ኢትዮጵያ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን ክብር ማስጠበቅ እንደሚገባ ተገለፀ

ተመራቂ የሠላም አስከባሪ የሠራዊት አባላት ተልዕኳቸውን በውጤታማነት በመፈጸም ሀገራችን በተልዕኮው በመሳተፍ ያገኘችውን ክብር ማስጠበቅ እንደሚገባቸው በመከላከያ የሠላም ማስከበር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌ/ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

ኃላፊው ይህን የገለጹት በሠላም ማሰከበር ዋና መምሪያ የኮንቲንጀንት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በ3ኛው ዙር 4 ሻለቆችን ሁርሶ በሚገኘው የትምህርት ቤቱ ማሠልጠኛ ግቢ ባስመረቀበት ወቅት ሰርተፊኬት ከሰጡ በኋላ ባሰሙት የመመሪያ ንግግር ነው።

ኢትዮጵያ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን ተቀባይነት ለማስቀጠል በዓይነትና በጥራት፣ እንዲሁም በብዛት ሥልጠና በመስጠት ለተልዕኮው ብቁ የሚያደርግ ውጤታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሌ/ጄኔራል ብርሃኑ ያላትን ተሰሚነትና ያገኘችውን ክብር ለማስቀጠል ከምልምላ ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ በማቀድና ተልዕኮ ተኮር ሥልጠና በመስጠት  አመርቂ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የቅድመ ስምሪት የኮንቲንጀንት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ይርዳው ገ/መድህን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የ3ኛ ዙር ሠልጣኞች የካሪኩለም ክለሳ ተደርጎ ለተልዕኮው ብቁ የሚያደርጓቸው የቀንና የሌሊት ሥልጠናዎች እንዲከታተሉ ተደርጓል።

በ3ኛ ዙር 4 ሻለቆች ሰልጥነው ለምረቃ የበቁ መሆናችን የገለጹት የትምህርት ቤቱ አዛዥ፣ 147 የሰው ኃይል በተለያዩ ሙያዎች የአጭር ጊዜ ሥልጠና መውሰዳቸውን እንዲሁም የአሰልጣኞችን አቅም ለማሳደግ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር እንዲሰለጥኑ ተደርጓል ብለዋል።

በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ግዳጃቸውን አጠናቀው የተመለሱ 2 ሻለቆች የግዳጅ አፈጻጸማቸውን ሂደት በመገምገም ለተሞክሮ ልውውጥ፣ ለሥልጠና ጥራት ሂደት  በግብዓትነት መጠቀም መቻሉን ኮሎኔል ገ/መድህን ጨምረው ገልፀዋል።

እንደ ኮሎኔል ገ/መድህን ገለፃ የኮንቲንጀንት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቱ ባለፉት ሁለት ዙሮች ለ5 ሞተራይዝድ ሻለቆች ለአንድ ሲግናል ስታፍ ሻምበል ዩኒትና ለሁለት ሴክተር ስታፍ ሻምበል ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ተልዕኮ አሰማርቷል። በማለት ኮሎኔል ገ/መድህን ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመስተዳድር አካላት፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!