ጄኔራል ሣሞራ የኑስ ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻንና የክብር ዶክትሬት ተሰጣቸው

በሳሙኤል ወንድሙ (ሻምበል)

 

የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ክቡር ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ከሱዳን ሪፐብሊክ መንግሥት ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ተሸለሙ፤ የኮራሪ  ዩኒቨርሲቲም  የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡

የሠላም ማስከበር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንዳስታወቁት  ሰሞኑን በካርቱም ሱዳን ከተማ በተከናወነው ሥነ-ሥርዓት የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ፊልድ ማርሻል ኦማር ሃሰን አልበሽር ለጄኔራል ሳሞራ የኑስ ያበረከቱት ይህ ልዩ ሽልማት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ሠላም ከማረጋገጡ ባሻገር የአካባቢው ሀገራት ሠላምና ደህንነት እንዲጎለብት ባበረከተው ጉልህ አስተዋፅኦ  ላስመዘገቡት የላቀ የአመራርነት ሚና የተሰጠ እውቅና ነው፡፡

 

 ሽልማቱና ዕውቅናው ኢትዮጵያ ሠላሟን ከማረጋገጥ ባሻገር በውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲዋ አማካኝነት በአካባቢው ሀገራት ሠላም እንዲሰፍን ለምታደርገው ሁለንተናዊ ጥረት የተሰጠ እንደሆነ የገለጹት የዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተና ጄኔራል አብርሃ ወልደማርያም፤ ሠራዊታችን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ብቃትና ስኬት ስለመወጣቱ የተሰጠ ማረጋገጫ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

 

ሽልማቱ የኢትዮጵያና የሱዳን ህዝብና መንግሥት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሮ  መቀጠሉንና ይህ መደጋገፍ የደረሰበትን ደረጃ አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑንም  አክለው ጠቁመዋል።                 

 ይህ በእንዲህ እንዳለ በ16ኛው የኢትዮ -ሱዳን ወታደራዊ ጥምር ኮሚቴ የአምስት ዓመት ወታደራዊ ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 17ኛው መደበኛ ስብሰባ እንዲቀርብ በሀገራቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ጄኔራል ሣሞራ የኑስ እንዳስታወቁት ስትራቴጂክ ዕቅዱ በድንበር አካባቢ የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች በቀጣይ እንዳይከሰቱና ከተከሰቱም በቀላሉ የሚፈቱበትን ግልጽ አቅጣጫዎች የሚያስቀምጥ ሲሆን፣  የሀገሮቹን  ሠላምና ደህንነት እንዲሁም የጋራ ግንኙነትና  ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል።

 

ስትራቴጂክ እቅዱ ሀገራዊ ሠላም፣ ልማትና እድገታችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተሳሰረ፣ ጥብቅ ግንኙነት ያለውና የሚከናወኑ የትብብር ስራዎችም ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገራቸውንና የበለጠ እየተጠናከሩ መቀጠላቸውን እንደሚያመላክት ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን በመሰረቱት ወታደራዊ ጥምር ኮሚቴ አማካኝነት ባለፉት ዓመታት በጋራ  በርካታ ስራዎች  ተከናውነዋል። ሀገራቱን የሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች አስተማማኝ ሠላም እንዲኖራቸው ከማድረጉም  ባሻገር “የአደጋና ስጋት ተጋላጭነትን መቅረፍም ተችሏል” ያሉት ደግሞ የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜ/ጄኔራል ደስታ አብቼ ናቸው።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!