አካዳሚው እጩ መኮንኖችን አስመረቀ

 

  የሜጄር ጄኔራል ሓየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ በዲግሪና ዲፕሎማ የትምህርት መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ዕጩ መኮንኖች በም/መ/አለቃ ማዕረግ አስመረቀ።

ሰሞኑን ሆለታ በሚገኘው የአካዳሚው ቅጥር ግቢ እጩ መኮንኖቹን ባስመረቀበት ወቅት በኢፌዴሪ መከላከያ የትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ሰዓረ መኮንን በክብር እንግድነት ተገኝተው ብልጫ ላመጡ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ የመመሪያ ንግግር አድገዋል።

ጄኔራል መኮንኑ  በንግግራቸው፤ የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል የመከላከያ ሠራዊታችን በላቀ ብቃት ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል። “ለዚህም እንደ ሜጄር ጄኔራል ሓየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ያሉ አቅም ፈጣሪ ተቋሞቻችን ሚና ከፍተኛ ነው” ብለዋል።

“የዕለቱ ተመራቂዎች የመጀመሪያዋን ሴት ታጋይ ማርታ ስያሜ በመያዝ ተልዕኳችሁን በብቃት ለመፈጸም የሚያስችል ክህሎት፣ ችሎታ፣ አስተሳሰብና ባህሪይ ተላብሳችሁ ለምረቃ እንደበቃችሁ ሁሉ በምትሰማሩበት አሃድ ዕውቀታችሁን በቀጣይነት በማጎልበት በንድፈ ሓሳብና በተግባር የቀሰማችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር እንዲሁም የተቋሙን  እሴቶችን ተላብሳችሁ አርአያ መሆን  እንደሚጠበቅባቸው”  ሌተና ጄኔራል ሰዓረ አሳስበዋል።

የሜጄር ጄኔራል ሓየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ዋና አዛዥ ተወካይ ኮሎኔል ሰለሞን ተስፋይ በበኩላቸው፤ አካዳሚው የተቋሙን ትምህርትና ስልጠና ፍላጎት ለማሳካትና የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት በዳሰሳ ጥናት በመገንዘብ ከውስጥ የተገኙ ግብዓቶችንም መነሻ በማድረግ የመደበኛና አጭር ኮርስ ዕጩ መኮንን የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተሻሻለው ስርዓተ ትምህርት መሰረት የመደበኛ ፕሮግራሙን በዲግሪ መርሃ ግብር ለመስጠትና በአጭር ኮርስ ተመራቂዎች ላይ የሚታየውን የአቅም ውስንነት ለማስቀረት የቆይታ ጊዜ ማሻሻያ ማድረጉን ያወሱት ኮሎኔል ሰለሞን፤ እጩ መኮንኖችን በብቃት ከማፍራት በተጨማሪ የእግረኛ ሻምበል አመራር በአጭር ኮርስ ለማሰልጠን ተልዕኮ ተቀብሎ ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ ስራው በያዝነው በጀት ዓመት ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አክለው አመልክተዋል።

ለምረቃ የበቁ አባላት መስፈርቱን አሟልተው የሚሰጠውን ፈተና አልፈው ወደ አካዳሚው መግባታቸውን፣ እንዲሁም በቆይታቸው የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች በሚገባ ሸፍነው የመመረቂያ መስፈርቱን በተገቢው አሳክተው መሆኑን ያወሱት የአዛዡ ተወካይ የንድፈ ሓሳብ፣የመስክ ልምምድ ባለፈ ሠራዊቱ በሚገኝበት ግንባር ድረስ በመሄድ የተግባር ስራ ማከናወናቸውን አስረድተዋል።

የተመራቂ መኮንኖች ተወካይ ም/መቶ አለቃ ስንታየሁ ምስጋናው በበኩሉ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ከነባሩ አመራር ልምድ በመቅሰምና አቅማቸውን በቀጣይነት በማሳደግ ህገ -መንግስቱንና ህገ -መንግስታዊ ስርዓቱን በፍጹም ታማኝነትና የማይናወጥ አቋም ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ያነጋገርናቸው ተመራቂዎችም በአካዳሚው ያገኙት ዕውቀት የተለየ ብቃት የሚያስጨብጥ የሀገርና ህዝብን ታላቅ ኃላፊነት የሚያሳካም ነው በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!