በኢትዮጵያ የሰራዊት አመሠራረትና ታሪካዊ አመጣጥ

 

ጦርነት ፍላጎትን በሃይል ማረጋገጫ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሰው ልጅ ታሪክ አንድ መሰረታዊ ክስተት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለወደፊት የሚኖር፤ የፖለቲካ ዓላማን ለየት ባለ መልኩ ለማሳካት የሚከናወን እንቅስቃሴም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክም ከጦርነት ታሪክ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ የነበሩ ንጉሳዊም ሆነ አምባገነናዊ ስርዓቶች ይብዛም ይነስም የፖለቲካ ዓላማቸውን የሚያስፈፅሙበት ሰራዊት ነበራቸው፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የነበረው ሠራዊት የተደራጀበት ዓላማ፣ መርሆዎችና የነበራቸውን ባህሪያት በግልፅ ለማወቅ የሚያስችሉ የተሰነዱ የታሪክ ማስረጃዎች ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሠራዊት የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው መሆኑ የሚካድ አይደለም።

ከዚህ አኳያ በፅሁፍ የተደራጀና የዳበረ የታሪክ መዛግብት በተሟላ ሁኔታ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ፤ የሰራዊቱ የረዥም ጊዜ ታሪክ አፈ-ታሪክ እንዲበዛበት ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለሆነም የሃገራችንን ሰራዊት ቅድመ ታሪክ፣ ምንነትና እድገት በተጣራና በተጨባጭ መረጃ አስደግፎ ለማመላከት አዳጋች እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ይሁንና በግርድፉም ቢሆን በዚህ ፅሁፍ በኢትዮጵያ ከነበሩ ከአፄቴዎድሮስ ንጉሳዊ አገዛዝ ጀምሮ በአፄ ዮሃንስበአፄ ሚኒሊክበአፄ ሃይለስላሴና በደርግ ስርዓት የሠራዊት አመሰራረትና ታሪካዊ አመጣጥ ባጭሩ የምንዳስስ ይሆናል፡፡ በተለይም ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አመሰራረት፣ ዓላማ፣ መርሆዎችና አደረጃጀት ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡

በ19ኛው ክፍለዘመን በአፄቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት አንድ ማዕከላዊ መንግስት ለመመስረት ጠንከር ያሉ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በዚህ ወቅት ታላላቅ የእርስ በርስ ጦርነቶች እንደነበሩም ታሪክ ያወሳል፡፡ ነገር ግን በዓላማና በመርህ ላይ ተመስርቶ የተደራጀ ሰራዊት ስላልነበራቸው አንዳቸውም ቢሆን የበላይነትን መቆጣጠር አልቻሉም ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መደበኛ ሰራዊት የመፍጠር ሙከራ እንደተጀመረም ይነገራል፡፡

ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነመንግስት ጀምሮ ሠራዊቱ በሶስት ዘርፎች ማለትም በአደረጃጀት፣ በጦር መሳሪያና በስነስርዓት አከባበር ለውጥ የማምጣት ጉዞ ጀመረ፡፡ በአደረጃጀት ረገድ በግዛቱ የመሳፍንት የነበረውን ጦር በብሔራዊ ጦሩ የማካተት፤ የወታደራዊ የማዕረግ እርከኖችን ስያሜ መስጠትና የጦር መሪዎችን መሾም የመሳሰሉ ስራዎች እንደተሰሩ ይነገራል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ግንባታ (መድፍ)፤ ወታደራዊ ስነስርዓትን ለማስፈን ቅጣት እንደተጀመረና ሰራዊቱ ቋሚ የደመወዝ ተከፋይ እንዲሆን የማድረግ ጅምሮች እንደነበሩ ታሪክ ያስረዳል፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የሰራዊት አመሰራረት ጅምርና ሂደቶች በአፄቴዎድሮስ ጊዜ የተከናወኑ ስለሆነ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ታሪክ ከዚህ እንደተጀመረ ይታመናል፡፡

ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበረው ሰራዊት የተደራጀበት ዓላማ ለአፄውና ለዙፋናቸው ታማኝ ሆኖ ማገልገልና የግዛታቸውን አንድነት ዳር ድንበር ከማስከበር በዘለለ ህዝባዊ መሠረት እንዳልነበረው እሙን ነው፡፡ ስለሆነም በዘመኑ የነበረው ነፍጥ ያነገበ የንጉሱ ሠራዊት በሄደበት ሁሉ በህዝቡና በገበሬው ላይ የፈለገውን የማድረግ ሙሉ መብት እንደነበረው የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡

ከአፄ ቴዎድሮስ ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የሆኑት አፄ ዮሃንስ የተጀመረውን የማዕከላዊ መንግስት ምስረታ ተግባራዊ ለማድርግ ራዕይ ነበራቸው፡፡ በመሆኑም አፄ ዮሃንስ ገና ዙፋን ላይ ከመውጣታቸው ጀምሮ የስልጣን ዘመናቸውን ያሳለፉት ከውጭ ሃይሎች በተለይም የግብፅን የመስፋፋት ፍላጎትና የኢጣሊያን የቅኝ ግዛት ወረራ በማክሸፍ ተጠምደው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡

ንጉሱ የጠላትን የመስፋፋት ፍላጎትና የቅኝ ግዛት ወረራ ለመግታት የዲፕሎማሲና የውግያ ስልት ምን መሆን እንዳለበት በአቅጣጫ በማስቀመጥ የተደራጀና ዘመናዊ ጦር ለመገንባት ትልቅ ሙከራ አድርገዋል፡፡ በዚህ መሰረት የውጊያ ብቃት፤ የዘመናዊ ትጥቅ አጠቃቀም፤ ደጀንና ስንቅ እንዴት መተሳሰር እንዳለበት በማስቀመጥ ሰራዊቱን ዘመናዊ ለማድረግ ከተለያዩ ሃገራት ጋር ግንኙነት ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሠራዊቱን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ማስታጠቅና ማሰልጠን ችለዋል፡፡ ስለሆነም አፄ ዮሐንስ ከግብፅ ወራሪ ሃይል ጋር ህዳር 16 ቀን 1875 ዓ.ም ጉንደት ላይ ባደረጉት ጦርነት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በርካታ የጠላት ወታደሮችን በመደምሰስ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ ይህ ሠራዊቱ ጠንከር ያለ አደረጃጀት እንደፈጠረና የወቅቱን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እንደታጠቀ የሚያመላክት ነው፡፡

ከአፄ ዮሐንስ ውድቀት በኋላም ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ በትረ ስልጣኑን በመረከብ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ መመስረት መሠረት የሆነውን ሠራዊት ለመገንባት በስፋት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት አስተዳደራዊ መዋቅሩ በሚኒስቴር ደረጃ እንደተዋቀረ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ከውጭ ሃገራት ጋር የተሻለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማድረጋቸውም ሰራዊቱን በተሻለና በተደራጀ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ማስታጠቅ ችለዋል፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በሃገራችን የሠራዊት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር ሚኒስቴር የሾሙና ሠራዊቱ ወታደራዊ ዩኒፎርም እንዲለብስ ያደረጉ ባለራዕይ መሪ እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል፡፡

 

ዳግማዊ አፄ ምኒሊክን ተከትለው ስልጣን ላይ የወጡት አፄ ሐይለስላሴ የጦር ክፍሉን በአደረጃጀት፣ በትጥቅና በስልጠና ይበልጥ ለማዘመን በርካታ ስራዎችን እንደሰሩ ታሪክ ያስረዳል፡፡ በዚህ መሰረት ሰራዊቱን ምድር ሃይል፣ አየር ሃይልና ባህር ሃይል በሚል በሶስት ክፍሎች እንዲደራጅ አድርገዋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ንጉሱ የሠራዊቱን የአመራር ጥበብና ክህሎት ለማሳደግና ስታፉን (የድጋፍ ሃይሉን) ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ የስልጠና ተቋማትን እንዲመሰረቱም ጭምር በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ከተቋቋሙት የስልጠና ተቋማት ውስጥ የሆለታገነት የጦር ትምህርት ቤት፣ የሐረር ቀዳማዊ ሃይለስላሴ አካዳሚ፣ የአየር ሃይልና የባህር ሃይል፣ የምድር ጦር ማመላለሻ ትምህርት ቤት፣ የቀላል ተሽከርካሪ የጥገና ትምህርት ቤት፣ የምድር ጦር አስተዳደር ድርጅት፣ የሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ተግባረዕድ፣ የመገናኛና የመሃንዲስ ትምህርት ቤቶችና ማስልጠኛዎች ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሰራዊቱ በዚህ መልክ ከተደራጀ በኋላ ከስርዓቱ ባህሪይ የመነጩ የንጉሱን ፍላጎትና ስልጣን የሚያስጠብቁ ተልዕኮዎች የተሰጡት ሲሆን ለመግለፅ ያህል፡- የሃገሩን ዳር ድንበር መጠበቅ (የግዛት አንድነትን ማጠናከር)፤ የንጉሰ ነገስቱን ስልጣንና ዘውድ መጠበቅና የንጉሱን ሕገ-መንግስት ከማንኛውም ጥቃት መከላከል የሚሉ ተልዕኮዎችን አንግቦ የንጉሱ ፍፁም ዘውዳዊ ስርዓት ጠበቃና ዋስትና ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው፡፡

ነገር ግን ፍፁም ዘውዳዊ ስርዓቱና ረዥሙ ንጉሳዊ የስልጣን ቅብብሎሽ ሰንሰለቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ትግል መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ተበጠሰ፡፡ ይሁን እንጂ ደርግ የህዝብ ትግልና እንቅስቃሴ የፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደስልጣን በመውጣት እስከ ግንቦት 2ዐቀን 1983 ዓ.ም ድረስ በትረ ስልጣኑን ለ17 ዓመታት ተቆጣጥሮት ቆይቷል፡፡

ደርግ በንጉሱ የነበረውን አደረጃጀትና የዕዝ ሰንሰለት ለተወሰኑ ዓመታት ካስቀጠለ በኋላ በ1972 ዓ.ም አዲስ የጦር ሃይሎች የዕዝ ተዋረድና ወታደራዊ ዶክትሪን አወጣ፡፡ በዚህም መሠረት ሠራዊቱ በሶስት ታላላቅ ተቋሞች ማለትም ከኢሰፓ አኮና ኋላም ከኢሰፓ፣ ከመከላከያ ፕሮፌሽናል አዛዦችና ከወታደራዊ ደህንነት ድርጅት የተዋቀረ የወታደራዊ አመራር እንዲኖረው አደረገ፡፡ ይህ የአመራርና የእዝ ስርዓት መዋቅር በእያንዳንዱ የጦር ክፍሎች ውስጥ እንዲተገበር በመደረጉ ደርግ ከስልጣን እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ ይህን የአመራርና የዕዝ ስርዓት አጠናክሮ በማስቀጠል በጦር ክፍሉ ውስጥ እርስ በእርሱ የሚጠራጠርና መተማመን ያልነበረበት እንዲሆን በማድረግ አምባገነናዊ ስርዓቱን ለማቆየት ከፍትኛ ትግል አድርጓል፡፡

ይህ ፅሁፍ የተዘጋጀው በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የተደራጀ ሰራዊት ካቋቋመችበት ከአፄዎቹ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ታሪክን ለማውሳት ሳይሆን፤ እነዚህ ሰራዊቶች በመሰረቱ አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ወይም ባህሪይ መኖሩን ማመላከትና አሁን ያለው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ባህሪይ በይዘቱና በቅርፁ ከነሱ ፍፁም የተለየ መሆኑን ለማየት ያመች ዘንድ ነው፡፡