በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ሲካሄድ የነበረዉ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያና አሜሪካ መንግስታት መካከል ለአስራ አምስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረዉ የጋራ ወታደራዊ  ልምምድ መጠናቀቁ ተገለፀ ፡፡

በልምምዱ የማጠቃለያ ስነስርዓት ላይ በክብር እግድነት የተገኙት የኢትዮጲያ የሰላም ማስከበር ማዕከል ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ሀብታሙ ጥላሁን ባሰሙት ንግግር በነበረን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ  በርካታ ልምዶችን የተለዋወጥንበትና ትልቅ ግብአት ያገኘንበት ልምምድ ነበር ብለዋል ፡፡

በልምምዱ አስራ አንድ አገራት የተሳተፉ ሲሆን እነሱም ከአፍሪካ  ኢትዮጵያ ፣ኡጋንዳ ፣ብሩንዲ ፣ ሶማልያ እና ጅቡቲ ሲሆኑ በተጨማሪም ከቀረዉ የአለም ከፍል ጃፓን ፣ዩናይትድኪንግደም ፣ኔዘርላንድ ፣ፈረንሳይ ፣ብራዚል እና አሜሪካ ተጠቃሽ  ናቸዉ፡፡

 ልምምዱን በዋናነት ሲምሩ የንበሩት ኢትዮጵያና አሜሪካ ሲሆኑ ልምምዱም በአዲስ አበባ የሰላም ማስከበር ማዕከል ፣ በጦርሃይሎች ሆስፒታል እና በሁረሶ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል መካሄዱ ተገልጿል ፡፡

የልምምዱ ዋና አላማም በሶማልያ ተሰማርቶ ለሚገኘዉ የአሚሶም ሰላም አስከባሪ ሃይል ግዳጁን በብቃት መወጣት እንዲችል አቅም ለመፍጠርና ድጋፍ ለማድረግ  ታስቦ የተደረገ ልምምድ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

 የጋራ ልምምዱ ካተኮረባቸዉ መስኮች ዉስጥም  በጤና፣ በዉጊያ ድጋፍ ፣በዉጊያ ዕቅድ፣ በመገናኛ ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በተለያዩ  የእስታፍ ስራዎች ዙሪያ በንድፈ ሃሳብና በመስክ የተግባር ልምምድ በማድረግ በረካታ የተሞክሮ ልውውጥ ማድረጋቸዉ ተገልጿል ፡፡

ጀነራሉ አያይዘዉም በተለይ ደግሞ ለምስራቅ አፍሪከና የቀጠናዉ አገራት ሰላም እና ፀጥታን ከማረጋገጥ አንፃር ለምንሰራቸዉ ስራዎች ካሉን አቅሞች በተጨማሪ የጋራ የሆነ አስተሳሰብ  እንዲኖረንና ከወቅቱ ጋር ሊሄድ የሚችል ዘመናዊ እና ፕሮፌሽናል ቁምናን በመላበስ በብዙ መስኮች ላይ አብረን  መስራት የምንችልበትን ሁኔታ ፈጥረናል በማለት ተናግረዋል ፡፡

 ብርጋዴል ጀነራል ሃብታሙ አክለዉም ኢትዮጵያ ለዚህ ልምምድ መመረጧ ለአህጉሩና ለመላዉ አለም ለሰዉ ልጆች ሰላም  እንዲሰፍን ካበረከተችዉ እና እያበረከተች ካለችዉ አስተዋፅዖ አንፃር መሆኑ የተቀረው አለም ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነትና ታማኝነት ምን ያህል እንደተረዳ የሚያሳይ በመሆኑ መላዉ ሰራዊታችንና ህዝባችን ልንኮራ ይገባል ብለዋል ፡፡

 

በተጨማሪም የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት ለበርካታ አመታት የዘለቀና በብዙ የትብብር መስኮች አብረን እየሰራን የመጣን በመሆኑ አሁንም ወደፊት የዚህ አይነቱ ትብብር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል በማለት አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል ፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የአሜሪከዉ ወታደራዊ  አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ላፕቲ  ቻኡ  ፍሎራ እንደተናገሩት በነበረን የጋራ ልምምድ አንዳችን ከአንዳችን በርካታ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን የቀሰምን ሲሆን በተለይ በሶማሊያ አልሼባብን ለማጥፋት በሚድረገዉ ዘመቻ የተሳተፉ አገራትን አቅም ለማጠናከር ታስቦ የተካሄደ ልምምድ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ ጀነራል ላፕቲ አያዘዉም በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ፣ ኬንያ ፣ ኡጋንዳ ፣ ጅቡቲና ብሩንዲን በመጥቀስ እስካሁን ላድረጋችሁት እና እያደረጋችሁት ላላችሁት አስተዋፅዖ ልትደነቁ ይገባል ብለዋል ፡፡

 

በማስከተልም በተለይ  ኢትዮጵያዉያን ለቀጠናዉ ሃገራትና ለዓለም ሰላም እያበረከታችሁ ላላችሁት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ፤ እንዲሁም በነበረን ቆይታ ላሳያችሁን ቁርጠኝነት እና ላደረጋችሁልን ድጋፍ  ከልብ እናምሰግናለን በማለት ተናግረዋል ፡፡

በመጨረሻም  የመንግስታችንን የአረንጓዴ አሻራ የልማት ጥሪን ምክንያት በማድረግ የሁሉም አገራት የሰራዊት አዛዦችና አባላት በሰላም ማስከበር ዋና መምሪያ ቅጥር ግቢ ዉስጥ በተዘጋጀላቸዉ ቦታ ላይ በግልና በቡድን  በመሆን የችግኝ ተከላ ስነ ስረዓት በማከናወን  የዕለቱ መርሃ ግብር ተጠናቋል ፡፡

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!