የመከላከያ ፋይናንስ እቅድ አፈፃፀም ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ

 

የመከላከያ ፋይናንስ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበረ ተገለፀ።

ይህ የተገለፀው በመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች ክበብ በተካሄደው የ2010 በጀት ግምገማ ላይ ነው።

የመከላከያ ፋይናንስ ሥራ አመራር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት አምባሳደር ሌላአለም ገብረዮሐንስ እቅዱን መሠረት አድርጎ በማሰራት፣ ያልታቀዱ ግዢዎችን በማስቀረት የዓመት እቅድ አፈፃፀማቸው ውጤታማ እንደሆነ ገልፀው፤ ለተቋሙ የተመደበ ጥሬ ገንዘብ ወደ ልዩ ልዩ ንብረትና ትጥቆች ሲቀየር ማንኛውም የሠራዊት አባላት በባለቤትነት ስሜት ጥንቃቄና እንክብካቤ በማድረግ በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል።

የመከላከያ ፋይናንስ ሥራ አመራር ሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሲሳይ በበኩላቸው፤ ለሠራዊቱ ቀለብና ደመወዝ እስከ መጨረሻ ምሽግ በማዳረስ የተለያዩ ግዢዎች በመፈጸም የሠራዊቱን ፍላጎት በማሟላት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለሠራዊቱ ወትሮ ዝግጁነት የሚያስፈልጉ ግዢዎችን በወሳኝ መልኩ በመፈጸም በየ6ወሩ  ግምገማ በማካሄድ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የሥራ አፈፃፀሙ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

ሠራዊቱ የሠላም ማስከበር ተልዕኮውን አጠናክሮ ቀጥሏል

 

የዩኔስፋ ጠቅላይ መምሪያ እጀባ ዩኒት የ10 ወር ግዳጅ አፈጻጸም፣ የሜዳሊያ በዓልና አዲስ የተመደቡ የዩኔሴፋ ከፍተኛ አመራሮች የትውውቅ ፕሮግራም ተካሄደ።

በፕሮግራሙ ላይ የዩኔስፋ የበላይ ጠባቂ ተወካይና ኃይል አዛዥ የሆኑት ሜጄር ጄኔራል ገብረ አድሃና የተገኙ ሲሆን፣ በ10 ወር ግዳጅ አፈጻጸም የላቀ ተሳትፎ ለነበራቸው አባላት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ሠራዊታችን በተሰማራበት ግዳጅና ቦታ ሁሉ ሀገሩን ስለሚያስብ ተደራጅቶ ስለሚሰራ ግዳጁን በጀግንነትና በውጤታማነት እንዲወጣ አስችሎታል ብለዋል።

የዩኔስፋ ጠቅላይ መምሪያ እጀባ ዩኒት ሻለቃ ዘመዱ ደሱ በበኩላቸው ዩኒቱ ለጠቅላይ መምሪያው ተልዕኮዎች ስኬት ደጋፊ  የሆኑ የተለያዩ ግዳጆች ያሉት መሆኑን ጠቁመው በግዳጅ አፈጻጸም ሂደቱም ውጤታማ ተግባር አከናውነዋል ብለዋል።

ከጠቅላይ መምሪያው ድጋፍ ሰጪ ዩኒት ጋር በተያያዘ አባላቱ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎና አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለታላቁ ህዳሴ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ ያዘጋጀውን የቶንቦላ ሎተሪ በመግዛት ድጋፍ አድርገዋል ።

በዩኔስፋ ጠቅላይ መምሪያ እጀባ ዩኒት አዛዥ ሻለቃ ዘመዱ እንደተናገሩት፤ የዩኒት አባላቱ በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን ልማት በመደገፍ በራስ ተነሳሽነት ካጠራቀሙት የኪስ ገንዘብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያነት የተዘጋጀውን የቶምቦላ ሎተሪ በመግዛት 1ሺህ 510 የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ በቀጣይም ሀገራዊና ተቋማዊ  ሚናቸውን ከመወጣት ጎን ለጎን የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የዩኒቱ አዛዥ አረጋግጠዋል ሲል ዜናውን ያደረሰን መ/አለቃ ክንፈ አስገዶም ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን አብዬ ተሰማርቶ የነበረው የ16ኛ ሞተራይዝድ ሠላም ማስከበር ሻለቃ የተሰጠውን ግዳጅ ውጤታማ በሆነ መልኩ አጠናቆ መመለሱ ተነገረ።

በሁርሶ ኮንቲጀንት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የግዳጅ አፈጻጸሙን በማስመልከት ባካሄዱት ዓመታዊ ግምገማ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በሠላም ማስከበር ዋና መምሪያ የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ጠቅለው ክብረት፤ “ሞተራይዝድ ሻለቃው የተሰጠውን የሀገሩን አደራ ተረክቦ ተልዕኮውን በብቃት ማከናወኑን ገልጸው እንደቀደሞው ሁሉ በሀገር ውስጥ የሚሰጣችሁን ግዳጅም በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፈጸም ዝግጁነታችሁ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል” ብለዋል።

የ16ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ አዛዥ ኮሎኔል ተወልደ ሀጎስ በበኩላቸው፤ የሻለቃዋን የግዳጅ ቆይታ በማስመልከት እንደገለጹት ሞተራይዝድ ሻለቃው ቀጣናውን ከተረከበ በኋላ የአካባቢውን የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመቋቋም የሠላም ማስከበር ግዳጁን በውጤታማነት ፈጽሟል ማለታቸውን ሻምበል አሰፋ በለው ነው።

በተመሳሳይ ዜና በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚሰማራው 7ኛ የኃይል መከላከል ሞተራይዝድ ሠላም ማስከበር ሻለቃ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አሸኛኘት ተደረገለት።

በሠላም ማስከበር ዋና መምሪያ የሎጀስቲክ ስምሪት ክትትልና ድጋፍ መምሪያ ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በሽኝቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት መንግሥት በሚከተለው የወጪ ጉዳይ ፖሊሲ እና በፀጥታና ደህንነት ጉዳይ ላይ ያለው ጠቀሜታ አስተዋጽኦ መነሻ በማድረግ የጎረቤታችን የደቡብ ሱዳን ህዝቦችን ሠላም ለማስፈን ሠራዊቱ ውጤታማ የሠላም ማስከበር ተልዕኮውን በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ በመግለጽ ወደተልዕኮው ለሚሰማሩ ለ7ኛ የኃይል መከላከል  ሞተራይዝድ ሻለቃ ሠላም ማስከበር የሠራዊት አባላትም ሀገራዊ አደራቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወጡ ጄኔራል መኮንኑ አሳስበዋል። ዜናውን ያደረሰን ሻምበል አሰፋ በለው ነው።

በተያያዘ ዜና በደቡብ ሱዳን የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የ9ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ ደረጃ አንድ ሆስፒታል “ለቦር” ከተማ ማረሚያ ቤት የመድሃኒት ድጋፍ አደረገ።

የሆስፒታሉ ኃላፊ ሻለቃ ሀብቱ ገብረስላሴ እንደገለጹት በከተማዋ ማረሚያ ቤት በልዩ ልዩ ወንጀል ቅጣት የተበየነባቸው በርካታ እስረኞች ይገኛሉ፤ ሆኖም የህግ ታራሚዎቹ  የጤና እክል ሲገጥማቸው የከተማው ሪፈራል ሆስፒታል ነፃ ህክምና አገልግሎት ይሰጣቸው የነበሩ ቢሆንም ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ከሆስፒታሉ አቅም በላይ እንደሆነ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በአቅራቢያቸው ለሚገኙ የተለያዩ ሀገራት የሠላም አስከባሪ ኃይሎች እርዳታ እንዲደረግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።  ይህን ጥያቄያቸውን እና ችግራቸውን የተረዳው የሞተራይዝድ ሆስ ፒታል ልዩ ልዩ ዓይነት መድሃኒቶችን በመ ለገስ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን አረጋግጧል ሲሉ ተናግረዋል። ዜናውን ያደረሰን የሻለቃዋ ሪፖርተር ም/መ/አለቃ ማርየ ፀሀይ ነው።

በተመሳሳይ ዜና በአብዬ ሠላም ማሰከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የ6ኛ ዙር ዩቲሊቲ ሄሊኮፕተር ዩኒት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተልዕኮ አፈጻጸሙ ስኬታማ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሠላም ማስከበር ግዳጁን ተቀብሎ በአግባቡ እየተወጣ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት  የዩኔስፋን ተልዕኮ ቀጣይነት ባለው መንገድ በማረጋገጡ በቀጣናው አስተማማኝ ሠላም ሰፍኗል ተባለ።

የዩኔስፋ የበላይ ጠባቂ ተወካይና ኃይል አዛዥ ክቡር ሜጄር ጄኔራል ገብሬ አድሃና በሱዳን አብዬ ዲፍራ የ17ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ መሰብሰቢያ አዳራሽ በመገኘት ከሚሰሪያ የሠላም ኮሚቴዎች፣ የጎሳ መሪዎችአሚሮችና አመራሮች ጋር ባደረጉት በአካባቢው ስላለው የፀጥታ ሁኔታ፣ የመረጃ ልውውጥና የትውውቅ መድረክ ላይ ነው የተገለፀው።

ጄኔራል መኮንኑ እንደተናገሩት፤ ሠራዊታችን በተባበሩት መንግሥታት ህግና ደንብ እንዲሁም ወታደራዊ ዲሲፕሊን ግዳጁን በተገቢው መንገድ እየተወጣ እንደሚገኝና በቀጣይነትም ሠላም  ከሌለ የህዝቦች ህይወት ስለሚናጋ ሊገጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶችን ቅድሚያ በመከላከል  በጋራ ለመወያየት የሚያስችል መድረክ በመፍጠር እየተመካከሩ ለሠላም እንዲሰሩ ኮሚቴዎቹ አሳስበዋል።

የዩኔስፋ  ምክትል ኃይል አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ድሪባ መኮንን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ግዳጁን ሲፈጽም ተልዕኮው ሠላም ማስከበር ብቻ ሳይሆን እንደጎረቤት ሀገር በማሰብ ሌት ተቀን 24 ሰዓት በመስራት በአካባቢው የሠላምና የፀጥታ ጥበቃ ሰራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሠላም ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል ሲል ዜናውን ያደረሰን መቶ አለቃ ቀለምወርቅ አዳነ የሞተራይዝድ ሻለቃዋ ሪፖርተር ነች።

በሠራዊቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች  ሽልማት ተሰጠ

 

በልዩ ልዩ የሠራዊቱ ክፍሎች በ2010 ዓመት በጀት አፈጻጸም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ክፍሎች ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተበረከተላቸው።

በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ የ33ኛ አባይ ክፍለ ጦር በ2010 በጀት ዓመት በሥራ አፈጻጸማቸው ውጤታማ የሆኑ ሻምበሎችና ሬጅመንቶች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በዕለቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው ሽልማቱን የሰጡት የ23ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አድማሱ አለሙ እንደተናገሩት፤ በቀጣይ የሥራ ሂደታቸው ከዚህ በተሻለ ውጤታማ እና የተመቻቸ መሆን አለበት ብለዋል።

በተጨማሪም በዓመቱ ውስጥ ሙሉ የሰው ኃይላቸውን አቅበው የቆዩ ሻምበሎችና የስታፍ ክፍሎች ሽልማት እንደተበረከተላቸው የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ፲ አለቃ አዛናው ፀጋየ ዘግቧል።

በተያያዘ ዜና በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ በወጋገን 7ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የ2ኛ ሬጅመንት ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ተከትሎ አመራር እና አባላት ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት እንደፈጠረላቸው ተገለጸ።

የሬጅመንቱ አዛዥ ኮሎኔል ልዑል ታደሰ በዓመቱ የግንባታ ሥራችን በሚገባ አጠናክረን በመቀጠላችን በየደረጃው የሚገኝ የሬጅመንቱ አመራር እና አባላት አቅማችንን አጠናክረናል ማለታቸውን የሬጅመንቱ ሪፖርተር መ/ወ/ር ግዛቸው ጣሴ ያደረሰን ዘገባ ያስረዳል።

በተመሳሳይ ዜና በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ 8ኛ ማዕበል ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የ87ኛ መድፈኛ ሬጅመንት በ2010 ዓ.ም ግምገማ መነሻ በማድረግ ውጤታማ የግዳጅ አፈጻጸም ለነበራቸው ሻምበሎች እና የመቶዎች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጠ።

በዕለቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ለሰው ሀብት ልማት ኮሎኔል ሀሰን አብደላ የሬጅመንታችሁ የሠራዊት አባላት የሀገራችሁን ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ ውጤታማ የሆነ የግዳጅ አፈጻጸም ማከናወን አለባችሁ ማለታቸውን የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ሻለቃ መጋቢ ባሻ ባየ ወርቅነህ ዘግቧል።

በሌላ በኩል በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ 332ኛ ሬጅመንት በ2010 ዓ.ም በጀት አፈጻጸማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የመቶዎችና ሻምበሎች ሽልማት እና የምስክር ወረቀት ተበረከተላቸው።

በዕለቱ የተገኙት የሬጅመንቷ ምክትል አዛዥ ለሎጀስቲክስ ሌተና ኮሎኔል ፋንታዬ ወልዱ እንደተናገሩት በዓመቱ በርካታ ሥራዎችን  መስራት የተቻለው የሥራ ተነሳሽነታቸውና አፈጻጸማቸው ውጤታማ ስለሆነ ነው ማለታቸውን የሬጅመንቱ ሪፖርተር ፶ አለቃ ወንድም ገዛሁ አውላቸው ዘግቧል።

በሠራዊታችን የተለያዩ ክፍሎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችና የማዕረግ ዕድገት ተሰጠ

 

በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ የ22ኛ ክፍለ ጦር የላቀ የሥራ አፈጻጸም ያስመዘገቡና የመቆያ ጊዜያቸውን የሸፈኑ ባለሌላ ማዕረግ ተሿሚዎችን አሰልጥኖ አስመረቀ።

የ22ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል ተክለ ፍስሃ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በመገኘት ለተሿሚዎች ማዕረግ ካለበሱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “የዛሬ ተሿሚዎች በነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ለማዕረግ ዕድገት ብቁ ናቸው በሚል ለአመራርነት የሚያበቃ ሥልጠና ተከታትለው ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ማዕረግ ማግኘት የላቀ ሥራና ኃላፊነት የሚያመጣ መሆኑን ተገንዝበው ወደ የሬጅመንታቸውን ሲቀላቀሉ በአገኙት አቅም በመስራት ግዳጃቸውን በአግባብ ሊፈጽሙ ይገባል” ብለዋል።

የማዕረግ ዕድገት ካገኙት መካከል ጥቂቶቹ በሰጡት ተመሳሳይ አስተያየት፤ በነበራቸው የማዕረግ ሥልጠና ቆይታ ለአመራርነት የሚያበቃ ግንዛቤ መያዛቸውን ጠቅሰው ቀጣይ ለሚሰጣቸው ግዳጅ በበለጠ ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን እንደገለጹ የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ፲አለቃ አብርሃም ጥላሁን ዘግቧል።

በተመሳሳይ ዜና በሰሜን ዕዝ የ20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር የበታች ሹሞች ለአንድ ወር ሲሰጥ የቆየውን ወታደራዊ ሥልጠና አጠናቅቀው ተመረቁ።

በክብር እንግድነት የተገኙት የ20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ገብረእግዚአብሄር ገብረሊባኖስ በንግግራቸው፤ ተመራቂዎች በቆይታችሁ የቀሰማችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለምትመሩት አሃድ አርአያ መሆን ይጠበቅባቸኋል ካሉ በኋላ አሀዱ ወታደራዊ ዝግጁነቱን ተጠብቆ እንዲቀጥል የተሿሚዎች አቅም ተደማሪ ስለሆነ የተሰጣችሁን ሥልጠና ተጠቅማችሁ በላቀ የሥራ መንፈስና ኃላፊነት ግዳጃቸውን እንዲፈጽሙ አሳስበዋል።

የክፍለ ጦሩ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ክትትል ዴስክ አስተባባሪ ሻምበል ሲሳይ ተሾመ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች በሥልጠናው የካበተ ዕውቀት የተሻለ  አቅም እንዲፈጥሩ ያስቻለ በመሆኑ በቀጣይ ሊያሰራ የሚያስችላቸውን ክህሎት መጨበጥ ችለዋል ማለታቸውን የዘገበው የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ም/መ/አለቃ ስንታየሁ ግዛው ነው።

በሌላ በኩል በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ የ31ኛ ክፍለ ጦር ለ2 ወራት በጓድ አመራርነት ሥልጠና የወሰዱ አባላት ተመረቁ።

የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ለሎጀስቲክስ ኮሎኔል ሱራ ከድር ተመራቂዎችን ማዕረግ ካለበሱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ተመራቂዎች በሥልጠና ቆይታችሁ ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ህዝብና መንግሥት የሰጣችሁን ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመጠበቅ ኃላፊነት በአግባቡ ልትወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የክፍለ ጦሩ ሥልጠና ክፍል ኃላፊ ሻለቃ አለማየሁ ረታ የሥልጠና ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ሠልጣኞቹ በነበራቸው ቆይታ የሚሰጡትን ትምህርቶች ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል በተመደቡበት ክፍል ሊያሰራቸው የሚያስችላቸውን ዕውቀት ያገኙ ሲሆን በቀጣይ በሚሰጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እራሳቸውን የበለጠ ማብቃት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ዘገባው የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ፲ አለቃ ኤፍሬም አድማሱ ነው።

በተያያዘ ዜና በ23ኛ ክፍለ ጦር ለሦስት ወራት ያህል ወታደራዊ ሥልጠና ሲሰለጥኑ የቆዩት ተሿሚዎች ተመረቁ።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የትከሻ ምልክት ያለበሱት የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል እያሱ ነጋሽ ባሰሙት ንግግር “ከሥልጠናው ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደተግባር በመቀየር ተተኪ አመራር መሆን ይጠበቅባቸዋል ካሉ በኋላ በምታደርጉት ማንኛውም የግዳጅ አተገባበር ላይ የተሻለ  አቅም በመፍጠር ወታደራዊ ብቃታችሁን በማሳደግ ለምትመሩት ክፍል አርአያ መሆን አለባችሁ” ብለዋል።

የክፍለ ጦሩ ሥልጠና ዴስክ አስተባባሪ ሌተና ኮሎኔል እንደሻው ወርቅነህ በበኩላቸው፤ የሥልጠናው ዋና ዓላማ የተለያዩ ወታደራዊ ሳይንስ እና ተዛማጅ ሥልጠና አይነቶችን እንዲያውቋቸውና የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር ለተግባር ሥራቸው እንዲያከናውኑ መሆኑን የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ፶ አለቃ ፍሬዘር በርሁ ዘግቧል።

በተመሳሳይ ዜና በ33ኛ ክፍለ ጦር የማዕረግ ዕድገት ሥልጠና የሰለጠኑት ተሿሚዎች ተመረቁ።

የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ተክላይ ወ/ጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ ሠራዊቱ ተልዕኮውን በሚገባ በመረዳት የሀገራችን ሠላምና ልማት እንዲሰምር በርትቶ መሥራት እንዳለበት ጠቁመው፤ ህገ-መንግሥቱንና ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያስጠብቅ እሴቶችን በመላበስ ጠንክራችሁ መስራት ይኖርባችኋል ብለዋል።

የክፍለ ጦሩ ህብረት ዘመቻ ኃላፊ ሌተና ኮሎኔል መላኩ ደመላሽ በበኩላቸው  ሠልጣኞች በሥልጠና ቆይታቸው ጥሩ አቅም መፍጠር መቻላቸውን ገልጸው ሥልጠናው የታቀደው ግብ ላይ መድረስ መቻሉን መናገራቸውን የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ፲ አለቃ አዛናው ፀጋዬ ዘግቧል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!