የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ በጀኔራሎቹ ሹመት ስነ-ስርዓት ላይ ያስተላለፉት መልዕክት

 

‘’በሀገሩ የሚኮራ ሀገሩንም የሚያኮራ፣ ለዘመናት ጀግንነቱን እየደጋገመ ያስመሰከረ፣ የሀገሩን ሉዓላዊነት በማስከበር ፈጽሞ ግንባሩን የማያጥፍ፣ ድል ማድረግ ዜማው፣ ማሸነፍ ቋንቋው የሆነ፣ የአፍሪካ ኩራት የኢትዮጵያ መከታ፣ የራሱን የማይሰጥ የሰውም የማይነካ፣ ሰላምን ከፍ ለማድረግ ራሱ ዝቅ የሚል፣ ህዝቡን በነፃነት ለማኖር የደም ዋጋ የሚከፍል፤ እየከፈለም ያለው ማነው ተብሎ ቢጠየቅ ዓለም ሁሉ ተስማምቶ የኢትዮጵያ ወታደር ነው ማለቱ አይቀርም፡፡

ከድሆች ጓዳ እስከ ገበሬው አጨዳ ድረስ ተሰማርቶ ሰላም የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን ልማት የሚያሳልጥ የመከላከያ ኃይላችን የአገር ፍቅሩ ረቂቅ፣ ዲስፕሊኑ ጥብቅ፣ ተልዕኮው ትልቅ ርዕይው ሩቅ ነው፡፡ የዚህ ጀግና ሰራዊት አካል ሆነው ሽዎች ግዳጃቸውን በላቀ ክብር ፈጽመው አልፈዋል፡፡ እሳት እሳት እየተካ፣ ኮከብ ኮከብን እየወለደ የኢትዮጵያ ማሕፀን ጀግና ማፍራቱን ቀጥሏል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያን የነፃነት ታሪክ ስናስብ ይህንን ለመጠበቅና ለማስከበር የተሰውትን የኢትዮጵያ ልጆች በፅኑ እናስባቸዋለን፡፡ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ናት ስንል የቅኝ ግዛትን ቀንበር የሰበሩትን ኢትዮጵያውያንን ማሰብ ይኖርብናል፡፡

 እንደ እሳት ወላፈን በሚጋረፉ የኢትዮጵያውያን አጥንቶች የታጠሩትን ድንበሮቿን ስናስብ አጥር ቅጥር ሆነው የወደቁትን ኢትዮጵያውያንን ማሰብ አለብን፡፡

ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተፈጥሮ ወታደሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ደግሞ የተፈጥሮ ወታደርነትን ከዘመናዊ ስልጠናና ከዲስፕሊን ጋር ያዋሀዱ ምርጦች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ይህ ነው የዘመናት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የማሸነፍ ጥበብ”፡፡

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!