"ሰባተኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን በዓል አከባበር የታለመለትን ዓላማና ግብ ያሳካ ነበር" የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

 

ሰባተኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን በዓል አከባበር የታለመለትን ዓላማና ግብ ያሳካ እንደነበር የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለፁ፡፡

ኢንጂነር አይሻ መሀመድ  የመከላከያ ሰራዊት ቀን አከባበር አስመልክቶ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ  ለሰባተኛ ጊዜ የተከበረው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን ሰራዊቱንና ህብረተሰቡን ያቀራረበ፤ የሰራዊቱን ተልዕኮ የመፈፀም ብቃት ያሳየና ለቀጣይ ተልዕኮ ጠቃሚ ግብዓት የተገኘበት  ሆኖ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ  አክለውም ህገ-መንግስታዊ ታማኝነታችንንና ህዝባዊ ባሕሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ተቋማዊ ለውጥ እናስቀጥላለን በሚል መሪ ቃል ለሰባተኛ ጊዜ የተከበረው በዓሉ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ስኬታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ዝግጅቶች በመከላከያ ደረጃ  በሁሉም የሰራዊት ክፍሎች ስኬታማ በሆነ መልኩ መከበሩን አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትሯ ለበዓሉ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱት ለኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፤ለአዳማ ከተማ ህዝብና ለከተማው አስተዳደር እንዲሁም ለኢፌዴሪ አየር ሃይል  በመከላከያና በራሳቸው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

መከላከያ  የሪፎርም ስራውን ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተገበረ ይገኛል ያሉት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በህገ-መንግስቱ በተቀመጡት መርሆዎች መሰረት የሰራዊቱን የብሄር  ተዋዕፆ ሚዛናዊ ለማድረግ ከላይ ወደታች ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝና ይህም በመቶ ቀን የዕቅድ አፈፃፀም ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!