የኪነ-ጥበባት ስራዎች ዳይሬክቶሬት ሙያተኞችን አስመረቀ

የመከላከያ የኪነ-ጥበባት ስራዎች ዳይሬክቶሬት ከሁሉም ዕዞችና አየር ሃይል ተዉጣተዉ በኦኬስትራ እና በክብር ዘብ ሰልፈኛ ሙያ ያሰለጠናቸዉን ሰማኒያ የሙዚቃ መሳሪያ ሙያተኞችን በመኮንኖች ክበብ በደማቅ ስነ-ስርዓት አስመረቀ፡፡
በዕለቱ የምረቃ ሰነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ደይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ተሰማ ለተመራቂ ሙያተኞችና ባለ ድርሻ አካላት የእዉቅና ሰረተፍኬት ካበረከቱ በኋላ ባሰሙት የስራ መመሪያ ንግግር ኪነ ጥበብ በሰላም ጊዜ ሰራዊትን በሞራልና በወኔ በማዘጋጀት እንዲሁም በጦርነት ወቅት በማነሳሳትና በማዋጋት ከፍተኛ ሚና ያለዉ በሞሆኑ፣ ተመራቂዎች በትምህርት ቤቱ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን እዉቀት ተጠቅማችሁ በየክፍላችሁ በምትሄዱበት ወቅት ሰራዊቱን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ከጎኑ ሆናችሁ ሞራልና ወኔዉን በማነሳሳት፤ ደስተኛና ንቁ እንዲሆን በማድረግ የተጣለባችሁን ተቋማዊ ሃላፊነት በብቃት እንድትወጡ በማለት አሳስበዉ ለተመራቂዎች መልካም የስራ ዘመን ይሁንላችሁ ብለዋል፡፡
በማስከተልም የኪነ ጥበባት ስራዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል አዳነ አስመላሽ የኪነ ጥበባት ትምህርት ክፍሉ ከተመሰረተበት ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ያለፈባቸዉን ዉጣ ዉረዶች የሚያሳይ በፎቶና በድምጽ የተደገፈ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡በሪፖርቱ ካነሱት ነጥብ ዉስጥ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ተልዕኮን መሰረት ያደረገ የኪነ ጥበብ ዉጤት ለዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ አጋዥ የሆኑ የፈጠራ ስራዎች በመፍጠርና በየጊዜዉ በማቅረብ ሰራዊቱንና ህዝቡን የሚያቀራርቡ የኪነ ጥብ ስራዎች እየሰሩ እነደሆነ አብራርተዋል፡፡
የኪነ-ጥበብ ዳይሬክቶሬቱ ዘንድሮ ያስመረቃቸዉ ተመራቂዎች ለ12ኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ በፊት ከተመሰረተበት ከ1935 እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ስያሜ እየተሰጠዉ ለ11 ዙሮች በተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ተጫዋችነት፤ በተወዛዋዥነት፣ በድምፃዊነት፤ በቲያትርና በክብር ዘብ ሰልፈኛ ከተቋሙ መከላከያ አልፎ የክልሎችን የፖሊስ ሰራዊት የኦኬስትራ ሙያተኞችን በማሰልጠን ትላልቅ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችን ያፈራ እና ለዘርፉ ትልቅ አበርክቶ ያለዉ አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ትምህርት ቤት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ከተመራቂ ሰልጣኞች መካከል መሰረታዊ ወታደር ምኞቴ ዘመዱ እና መሰረታዊ ወታደር ሰላም ካህሳይ በሰጡት ተመሳሳይ አስተያየት ተቋሙ በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት ብቁ እንዳደረጋቸዉ ገልፀዉ፤በቀጣይ በሚሄዱበት ክፍል የተማሩትን ሙያ በመጠቀም ሃገራቸዉንና ተቋማቸዉን በቁርጠኝነት፣ በቅንነት እና በጀግንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡
በምረቃ ሰነ-ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች፤ ከዚህ በፊት በትምህርት ቤቱ የተማሩና ያስተማሩ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ጥሪ የተደረገላቸዉ የሰራዊቱ ቤተሰቦችና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!