ሰራዊት ለምን ይደራጃል?

 

ሰራዊት ጦርነትን ለማካሄድ ተብሎ የሚገነባ የታጠቁ ሰዎች ሰብስብ ወይም የተደራጀ ሃይል ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይህ ጦርነትን ለማካሄድ በሚል ዓላማ የተገነባ የታጠቁ ሰዎች ስብስብ፤ በወቅቱ ህብረተሰቡ ወይም መንግስት ሊያቀርብለት የሚችል፤ የጦር መሣሪያዎችን ታጥቆ የተደራጀና በአጠቃላይ መንግስት አስታጥቆና አሰልጥኖ ከወቅቱ ሁኔታ አኳያ ሊያዝ የሚችል ዕውቀትና ችሎታንም አስይዞ ለጦርነት የተዘጋጀ ተቋም እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ሠራዊት የታጠቀና የተደራጀ ወታደራዊ ኃይል በመሆኑ፤ ከመንግስት አካላት እንደ አንዱ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን ጦርነትን ለማካሄድ የምንጠቀምበት ትልቁ መሣሪያና የጦርነት ተግባር ዋነኛ ተሸካሚ ሃይልም ጭምር ነው፡፡

በዚህም መሰረት የተደራጀ ሠራዊት ሁለት መሠረታዊ ተልዕኮዎችን መፈፀም ይጠበቅበታል፡፡ አንደኛ በአገር ውስጥ የሚከሰቱ የውስጥ ጠላቶችን ከመንግስት በሚሰጠው መመሪያ መሰረት የውስጥ ደህንነት ይከላከላል፤ ይጠብቃል፡፡ ሁለተኛ የፖለቲካ ስልጣን የጨበጠውን መደብ ዓላማ ለማሳካት ሲባል ከአገር ውጪ የሚካሄድ ወረራን ያካሄዳል፤ ወይም ደግሞ ከሌላ የሚመጣ ወረራን ይከላከላል፡፡ እነዚህ ሁለት ተልዕኮዎች ሰራዊት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያሉ መሰረታዊ ተልዕኮዎች ናቸው፡፡

የአንድ አገር ሠራዊት ባህሪይ የሚወሰነው በስርዓቱ ባህሪያት ነው፡፡ በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ የሚገነባው ሠራዊት የህዝቦችን የስልጣን ሉዓላዊ ባለቤትነት መብት ወደጎን በመተው፤ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ፖለቲካዊ ስልጣን እንዲጠብቅና ዓላማውን እንዲያሳካ ተደርጎ ይገነባል፡፡ በዚህ ምክንያት ሠራዊቱ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመጨፍለቅ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ብቻ እንዲጠብቅና እንዲከላከል ተደርጎ ይቀረፃል፡፡ ስለሆነም በዚህ ስርዓት ውስጥ ያለ ሰራዊት ህዝባዊ ድጋፍ የሌለውና ህዝባዊ ባህሪ ያልተላበሰ ፍፁም ፀረ-ህዝብና አምባገነን ይሆናል፡፡

በዴሞክራሲ ስርዓት የሚገነባ ሰራዊት ዴሞክራሲያዊ ባህሪያትን የተላበሰ፤ የህዝብን ሉዓላዊነት አምኖ የተቀበለ፤ ህዝቦች ለወሰኗቸውና ላፀደቋቸው ህጎች ተገዢ የሆነ ሃይል መሆን ይኖርበታል፡፡ ማንኛውንም ተልዕኮ ሲፈፅም ከህዝብና ከመንግስት ጥቅም አንፃር እየተመለከተ በሚሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ ተልዕኮውን በብቃት የሚፈፅም ሰራዊት ይሆናል፡፡ ስለሆነም ሠራዊቱ ሁሌም ህዝባዊ ድጋፍ የማይለየው፤ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅና ትልቅ እምነት የሚጣልበት ኃይል ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ከዚህ አኳያ የኢፌዴሪ መከለከያ ሠራዊትን ስንመለከት በዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ የተገነባ፤ ግልፅ መርሆዎች ያሉት፤ ተነጥረው የተቀመጡ ተልዕኮዎች የተሰጡትና የጀግንነቱና የህዝባዊነቱ ምክንያት የሆኑት ተቋማዊ እሴቶች የተላበሰ ሰራዊት ስለመሆኑ ወደኋላ ላይ ተዘርዝሮ ተቀምጧል፡፡

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!