የክቡር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን የህይወት ታሪክ

ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ከአባታቸው ከ፲አለቃ መኮንን ይመር አና ከእናታቸው  ከወ/ሮ ሂይወት ይህደጎ ተላ በትግራይ ክልል በሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ምጽብላ ወረዳ በእንዳባጉና ከተማ በ1954 ዓ.ም ተወለዱ።

ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በእንዳባጉና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል እንዲሁም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሽሬ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማሩ በነበሩበት ወቅት  የደርግን አስከፊ ሥርዓት ለመደምሰስ በህወሓት የሚመራው የትጥቅ ትግል የተጀመረበት  ስለነበረ ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው በ1969 ዓ.ም ወደ ትጥቅ ትግል በመቀላቀል ቡምበት በሚባል የሥልጠና ማዕከል ሥልጠናቸውን አጠናቀቁ።

ከ1969 እስከ ታህሣሥ 1971 ዓ.ም በህወሓት 91ኛ እና 73ኛ የሚባሉ ሻም በሎችን በተራ ተዋጊነትና በጓድ አመ ራርነት በተለይ በ1970 ዓ.ም ክረምት ደርግ ባካሄደው የሰሜን ዘመቻ በተለምዶ 3ኛ ዘመቻ ተብሎ የሚጠራው ፀረ-ደርግ ዘመቻን በመመከት በጀግንነት ተዋግተዋል።

ከታህሣሥ 1971 እስከ ታህሣሥ 1972 ዓ.ም በህወሓት የተደራጁ የታጥቁ ፕሮፓጋንዳ አሃዱ (በተለምዶ ክርቢት) በሚል የሚጠሩ የጋንታ አመራር በመሆን ግዳጃቸውን በብቃት ተወጥተዋል።

ከታህሣሥ 1972 እስከ ግንቦት 1973 ዓ.ም 573 እና 753 ቦጦሎኒዎች (ሻለቃዎች) የሻምበል መሪ በመሆን፣ ጄኔራል ሰዓረ ከ1974 እስከ 1975 በብርጌድ 43 ውስጥ የሻለቃ አመራር በመሆን በኤርትራ የደርግ ሠራዊት የሻዕቢያ ሠራዊትን ለመደምሰስ ባካሄደው የቀይ ኮከብ ዘመቻ ተሳታፊ በመሆን እጅግ አኩሪና አስደናቂ ጀግንነት ከፈጸሙ አመራሮች ውስጥ አንዱ ነበሩ።

ከጥር 1974 እስከ 1977 ዓ.ም በብርጌድ 43 እና 45 የቦጦሎኒ አዛዥ እንዲሁም በ1978 ዓ.ም የብርጌድ 77 ምክትል ብርጌድ አዛዥ በመሆን በራያ አካባቢ ደርግ ያካሂዳቸው የነበሩ ተደጋጋሚ ዘመቻዎችን በመመከትና በልዩ ስምሪቶች ማለት የታጋዮች ልዩ ጽናት የፈተነ የሠርዶ ልዩ ስምሪትን በጽናት በመምራት፣ በጥር 30 ቀን 1978 ዓ.ም ከመቐለ ከተማ ከነበረው  የደርግ ወህኒ ቤት 1 ሺህ 300 እስረኞች ነጻ ባወጣ ታሪካዊ የአግአዚ ኦፕሬሽን ብርጌድ ምክትል አዛዥ በመሆን ሙሉ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል።

ከ1979 እስከ 1981 ዓ.ም የብርጌድ 70 አዛዥ ሆነው፣ በ1980 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ በተካሄደው ተከታታይ ዘመቻ ´ዘመቻ ብሩኸª በሚል በተሰየመ ከምጉላት- ስንቃጣ-ውቅሮ - ገለበዳ ድረስ፣ ዘመቻ ድልድል በሚል የሚታወቀው 17ኛ የደርግ ክፍለ ጦርን በመደምሰስ አክሱም፣ አድዋና ሽሬ ከተሞች ነፃ ያወጣ ዘመቻ ´ ዘመቻ ጥሙር ቅልጽምª (የተባበሩት ክንድ ዘመቻ) በሚል የሚጠራ ከኮረም እስከ አምባላጃ የደርግ 1ኛ ክፍለ ጦርን ለመደምሰስ በተደረጉ ውጊያዎች በተለይም ልዩ ብቃትና ጀግንነት ይጠይቅ በነበረው የአምባላጃ ውጊያ በብቃትና በጀግንነት ብርጌዳቸውን በመምራት ለድል የበቁ ምርጥ ታጋይ ነበሩ።

ከመስከረም 1981 እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም የደርግ ሥርዓት እስከ ወደቀበት ድረስ የአውሮራ ክፍለ ጦር አዛዥ በመሆን፣ ከመስከረም 1981  እስከ የካቲት 12 ቀን 1981 ዓ.ም ሽሬ እና አካባቢው መሽጎ የነበረ የደርግ 604ኛ ኮር በተከታታይ ውጊያዎች አዳክሞ ለመደምሰስ በተደረጉ ውጊያዎች እንዲሁም አብዛኛው የትግራይ መሬት መቐለ ከተማን ጨምሮ የደርግ ሠራዊት ለቆ ከወጣ በኋላ ከነሐሴ መጨረሻ እስከ ጳጉሜ 1981 ዓ.ም ´ሠላም በትግል ዘመቻª ተብሎ በሚጠራው ከማይጮው እስከ ጎብዬ በተደረገው የደርግ 605ኛ ኮር የመደምሰስ ዘመቻና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትግራይን ነፃ ያወጣ ዘመቻ ክፍለ ጦራቸውን በብቃት በመምራት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ተወ ጥተዋል።

ከመስከረም 1982  እስከ ጥር 1982 ዓ.ም ´ፋና ኢህአዴግª ተብሎ በሚጠራ መላ ደቡብ ወሎን ከፊል ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ጎንደርን ነጻ ያወጣ ዘመቻ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ጽናት የጠየቀው የጉና የመከላከል ውጊያ ደማቅ የደብረ ታቦር የማጥቃት ውጊያ ክፍለ ጦራቸውን በብቃት መርተው ለድል አብቅተዋል።

በመጨረሻዎቹ 1982 ዓ.ም ደርግ ይመካበት የነበረውን 3ኛ ክፍለ ጦርን ለመደምሰስ ሰሜን ሸዋ መራኛ ላይ የተደረገውን ውጊያ በከፍተኛ ብቃት መርተዋል። በ1983 ዓ.ም አጋማሽ ´ዘመቻ ዋለልኝª ደሴንና ከፊል ሰሜን ሸዋን ነፃ ለማውጣት በተደረገው ውጊያ እና ´ዘመቻ ወጋገንª ተብሎ በተሰየመው የደርግን ሥርዓት ጠቅልሎ ለመደምሰስ በተደረጉ ተከታታይና አንጸባራቂ ድሎች እየታጀቡ ክፍለ ጦራቸውን መርተው እስከ ኡጋዴን የዘለቁ ጀግና የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ በደርግ የሽግግር መንግሥት የኢህአዴግ ሀገራዊ የሠራዊት አደረጃጀት የምሥራቅ ዕዝ ዘመቻ ኃላፊ በመሆን፤ እንዲሁም ከየካቲት 1987 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሀገር አቀፍ የሠራዊት ምሥረታ የምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ በመሆን ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በብቃት ተወጥተዋል። በግንቦት 1990 ዓ.ም የኤርትራ መንግሥት ሀገራችን በወረረበት ወቅት የቡሬ ግንባር አዛዥ በመሆን የሀገራችንን ዳር ድንበር አስከብረዋል። በየካቲት 1991 ዓ.ም የኤርትራ ሠራዊት ከባድመ ነፃ ባወጣ ´ዘመቻ ፀሐይ ግባትª የባድመ ግንባር ግራ ክንፍ አዛዥ በመሆን ዘመቻው እንዲጠናቀቅ አኩሪ ድል ፈጽመዋል።

 እንዲሁም ከ1992 እስከ 1994 ዓ.ም የ107ኛ ኮር ዋና አዛዥ፣ ከ1994  እስከ 1997 የአርሚ አንድ (የሰሜን ግንባር) ዋና አዛዥ፣ ከ1997  እስከ 2006 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ በመሆን ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል።

ጄኔራል ሰዓረ ከትጥቅ ትግሉ እና በመደበኛ ሠራዊት ግንባታ ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ ተጠቅመው በተለይም ሠራዊቱን በወታደራዊ ሳይንስ ጥበብ የተካነ እንዲሆን፤ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ሚናቸውን በይበልጥ እንዲጫወቱ ለማድረግ ከ2006  እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። በዚህም በትምህርትና ሥልጠና ተቋማት በሠራዊት ግንባታችን ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ በብቃት የመሩ ጄኔራል መኮንን ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ ለረጅም ዓመታት የመከላከያ ካውንስል አባል በመሆን መከላከያ ሠራዊታችን ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ጠብቆ ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ መወጣት የሚችል ሠራዊት ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና የተጫወቱ ከመሆኑም ባሻገር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሴኩሪቲ ካውንስል አባል በመሆን ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሀገራችን አስተማማኝ ሠላም ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ጄኔራል ሰዓረ በነበራቸው የአመራር ብቃት ከመጋቢት 2010  እስከ ግንቦት 2010 ዓ.ም የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ  ኤታዦማር ሹም በመሆን፤ ከግንቦት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ያለመረጋጋትና የህዝብ መፈናቀል የነበረበት በመሆኑ በአብዛኛው የሀገራችን አካባቢዎች ሠራዊታችን አሠራርን ተከትሎና ህዝባዊ ባህሪውን ጠብቆ ግዳጁን እንዲወጣ በማድረግ ህዝባችን በሠላም ወጥቶ እንዲገባ በማድረግ ሂደት የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል። በሀገራችንም ለውጥ በተከሰተ ጊዜ በሀገራችን የነበረው ሁኔታ ውስብስብ መሆኑ ይታወቃል።

የኢፌዴሪ መከላከያ በሁሉም የጦርነት አውዶች ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ መወጣት የሚችል ጠንካራና ዘመናዊ ሠራዊት አድርጎ ለመገንባት የሪፎርም ሥራ መጀመሩ ይታወቃል። ይህ የሪፎርም ሥራ ሲጀመርም ሀገራችን በበርካታ አካባቢዎች የፀጥታ መደፍረስ የሚታይበት ነበር። ይሁን እንጂ ጄኔራል ሰዓረ በአንድ በኩል በሀገራችን የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት እና ሠላምን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት  አድርገዋል። በዚሁ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ደግሞ ተቋማዊ ሪፎርም በማቀድና በመምራት የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል።

ጄኔራል ሰዓረ የመከላከያችን የሪፎርም ሥራ በተፈለገው መንገድ በውጤታማነት እንዲቀጥል ከማድረግ አንጻር በብዙ ጫናና ተግዳሮት ውስጥ በማለፍ ከምንም በላይ ለውጡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ፋይዳ በማስቀደም የበኩላቸውን ድርሻ ያበረከቱና ጉልህ ሚና የተጫወቱ ዕንቁ ኤታማዦር ሹም ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ በነበራቸው ከፍተኛ ተቋማዊ አስተዋጽኦ የኢፌዴሪ መደበኛ ሠራዊት ሲመሰረት በ1988 ዓ.ም የሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረግ ጀምሮ በ2010 ዓ.ም የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ የደረሱ ሲሆን፤ የትጥቅ ትግል ተሳትፎ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳይ ጨምሮ በርካታ ሜዳይና ኒሻኖች ከኢፌዴሪ መንግሥት ተበርክቶላቸዋል።

ጄኔራል ሰዓረ በነበራቸው ከፍተኛ የመማርና ራስን በትምህርት የማሳደግ ፍላጎት ትምህርታቸውን በመቀጠል በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በለንደን ግሪንዊች ዩኒቨርስቲ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የማንበብ ልምድ የነበራቸውና ሌሎችም እንዲያነቡ የሚገፋፉ ምሳሌ የሆኑ መሪ ነበሩ።

 ጄኔራል ሰዓረ  በወጣትነት ጊዜያቸው ወደ ትግል ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ ህይወታቸውን ለህዝብ የሰጡ፣ ለህዝብ የታገሉ፣ ስለግላቸውና ቤተሰባቸው ሳይ ጨነቁ፣ ለህዝብ ሲጨነቁና ሲታገሉ የኖሩና ለህዝብ ልዕልና ህይወታቸውን የሰጡ አኩሪ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ መኮንን በትግል ወቅትም  የውትድርና አገልግሎት ዘመናቸው በግላቸው ፍጹም ጀግና፣ ከተራ ወታደር ጀምሮ አሁን እስከ ነበሩበት ኃላፊነት ደረጃ ድረስ በሁሉም አውደ ውጊያዎች በጀግንነታቸው የታወቁ፣ በዋሉባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ በአኩሪ ጀግንነት የተወጡ፣ በነበራቸው ፍጹም የጀግንነት ባህሪም አባሓዊ (አባ እሳቱ) እየተባሉ የሚቆላመጡ ጀግና ታጋይ ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ አንድ ቀንም ራሳቸውን እንደ መሪና አዛዥ አይተው የማያውቁ፣ ሁሉንም  ሰው በእኩል ዓይን የሚያዩና የሚታገሉ፣ ከተራ ወታደር ራሳቸውን ተራ ወታደር አድርገው የሚያዩ፣ ከጓደኞቻችውና እኩያዎቻቸው ደግሞ ተግባቢ እና ሳቂታ፣ አንድ ቀንም በጥቃቅን ስሜቶች ለማንም ሰው ፊታቸውን አጥፈው የማያውቁ አኩሪ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ ከውጊያ በፊት በውጊያ ውስጥና ከውጊያ በኋላም የተጋጣሚውን ኃይል ሁኔታ በጥልቀት የሚያውቁና የሚያነቡ፣ በየደቂቃውና ሰከንዱ የሚኖሩ ለውጦች ከዕውቀታቸው ውጭ የማይወጡ፤ ሁልጊዜ ፍጹም የቀደምትነትና የድል አድራጊነት ብቃትና ውጤት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ፣ በአካሄዷቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ውጊያዎች ሁሉ ውጤታማ ታጋይ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ጀግና ታጋይ መሪ ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ ራሳቸው  ጀግና መሆን ብቻ ሳይሆን በሥራቸው የሚመደቡ ታጋዮችና ወታደሮች ራሳቸውን አስመሰሎ የመቅረጽ ባህሪ የነበራቸው፣ በትግል ወቅትና ከትግሉ ወቅት በኋላም  የሚመሯቸው የሠራዊት ክፍሎች በጀግንነታቸው የታወቁና በድል አድራጊነታቸው ቅድሚያ የሚመደቡ አሃዱዎችና ዩኒቶች እንደነበሩ ሁሉም የሚመለከተው ሃቅ ነው። በጥቃቅን ችግሮች ፍጹም የማይንበረከኩ፣ በአስቸጋሪ ወቅትም ራሳቸውን እንደ ብረት አቅልጠው ጠርተው በድል አድራጊነት የተወጡ፣ ሠርዶ በነበረው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታም በተፈጥሮ ይሁን በሰው ሰራሽ  አስቸጋሪ ሁኔታ ሳይሸነፉ በድል አድራጊነት የተወጡ፣ የሚፈጠሩ እጅግ አስቸጋሪ የሚባሉ ሁኔታዎችም ለድል የመቀየር ልምድና ባህሪ ያካበቱ ፍጹም የተዋጣላቸው ጀግና ተመሪና መሪ የነበሩ አንቱ የሚባሉ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ በፍጹም ሥነ-ምግባር የታነጹ፣ ለህዝብ ዓላማ ከመኖርና ከመሞት ውጭ ስለ ግላቸው ፍጹም የማይጨነቁ፣ ራሳቸውንና ህዝቡን አክብረው ለህዝቦች ልዕልና ሲሉ ህይወታቸውን የሰጡ ፍጹም የተዋጣላቸው ጀግና የህዝብ ልጅ ነበሩ። እንዲሁም ለህዝብና ለመንግሥት አመራሮች ራሳቸውን ተገዢ በማድረግ ከህዝብና መንግሥት የተሰጣቸውን ተልዕኮና ኃላፊነት ለመወጣት ሲታትሩ የኖሩ፣ ለግል ዕረፍትና ጨዋታም ጊዜ ሰጥተው የማያውቁ በሁኔታ ውስጥ የተፈጠሩ በሁኔታ ውስጥ ያደጉ ሁኔታዎችን ለህዝብ ጥቅምና ልዕልና ሲቀይሩ የኖሩ ´የሁኔታ ሰውª ተብሎ ሊያስጠራ የሚያስችል ባህሪ ያሳደጉ ምርጥ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ በመሪዎችም ቢሆን ፍጹም ተወዳጅ የአስቸጋሪ ሁኔታ ቀያሪ ተደርገው ሲመረጡና ሲሰሩ የኖሩ ሲሆን፤ ህዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እየተወጡ በነበሩበት ወቅት በአንድ የጠላት ቅጥረኛ የጥበቃ አባል በተተኮሰባቸው ጥይት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ አኩሪ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ጄኔራል ሰዓረ ከህግ ባለቤታቸው ከኮሎኔል ጽጌ አለማየሁ አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል።

 

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!