ፋውንዴሽኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ሊያስረክብ ነው

የመከላከያ  ፋውንዴሽን  በመጀመሪያ ዙር ያስገነባቸውን 112 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በቅርቡ ለሠራዊቱ በዕጣ ለማስተላለፍ ዝግጅት መጠናቀቁን የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሜጀር ጄኔራል አብዱራህማን  እስማኤል ተናገሩ ፡፡

 ጀነራል መኮንኑ ሰሞኑን በፅህፈት ቤታቸው አፈፃፀሙን  አስመልክተው ለመከላከያ ሚዲያ አባላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ በ2002 ዓ.ም በሚኒስትሮች  ምክር ቤት የተቋቋመው የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን የሠራዊቱን የመኖሪያ ቤት ፍላ ጎት ለማሟላትና ተጠቃሚ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ መሰረትም ሠራዊቱ በተቋሙ ውስጥ በማገልገል ላይ እያለም ሆነ አገልግሎቱን አጠናቆ ሲወጣ የቤት ባለቤት እንዲሆን ለማድረግና ሌሎች መሰል ማህበራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ዓላማ ይዞ ፋውንዴሽኑ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

 ለመጀመሪያ ጊዜ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ቤቶችን ለሠራዊቱ ለማስተላለፍም ኮሚቴዎች  በማዋቀርና አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የፊታችን ሓምሌ 13 ቀን 2011 ዓ.ም  በሳሚት ቁጥር አንድ 112 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ለባለ ዕድለኞች በዕጣ ለማስተላለፍ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል ፡፡

 ፋውንዴሽኑ ከዚህ ቀደም  ከባህር ዳር ከተማ መስተዳደር የገዛውንና በአሁኑ ወቅት ምዕራብ ዕዝ በኪራይ እየተገለገለበት የሚገኘውን የ84 አባወራ የጋራ መኖሪያ ቤቶችም በቦርድ እንዲወሰን በማድረግ የተቀመጠውን መስፈርት ለሚያሟሉ የሠራዊቱ አባላት በእጣ ለማስተላለፍ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ያሉት ጄኔራል መኮንኑ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ ከሚገኙት መካከልም የሳሚት ቁጥር ሁለት 528 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በቅርቡ በማጠናቀቅ ለሠራዊቱ እንዲተላለፉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡   በቅርቡ ዕጣ የሚወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከባለ አንድ መኝታ እስከ ባለ አራት መኝታ መሆናቸውንና ቀደም ሲል በወጣው መመሪያ መሰረት  እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም 20 በመቶና ከዚያም በላይ ለቆጠቡ የሰራዊት አባላትና በተቋሙ ውስጥ ላሉ ቋሚ ሲቪል ሠራተኞች እንዲሁም ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ የተሰናበቱ  የሠራዊቱ  አባላት  በዕጣው እንደሚካተቱ የተናገሩት ደግሞ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚና  የቤቶች ግንባታ ማስተላለፊያና ማስ ተዳደር ኃላፊ ኮሎኔል ያዴታ አመንቴ ናቸው ፡፡

 ኮሎኔሉ አክለውም ከጥር 2001 ጀምሮ እስከ ነሓሴ 2006 በጡረታ የተሰናበቱ የሠረዊቱ አባላት በተቀመጠላቸው መስፈርት መሠረት እንደሚካተቱና ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታ የወጡ እንዲሁም አሁን በስራ ላይ ያሉ  የሠራዊቱ  አባላት እኩል ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡

 የቤቶች የአባላት ምዝገባና ጥንቅር ቤት ማስተላላፍና ማስተዳደር ቡድን ኃላፊ የሆኑት ሻለቃ ያሬድ ሰለሞን በበኩላቸው ለዕጣው ብቁ የሆኑ ተጠቃሚዎች በስራ የሚገኙ የሰራዊቱ አባላት ፣ቋሚ ሲቪል ሠራተኞችና በክብር የተሰናበቱ የሠራዊቱ አባላት በሚል በማዘጋጀት መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት ወደ ሶፍት ዌር ተቀይሮ በሶፍት ዌሩ አማካኝነት ማንኛውም ሠው ባስገበው ብር መጠን ለዚህ ዕጣ ዝግጁ እንዲሆን ተገቢ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!