ለሠላም አስከባሪው ሰራዊት ሜዳሊያ ተበረከተለት

 

በሱዳን አቢዬ በሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ለተሰማራው ከአንድ ሺ ስምንት መቶ በላይ ለሆነው ለ7ኛ ዙር የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊትና ከተለያዩ ሀገራት ለተውጣጡ ኦብዘርቨርና ስታፍ አመራሮች ዱኩራ በሚገኘው የሰላም ማስከበር ካምፕ ውስጥ የሜዳሊያ ሽልማት ተካሄደ፡፡

በዝግጅቱ ላይ  በተባበሩት መንግስታት የአቢዬ የሀይል አዛዥ ሜ/ጄ ገብረ አድሃነ ወልደእዝጊን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊና ሲቪል አመራሮች በመገኘት የሜዳሊያ ሽልማቱን አበርክተዋል፡፡

በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀይል አዛዡ “ሀገራችን በአፍሪካ የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ የመሪነቱን ስፍራ ይዛ እንደምትገኝ” ጠቁመው “በተነጻጻሪ በአሁኑ ጊዜ በአቢዬ አካባቢ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑና ይህም ለውጥ የታየው በሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ የተሰማራው  ሰራዊታችን ቀን ከሌት እያደረገ ባለው ጥረት፤ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን መንግስታት ለሰላም ባላቸው ፍላጎትና ድጋፍ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ዋና ማዘዣ እያደረገ ባለው ድጋፍ” መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዝግጅቱ አስተባባሪና 19ኛ ከፍለ ጦር አዛዥ ኮ/ል አብርሃ ግርማይ “የግዳጅ ቀጠናው ለእንቅስቃሴ የማይመች ክረምትና ከፍተኛ የበጋ ሙቀት የሚታይበት ቢሆንም በአስቸጋሪ ሁኔታ በማለፍ ድል የማድረግ  ብቃት ያለው ሰራዊታችን የተሰጠውን ተልዕኮ በአኩሪ ሁኔታ እየተወጣ” እንደሚገኝ ገልጸዋል “በሜዳሊያ ስነ ስርዓቱ ላይ የ19ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ፤ የአየር ዩቲሊቲ ዩኒት፤ቀላል መሀንዲስ፤ ሁለገብ ሎጂስቲክ፤ ፈጣን ተነቃናቂ ኮማንዶ ፤ ታንከኛና መድፈኛ ክፍሎች መሳተፋቸውና ክፍሎች ከግዳጃቸው በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በመስራት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውል በማድረግ ለህዝቡ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል  ብለዋል፡፡

በሜዳሊያ ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ወታደራዊ ትዕይንቶችና የሀገራችንን ባህል የሚያሳዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችም ቀርበዋል፡፡

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!