ለሠላም መረጋገጥ የሠራዊቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የሰሜን ዕዝ አካል የሆነው የ20ኛው ቃሉ ክፍለጦር 4ኛ ብርጌድ  በ2011 በጀት ዓመት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለፀ።

በማጠቃለያ ውይይቱ ላይ የክፍለጦሩ ዋና አዛዥ ብ/ጄኔራል ኑሩ ሙዘይን እንደገለፁት፤ በክፍለጦሩ ስር የሚገኙ ብርጌዶች የተሰጣቸውን ተቋማዊ ግዳጅ በተሻለ የግዳጅ አፈፃፀም በማጠናቀቃቸው ሊኮሩ እንደሚገባና በቀጣይ በጀት ዓመትም የበለጠ ጥረት በመጨመር ሀገርና ህዝብ የጣለባቸውን አደራ በሙሉ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የዓመቱን አጠቃላይ የሥራ አፈፃፀም አስመልክተው የ20ኛው ቃሉ ክፍለጦር የ4ኛ ብርጌድ ዋና አዛዥ ተወካይ ሌተና ኮሎኔል ተስፋዬ ተካ ሪፖርት ማቅረባቸውን የክፍለጦሩ ሪፖርተር ፲አለቃ መኳንንት ደባሱ ከስፍራው ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል በቦኖ በደሌ እና በጅማ ዞን ተሰማርቶ የሚገኘው የ12ኛ ክፍለ ጦር የ4ኛ ብርጌድ የሻለቃ 1 እና 3 የሠራዊት አባላት ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ሥራ መስራታቸው ተገለጸ፡፡

የ4ኛ ብርጌድ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አዘነ ሽመልስ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ200 በላይ ሽጉጥ፤ 55 ክላሽ፤ በርካታ ቁጥር ያለው የተለያዩ መሣሪያዎች ጥይቶች እንዲሁም ከ400 በላይ ሞተር ሳይክሎችና ከ350 በላይ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በአካባቢው ይፈጸሙ የነበሩ ወንጀሎች መቀነስ መቻላቸውንና በቀጣይም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ወንጀለኞችን የመቆጣጠር፣ የደህንነትና የፀጥታ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የሊሞ ኮሳ ወረዳ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደግፌ ነጋሶ በበኩላቸው፤ በወረዳው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ከገባ ጊዜ ጀምሮ የፀጥታ ሁኔታው መሻሻሉን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ ጨምዴሳ እና የፌዴራል ፖሊስ አባል ዋና ሳጅን ብርሃኑ ግርማ በሰጡት አስተያየት ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመቆም የወረዳውን ሠላምና ፀጥታ በአስተማማኝ እየጠበቅን እንገኛለን ብለዋል ሲል ም/፲ አለቃ ቡልቻ ዘመን ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡

በተያያዘ ዜና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን የመንዲ ክላስተር ፖስት ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የቀጣናውን ሠላም በማረጋገጥ ዙሪያ ከፍተኛ ሥራዎች መስራቱን አስታወቀ፡፡

የክላስተር ኮማንድ ፖስት በስራ አፈጻጸም ግምገማው ላይ እንደገለጸው ኮማንድ ፖስቱ በምዕራብ ዕዝ ከ22ኛ ንስር ክፍለ ጦር እና በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ሰባት ወረዳዎች ስር ከሚገኙ ቀበሌዎች የፀጥታ አካላት ተውጣጥቶ የተቋቋመ ሲሆን ተቀናጅቶ ወደስራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ውጤታማ ስራ ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በምዕራብ ወለጋ ዞን አንፃራዊ ሠላም ተፈጥሮ የአካባቢው ህዝብ ሠላማዊ ኑሮውን እየመራ ይገኛል ማለታቸውን  ሲል ፲አለቃ አብርሃም ጥላሁን ከስፍራው ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የ24ኛ ቴዎድሮስ ክፍለ ጦር የሠራዊት አባላት በምዕራብ ወለጋና አካባቢያቸው እያካሄዱት ባለው የሠላምና የፀጥታ ሥራ አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የአካባቢው አመራሮች ገለጹ፡፡

የሆሮ ጉድሩ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጁባ አዱኛ እንደተናገሩት፤ የ24ኛ ክፍለ ጦር የሠራዊት አባላት በሆሮ ጉድሩ ዞን በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች አስተማማኝ ሠላም መፍጠራቸውንና የህዝቡን ሠላም እያወኩ የነበሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችንም በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሆሮ ጉድሩ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ተመስገን ኃይሌ በበኩላቸው የመከላከያ ሠራዊቱ በራሱ አቅም የአካባቢውን ፀጥታ ከማስከበሩም ባሻገር የአካባቢውን ሚሊሻዎች በማሰልጠንና በማደራጀት ወደ ስራ እያስገባና ህብረተሰቡ ለሠላሙ ራሱ ዘብ እንዲቆም እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በነጆ ከተማና ዙሪያዋ የሚገኙ 35 ቀበሌዎች በሙሉ ከሠላም ስጋት ወጥተው ወደ ልማት መሸጋገራቸውና ይህም በሠራዊቱ ተከታታይና በማያቋርጥ ሠላምን የማስፈን ተግባር የተገኘ ውጤት መሆኑን የወረዳው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ተወካይ አቶ አማኑ ዴንሳ ገልጸዋል፡፡

የነጆ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ካሳዬ ፈቃዱ በበኩላቸው የሠራዊቱ አባላት ከወረዳው የፖለቲካ አመራሮች ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎችና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በጥምረት በሰሩት መጠነ ሰፊ ስራ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል ሲል የዘገበው የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ፲ አለቃ ሰማኸኝ ጥላሁን ነው፡፡

በተያያ ዜና በምዕራብ ዕዝ 22ኛ ንስር ክፍለ ጦር የ1ኛ ብርጌድ የሥራ መሀንዲስ የሠራዊቱን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት ውጤታማ ሥራ ማከናወኑ ተገለጸ፡፡

የ22ኛ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ ምክትል አዛዥ ለሰው ሀብት ልማት ሌተና ኮሎኔል በርሄ አብርሃ፤ የብርጌዱ ስራ መሀንዲስ ያከናወነውን ሥራ አስመልክተው እንደገለጹት፤ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ክልል የተፈጠረውን የሠላም እጦት ለመፍታት ሠራዊቱ ግዳጅ ተቀብሎ በአካባቢው መሰማራቱን አውስተው ሠራዊቱ የተሰጠውን ተቋማዊ ተልዕኮ ውጤታማ በሆነ መንገድ መወጣት እንዲችል መሀንዲስ ክፍሉ መንግስት በበጀተው በጀት የሠራዊቱን መኖሪያ ካምፕ እየሰራ ይገኛል፡፡

የብርጌዱ ስራ መሀንዲስ ኃላፊ ም/መ/አለቃ አብርሃ ግደይ በበኩላቸው በብርጌዱ ስራ መሀንዲስ ሙያተኖች የሠራዊቱ መኖሪያ ካምፕ፤ ሆስፒታል፤ ቢሮዎች መጸዳጃና ዳቦ ቤት እንዲሁም የመመገቢያና የመዝናኛ ክበብ ያካተተ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል ሲል የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ፲አለቃ አብርሃም ጥላሁን ዘግቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የ8ኛ ማዕበል ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አንደኛ ታንከኛ ብርጌድ በ2011 በጀት ዓመት ጥሩ ሥራ አፈጻጸም ለነበራት ሻለቃ ሽልማት ተሰጠ፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ሽልማቱን ያበረከቱት የሰሜን ዕዝ ኢንዶክትሪኔሽን  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል አበባው መንግስቱ እንደተናገሩት፤ እንደክፍለጦር ካሉት ብርጌዶች እና ሻለቆች በበጀት ዓመቱ ለመመሪያና ደንቦች ተገዥ በመሆንና እርስ በርስ በመደጋገፍ ያሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር የበለጠ ሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

የተሸላሚዋ 3ኛ ሻለቃ ዋና አዛዥ ሻለቃ ተክለ ሙዑዝ ሀይሉ በበኩላቸው ለሻለቃዋ የተሰጠው ዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ይበልጥ ጥንካሬያችንን አቅበን እንድንቀጥል የሚያደርግ መሆኑን አውቃችሁ በበለጠ ሞራል ልትሰሩ ይገባል በማለታቸውን የብርጌዱ ሪፖርተር ም/፲ አለቃ ደጀን ጉልላት ዘግቧል፡፡

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!