ዋና መምሪያዉ የተለያዩ ተሸከርካሪዎችን ለሰራዊቱ ክፍሎች አስረከበ

የህብረት ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ለሰራዊቱ የግዳጅ አፈፃፀም የሚያገለግሉ የተለያዩ ተሸከርካሪዎችን በምድር ሃይል ግቢ በመገኘት ለየእዝ አመራሮችና ለመምሪያ ሃላፊዎች ቁልፍ አስረክቧል፡፡ 

በቁልፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስቴር የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጄኔራል አደም መሃመድ ባሰሙት ንግግር እንደገለፁት አሁን እየታደሉ ያሉት ተሽከርካሪዎች የሰራዊታችንን የግዳጅ አፈፃፀም ቀልጣፋና ዉጤታማ ለማድረግ ታስቦ እና በርካታ የሃገር ኢኮኖሚ ወጪ ተደርጎባቸዉ የተገዙ ናቸዉ፡፡ መላዉ አመራርና ሰራዊታችን  ይሄንን ተገንዝባችሁ ከአሁን በፊት የነበሩ የአጠቃቀም ችግሮችን በመቅረፍ  ተሸከርካሪዎችን በእንክብካቤ በመያዝና ለተፈለገዉ ዓላማ ብቻ እንዲዉሉ በማድረግ በተለይ አመራሩ  ለሙያተኞች በግንዛቤ ማስጨበጥ ዙሪያ ትልቅ ንቅናቄ በመፍጠር ብክነትና አደጋን ዜሮ በሚባል ደረጃ በማድረስ የሰራዊታችን የዕለት ተዕለት የግዳጅ አፈፃፀም ያለምንም እንቅፋት እንዲፈፀም የየድርሻችሁን እንድትወጡ በማለት አሳስበዋል፡፡

በማስከተልም በመኮንኖች ክበብ የየዕዙ አመራሮችና የመምሪያ ሃላፊዎች በተገኙበት በተሸከርካሪዎች አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ዉይይት ተካሂዷል፡፡በዉይይቱ ወቅት በተለያዩ የሰራዊታችን ክፍሎች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በተገኘ ዉጤት ላይ በመመርኮዝ የመከላከያ ህብረት ሎጀስቲክስ ዋና ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል ገለፃ አድርገዋል፡፡

እንደ ሜጀር ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል ገለፃ ከዚህ በፊት እንደተቋም በነበረዉ የተሸከርካሪዎች አጠቃቀም ዙሪያ በርካታ ችግሮች የነበሩ መሆናቸዉንና በዚህም በንብረትና በሰዉ ህይወት ላይ ጭምር የተከሰቱ አደጋዎች መኖራቸዉን ገልፀዋል፡፡

ጄኔራሉ አክለዉም የችግሮቹ ዋነኛ መንስኤዎችም፡- የሚከሰቱ ችግሮችን መላመድ፣ ችግሮችን ዉጫዊ ማድረግና ችግሮችን ለባለድርሻ አካላት ብቻ የመስጠት ሁኔታ በመኖሩ ችግሮቹ ከአመት ወደ አመት ከመቀነስ ይልቅ እየጨመሩ መሄዳቸዉን ገልፀዉ ከአሁን በኋላ ሁሉም የሰራዊት አባላት ንብረቶቹን እንደግል ንብረቱ በመቁጠር እና በያገባኛል ስሜት በእንክብካቤና በቁጠባ ሊጠቀምባቸዉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!