የመከላከያ ሚኒስትር ክቡር ለማ መገርሳ በ2012 አዲስ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ለመከላከያ ሠራዊቱና ለተቋሙ ሲቪል ሰራተኞች ያስ ተላለፉት መልዕክት

የመከላከያ ሚኒስትር ክቡር ለማ መገርሳ በ2012 አዲስ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ለመከላከያ ሠራዊቱና ለተቋሙ ሲቪል ሰራተኞች ያስ ተላለፉት መልዕክት

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አኩሪ ግዳጆች እየተወጣችሁ የምትገኙ የመከላከያ ሠራዊቱና የተቋሙ ሲቪል ሰራተኞች፤ እንኳን ለ2012 አዲስ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የመልካም ስራ ዘመንና የብልጽግና እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ!!

የተከበራችሁ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች!

ኢትዮጵያ የሁላችንም ብቸኛ ቤት፤ የሁላችንም መኩሪያና መድመቂያ ናት፡፡ መላው ህዝባችንና የመከላከያ ሰራዊታችን በዚህ መርህ ዕጅ ለዕጅ ተያይዘን ሰላሟን በመገንባት እጅግ የተስፋ ብርሃንን የሚያሳዩ ውጤቶች አስመዝግበናል፡፡ ይህን የህልውና ጉዳይ በተከታታይ ማረጋገጥና ማስቀጠል እጅግ ከባድ ቢሆንም ግዳጆቹ የሚጠይቁትን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል የምንመካበት አኩሪ የሰላም ውጤት አረጋግጣናል፡፡ በዚህ ስኬት ልንኮራ ይገባል፡፡

በመሆኑም ልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶቻችንንና አሰራሮቻችንን በመጠቀም በሰላማችን ላይ የተደቀኑ የከፉ መሰናክሎችን እየበጣጠሳችሁ የአኩሪ ታሪክ ባለቤቷን ኢትዮጵያ ሰላም ወደነበረበት መመለስ ችላችኋል፡፡ በእርግጥም ብዝሃነታችን መድመቂያና መኩሪያ ነውና በአንድነት ተሳስባችሁና ተከባብራችሁ በመኖር፣ ፈተናዎችንም በጠንካራና በሚፋጅ ወኔያችሁና ጀግንነታችሁ በማስወገድና በመሻገር  የሰላሟ ዘብ፤ የህልውናዋ ግንባር ቀደም ጋሻና መከታም ሆናችኋል፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ የምትኖር አኩሪ ታሪክ ያላት፣ ነገም አዲሱ ትውልድ አዲስና የሚያኮራ ታሪክ የሚጽፍላት የኩሩ ህዝቦች መኖሪያ መሆኗንም ዳግም አስመስክራችኋል፡፡ ከመከላከያ ሰራዊቱም ጋር ሌት ተቀን በትጋት በመስራት አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም በመገንባት በተስፋ ለአዲስ ዓመት ብስራት በቅታችኋል!

በመጨረሻም ህዝባችን ለሠራዊታችን እየሰጠ ያለው ክብር፣ ሞራልና ድጋፍ ወደር የሌለው በመሆኑ፤ የመከላከያ ሠራዊታችንም ለኢትዮጵና መላው ህዝቦቿ ዘላቂ ደህንነት፣ ዕድገትና ብልጽግና ሲል ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተሟላ ዝግጁነት ያለው መሆኑን ሳረጋግጥላችሁ በታላቅ ኩራትና ደስታ ነው፡፡ በድጋሚ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!

መላው የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሲቪል ሰራተኞች!

የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ፤ አስተማማኝም የማድረግ ተልዕኳችሁን በሚያኮራ ሁኔታ እየተወጣችሁ እንደሆነ ስኬቶቻችሁ ይመሰክራሉ፡፡ በአኩሪ መስዋዕትነታችሁ ደማቅ ታሪክ ጽፋችኋል፡፡ በመሆኑም በሀገራችን ላይ ከዚህም ከዚያም የተደቀኑ ፈተናዎችን ሁሉ በጽናትና በጀግንነት እያሸነፋችሁ ቀጥላችኋል፡፡ ስለሆነም ሰላማችን እየተስፋፋ ነው፡፡ ድህነትን በጥረታችን ለማስወገድ የጀመርነው የጋራ ትግልም ግለቱን ጠብቆ ቀጥሏል፡፡ የውስጥ ሰላማችንን አስተማማኝ ማድረግ በመቻላችን ዲፕሎማሲያዊ ድሎች እያረጋገጥን እንገኛለን፡፡ ከጎረቤቶቻችን እና ከዓለም ወዳጆቻችን ጋርም ሰላምን በመገንባትና ድህነትን በመፋለም በተጠናከረ ሁኔታ አብረን እየሰራን እንገኛለን፡፡ ስለዚህ  የሀገራችንን ሰላም በጽኑ መሰረት ላይ በመገንባት የሚያኮራ አሻራ እያሳረፋችሁ በመሆኑ ኮርተንባችኋል ፤እናንተም ልትኮሩ ይገባል፡፡

ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት አባላት!

ሰላምን መገንባትና ማረጋገጥ ያለ ጥረትና መስዋዕትነት እንደማይገኝ የራሳችሁ ተሞክሮ ምስክር ነው፡፡ ስለዚህ የሀገራችንን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ዘወትር ዝግጁነትን መገንባት ይገባል፡፡ በመሆኑም መከላከያ ሚኒስቴር ሠራዊቱን ዘመናዊና ፕሮፌሽናል እንዲሁም አኗኗሩን ምቹ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ የሚያደርጉ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡አዋጆችን እና መመሪያዎችን በጥናት ላይ ተመስርቶና በሠራዊቱ ተሳትፎ በማሻሻል መብቶቹና ግዴታዎቹ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ እንዲከናወኑ እያደረገ ይገኛል፡፡የግዳጅ አፈጻጸሙ ቀልጣፋ፣ ምቹና ዘመናዊ እንዲሆንም የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የተጀመሩ ስራዎችም እጅግ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያረጋገጡ ናቸው፡፡ ይህን  በቁርጠኝነት አጠናክራችሁ በመቀጠል ዘመናዊና ፕሮፌሽናል ሰራዊት ግንባታ ሂደቱ ላይ እያበረከታችሁ ያለው ሚና የተለየ በመሆኑ ዘወትር ደማቅ አሻራችሁን ማሳረፍ ይገባችኋል፡፡

ውድ የመከላከያ ሰራዊት አባላት!

ከዚህች በየዕለቱ ተለዋዋጭና ውስብስብ ከሆነች ዓለም ጋር በፍጥነት መራመድና ተወዳዳሪ መሆን ተልዕኳችንን ለማሳካት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡  ስለዚህ ለራስ፣ ለወገንና ለሀገር ጠቃሚ በሆኑ ፍሬ ሀሳቦች፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶችና ዲስፕሊን በመታነጽ አብሮ መጓዝ ግዳጅን በሚፈለገው ልክ ለማሳካት ይረዳል፡፡ ስለዚህ ሀገራዊ፣ አካባቢያዊ ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በዴሞክራሲያዊ አግባብ በጥሞና በመተንተን፣ ዕውቀትን በመቅሰም፣ ክህሎትንም በማበልጸግ ዘመናዊነታችንን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅባችኋል፡፡ በህገ - መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት ዋነኛው ተልዕኳችን የሀገራችንን ሰላም መገንባት፤ሉዓላዊነቷንም መጠበቅ ስለሆነ ይህን በቅንነት፣ በታማኝነት እና በፍጹም ቁርጠኝነት መፈጸም ይገባችኋል፡፡ ስለሆነም የገባችሁትን ቃል ኪዳንና የጀግኖች ሰማዕታትን አደራ ዘወትር በማክበርና በማደስ አዳዲስ ድሎች እንደምታስመዘግቡ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡

መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ!

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!