፡

ንስር ከአዕዋፍ ሁሉ እጅግ የላቀ እና የመጠቀ ነው፡፡ ሰራዊታችን እንደንስር ነው ስንል በእውቀት፣ በክህሎት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በስልጠና ከሚፈለገው ደረጃ በላይ የላቀ ነው ማለታችን ነው፡፡ ሃገራችንን፣ ህዝባችንንና ጥቅሞቻችንን ሁሉ በሚፈለገው ልክ ለማስጠበቅ የሚችል ሰራዊት እንዲኖረን ልህቀት አንዱ መለያችን መሆን አለበት፡፡ ሃገራችንን ከውስጥም ይሁን ከውጭ ለመድፈር የሚያስቡት ቀድመው ተስፋ ቆርጠው እንዲተውት፤ የሚሞክሩትም ክንዱን ቀምሰው ዳግም እንዳይመኙት ለማድረግ የሚቻለው ከፈተናዎቹ በላይ መጥቆ ከተገኘ ነው፡፡

በወታደራዊ ሳይንስና ዲስኘሊን የታነፀ፤ ከፍተኛ ህዝባዊ ወገንተኝነት የተላበሰ፤ በአወቃቀሩ የሁሉም የሃገራችን ህዝቦች አሻራ ያረፈበት፤ ህገ-መንግስቱንና የሃገር ሉዓላዊነት በመጠበቅ ረገድ ሙሉ እምነት የሚጣልበት ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ለመፍጠር ስንተጋ የቆየነው ይህንን ልህቀት ለማምጣት ነው፡፡ የመከላከያ ኃይላችን በእውቀት፣ በመሣሪያ፣ በክህሎት፣ በአደረጃጀት፣ በዘመናዊነት፣ በንቃትና በብቃት የላቀ፤ ከሚገጥሙት ችግሮች በላይ የመጠቀ ከሆነ ችግሮቹን እንደንስር ከላይ ወደታች እንጂ ከታች ወደ ላይ አያያቸውም፡፡

በዓለማችን ዛሬ ለሲቪሉ ህዝብ ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተፈጠሩትና የመጀመሪያ አገልግሎት የሰጡት በመከላከያ ዘንድ ነው፡፡ ውትድርና ውጊያ ብቻ ሳይሆን ጥናት፣ ምርምር፣ ፈጠራና መራቀቅም ጭምር ነው፡፡ መከላከያ በጥናትና ምርምሩ፣ በፈጠራውና በልህቀቱ ራሱን ከማዘመኑና ከማራቀቁም በላይ የሲቪሉን ህይወት ያዘምነዋል፡፡

ይህ ሁሉ ቢሆንም እንኳን የላሟን ባህሪ የያዘ ሠራዊት ከሌለን ትልቁን እሴት እናጣዋለን፡፡ ህዝባዊነቱን፣ የህዝብ አገልጋይነቱን፣ በቁሟ በወተቷ፣ በሞቷ በስጋዋና በቁርበቷ እንደምታገለግለው ላም፤ የመከላከያ ሠራዊታችንም በህይወቱም በመስዋዕትነቱም ሃገሩን የሚያገለግል አለኝታችን ነው፡፡ በህይወት እያለ ይጠብቃታል፤ ያስከብራታል፣ በችግሯ ሁሉ ቀድሞ ይደርስላታል፤ በጥናቱና በምርምሩ ያዘምናታል፡፡ ሲሰዋም መስዋዕትነቱ ክብርና ሞገስ ይሆናታል፡፡ አጥንቱ አጥር ቅጥር ሆኖ ያስከብራታል፡፡

መቼም ጉንዳን በዲስኘሊኑ የታወቀ ነው፡፡ ለአንድ ዓላማ በጋራ መሰለፍ፤ በጋራ መፈፀም፤ ትግሉንም ድሉንም የጋራ ማድረግ፤ እጅግ በተደራጀ፣ የዕዝ ሰንሰለትን ባከበረና እንደብረት በጠነከረ ዲስኘሊን መመራት የጉንዳኖች ባህሪ ነው፡፡ ጉንዳን የተሰዋ ወገኑን እንኳን ትቶ አይሄድም፡፡ ከተሰጠው ተዕልኮ ወደ ግራም ወደ ቀኝም አይልም፡፡ ዲስኘሊን ለአንድ ሠራዊት ወሳኝ ነው፡፡ ለህገ-መንግስት መታመን፣ ለህዝብ መወገን፣ ለስርዓት መገዛት፣ ቃለ-መሃላ ማክበርና ራስን ሁል ጊዜ ለግዳጅ ማብቃት ከህዝብ ለህዝብ የቆመ ሠራዊት መለያዎቹ ናቸው፡፡

የመከላከያ መሪዎች በሁሉም ረገድ ተልዕኳቸውን የተረዱ፤ ኃላፊነታቸው ለመላው ህዝባቸው መሆኑን የተገነዘቡ፤ ከሙስና፣ ከዘረኝነትና ከግላዊ ጥቅም የራቁ፤ ለሠራዊቱ ሁለገብ አርዓያዎች የሆኑ፤ በእውቀት፣ በክህሎት፣ በብቃት፣ በጀግንነትና በዲስኘሊን የላቁ ከሆኑ ጠንካራ ዲስኘሊን ያለው ሠራዊት ማፍራታችን የማይቀር ነው፡፡ ከጉንዳን የምንማረው አንዱ ዲስኘሊን የመሪነት ዲስኘሊን ነው፡፡ ታላቁ እስክንድር ™በበግ ከሚመራ የአንበሳ መንጋ ይልቅ በአንበሳ የሚመራ የበጐች መንጋ ያስፈራኛል∫ ሲል የተናገረው የወታደራዊ መሪነትን ዲስኘሊን ነው፡፡

የመከላከያ ሠራዊታችን እነዚህን አራቱን ባህሪያት ለመላበስ እራሱን ሲያደራጅ፣ ሲያሰለጥን፣ ሲያዘምንና ሲገመግም ነው የከረመው፡፡ በሃገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙ አደጋዎች እጅግ ውስብስብና ተለዋዋጭ እየሆኑ በመምጣታቸው፤ ተቋሙ እነዚህን አደጋዎች ለመመከት በሚያስችለው መጠን ራሱን ማደራጀትና ማዘጋጀት እንደሚኖርበት ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡

ይህን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችሉ በአደረጃጀት፣ በጦር መሣሪያና በቴክኖሎጂ አቅም እንዲሁም በሰው ኃይልና በወታደራዊ አመራር ላይ ያተኮሩ ተከታታይ ለውጦችን ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ ሠራዊታችን አራቱን ባህሪያት ተላብሶ በባህር፣ በአየር፣ በምድር፣ በሳይበርና በጠፈር የሚመጡ አዳዲስና የመጠቁ ስጋቶችን በጊዜ ለመለየትና ጥቃቶችንም በአስተማማኝ ደረጃ ለመመከት እንዲችል፤ የተጀመረው የሠራዊት ሪፎርም የምንፈልግበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ እንገፋበታለን፡፡

ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትና ከጠባብ ዘረኝነት የራቀ፤ ዘመናዊና ኘሮፌሽናል የመከላከያ ኃይል የመገንባት ውጥናችንን ዳር እንደምናደርሰው ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡

የመከላከያ ኃይላችን በህገ-መንግሰታችን የተጣለበትን ኃላፊነት እንደአንበሳ በጥበባዊ ጀግንነት፤ እንደንስር በሞያዊ ልህቀት፤ እንደላም በህዝባዊ አገልጋይነት፤ እንደጉንዳንም በጠነከረ ዲስኘሊን እንዲወጣ በድጋሚ አደራ እላለሁ፡፡ መንግስት በህዝቦቿ የጋራ ክብርና እውነተኛ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተች አዲሲቷን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት ለሚወስዳቸው ተከታታይ የለውጥ እርምጃዎች  አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ የመከላከያ ሠራዊቱ የራሱን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ለማሳሰብም እወዳለሁ፡፡

™ስለእርሷ የሞቱላትን የምትዘነጋ ሃገር እርሷ ራሷ ትዘነጋለች∫ እንደተባለው፤ ለእኛ ስትሉ ውድ ሕይወታችሁንና አካላችሁን የሰዋችሁትን ሁሉ በክብር ዘወትር እናስባችኋለን፡፡

 

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ !