ኮሌጁ በተለያዩ ዘርፎች ሰልጣኞችን አስመረቀ

 

የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊቱን ለማዘመን የተለያዩ የትምህርትና የሰልጠና ተቋማትን ከፍቶ በልዩልዩ ሞያዎች አሠልጥኖ አስመርቋል። ይህው የሰው ኃይል የማልማት ስራም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከተቋሙ ኮሌጆች መካከል የሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አንዱ ነው። ኮሌጁ በ1953 ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ የሠረዊቱን አባላትና ስቪል የህብረተሰብ ክፍሎችን ለውጤት አብቅታል። ከግዜ ወደ ግዜ የማሠልጠን አቅሙን እያጐለበተ የመጣው ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ በዘንድሮው አመትም ሚያዝያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም 434 ሰልጣኞችን በቀንና በማታ መርሃ-ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች አስመርቋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ ብ/ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ «የመከላከያ ኮሌጆች በየዘርፉ በርካታ የሠራዊት አባላትን በተለያዩ ሞያዎች ለከፍተኛ ደረጃ እያበቁ እንደሚገኙና የሠራዊቱን የውጊያ አቅም ከመገንባት አኳያም ከፍተኛ ድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ» ገልጸዋል።

የክብር እንግዳው አክለውም ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት መስክ ሀገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት ሙያው በሚፈቅደው ዲስፕሊን በፈፀሙት ቃለ-መሀላ መሰረት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

ኮ/ል ብርሃነ ተክሌ የኮሌጁ ዋና አዛዥ እንደገለፁት፡- ኮሌጃችን ሠልጣኞችን አብቅቶ በማውጣት አንጋፋ ከመሆኑም በላይ ለመከላከያ ተቋምም ዋነኛ ተልዕኮ እንዲሳካ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

ዋና አዛዡ በተጨማሪም ኮሌጁ ለሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን ለስቭል ማህበረሰቦችም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን በዚህም ተሸላሚ ለመሆን በቅቷዋል በማለት ኮሌጁ በዋናነት ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ገልጸዉ በመጨረሻም ለተመራቂዎች መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ተመኘተዋል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ም/መ/አለቃ ትግዕስት ገብሬና አበበ መኮንን እንዲሁም ሳጂን መክሊት ኤሊያስ እንደተናገሩት፡- ኮሌጁ ለተማሪዎች የሚያደርገው እገዛ የሚበረታታ ነው በተለይ ለሴት ተማሪዎች የሚሰጠው ትኩረት የሚያስደስት ነዉ ሲሉ ገልፀው በኮሌጁ ቆይታ በንድፈ ሃሳብና በተግባር ያገኙትን ክህሎት ለሀገርና ለህዝብ ጥቅምና ለዉጥ መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ ነን በማለት ተናግረዋል።

ከስቪል ተመራቂዎች መሀከል አንዱ የሆነዉ አዳነ አሰፋ፡- በትምህርት ቆይታ ብዙ ነገር ቀስሚያለሁ በተለይ በመከላከያ ተቋም ውስጥ መከባበር መተሳሰብና ከራስ በፊት ቅድሚያ ለሌላ መስጠትን አይቻለዉ እኔም ቀጣይ ይህን አደርጋለሁ ሲል ገልጻል።በመጨረሻም በትምህርት ቆይታቸው አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ማበረታቻ ሽልማት በመስጠት ፕሮግራሙን አጠናቀዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!