“ሽልማቱ የሁላችንም ነው፣ ልንኮራበት ይገባል” የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ክቡር ጄኔራል ሳሞራ የኑስ

“ሽልማቱ የሁላችንም ነው፣ ልንኮራበት ይገባል”  ሲሉ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ክቡር ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ገለጹ።

ጄኔራል ሳሞራ ይህን የገለጹት በተቋሙ ሥር የሚገኙ ዕዞች፣ የአየር ኃይልና በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ሥር የሚገኙ ልዩ ልዩ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት የተበረከተላቸውን ሽልማቶች አስመልክተው የደስታ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ነው።

 “ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብራክ የወጣ፤ ለህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱና ለህዝቦች የሚያገለግል ሠራዊት መገንባት ተችሏል” ያሉት ጄኔራል ሳሞራ የክብር ሽልማቱ ሠላም በሀገር ውስጥና በውጭ እንዲጠናከር መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ ተልዕኮውን በስኬታማነት ለፈጸመው የመከላከያ ሠራዊታችን የተሰጠ ሽልማት እንደሆነ አስታውቀዋል።

ሽልማቱ የመላው የመከላከያ ሰራዊታችን ጥረት ውጤት እንደሆነ የገለጹት ጄኔራል ሳሞራ፤ “የፈጠርናቸውን አቅሞችና የገነባናቸውን እሴቶች ለማጠናከር ቃል የምንገባበት፣ የሠላምና የልማት ኃይል ሆነን የምንቀጥልበትም ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

ጄኔራል ሳሞራ በተጨማሪ ሽልማቱ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤት እንደሆነም ገልጸዋል።

እንደ ጄኔራል ሳሞራ ማብራሪያ፤ የክብር ሽልማቱ ሠራዊቱ በህዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ በቁርጠኝነት ለማሳካት የሞራል ስንቅ ይሆነዋል ብለዋል።

ጄኔራል ሳሞራ በ2009 ዓ.ም ከቻይና የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የክብር ፕሮፌሰርነት ማዕረግ፣ በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም ደግሞ ከሱዳኑ ፕሬዝደንት ዑመር ሀሰን አልበሽር ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻንና ከሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት የተበረከተላቸው መሆኑ ይታወሳል።

 

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!