የሠራዊቱ የልማት ኃይልነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ

 

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱ ዋነኛ የልማት ደጋፊ ኃይል ሆኖ እንዲቀጥል ሁለንተናዊ ዝግጅቶች ማድረግና ተሳትፎውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማሳደግ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ።

ክቡር ፕሬዚዳንቱ ይህን የገለፁት የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክቶሬትና የሰሜን ዕዝ በመቀሌ ከተማ ሰማዕታት አዳራሽ ባዘጋጁት የአዲስ ዓመት በዓል ላይ ነው።

ክቡር ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ንግግራቸው የልማት ሥራዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ እንደ አንድ ሰው ሆኖ መረባረብ ይገባዋል ብለዋል።

በዚህ ረገድም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ልማት ለማስቀጠል የሚያስችሉትን ሠላም የማረጋገጥ ሁለንተናዊ ዝግጅቱን ማሳደግ እንደሚገባው ተናግረዋል።

በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ተቋማዊ አሰራር በተጠናከረ መንገድ መገንባት እንዳለበትም ዶክተር ሙላቱ አስረድተዋል።

በዚሁ የአዲስ ዓመት ዝግጅት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እሴቶቹን ተላብሶ በተወጣቸው ተልዕኮዎች በህዝብ ተወዳጅና ምስጉን ሠራዊት መሆን ችሏል ብለዋል።

ሠራዊቱ የተሳተፈባቸውን የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች በብቃትና በህዝባዊነት መንፈስ መፈፀሙ የሀገርን መልካም ገጽታ በመገንባት የአምባሳደርነት ሚናውን እየተወጣ እንዳለም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ገልፀዋል።

“ሀገሪቱ በሁሉም መመዘኛ የሚያኮራ ሠራዊት አላት “ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ያስመዘገበችው የልማት ዕድገት በሠራዊቱ ተጋድሎ ጭምር የተገኘ ውጤት  እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢፌደሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ደንብና መመሪያን ባህል አድርጎ መሥራትና አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ኤታማዦሩ በዚሁ ንግግራቸው በአዲሱ ዓመት መሻሻል የሚገባቸውን በመፈተሽና እንዲሻሻል በማድረግ፣ እንዲሁም በአዲስ መልክ በማዘጋጀት አሰራርና መመሪያን ለመተግበር ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።

ሠራዊቱ ህገ- መንግሥታዊ ግንዛቤው ከፍ ያለ፣ እሴቶች የተላበሰ ቆራጥና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጁነቱ የተሟላ ለማድረግ የተጀመረው የሪፎርም ሥራ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ጄኔራል ሰዓረ፤ ጦርነትን መግታት የሚያስችል ጦርነትም ከተከሰተም በአነስተኛ ኪሳራ የጠላትን የማድረግ አቅም ማወክና ማሸነፍ የሚያስችል ቁመና መያዙን አስረድተዋል።

የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ሜ/ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የበዓሉ ዓላማ ሠራዊቱ ከህዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሆነም ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተከሰቱትን የፀጥታ ችግሮች በማስወገድ የተፈጠረውን ሠላም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሆነም ዋና አዛዡ ገልፀዋል።

ዕዙ በአዲሱ ዓመት የያዛቸውን ዕቅዶች ለማሳካት በየደረጃው ያለ አመራርና አባል አውቆት ወደ ተግባር ይሸጋገራል ያሉት ሜ/ጄኔራል ጌታቸው፤ ዕዙ ህገ-መንግሥታዊ ተልዕኮውን ለመፈጸም በላቀ ብቃትና በጠንካራ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በበዓሉ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሰሜን ዕዝ ያለፉት ዓመታት የግዳጅ አፈጻጸም፣ የዝግጁነትና የልማት ሥራዎችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በእለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ በትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ተመርቆ ተከፍቷል። በእንግዶቹም ተጎብኝቷል።

በበዓሉ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ በሠራዊቱ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ሲያገለግሉ የነበሩና በጡረታ የወጡ ከሠራዊቱ ወታደራዊ መሪዎች፣ ከሠራዊቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች የተጋበዙ የሠራዊት አባላት የተገኙ ሲሆን፤ የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችና አዝናኝ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!