ሬጅመንቷ የምሥረታ በዓሏን አከበረች

 

የ23ኛ ሬጅመንት የሠራዊት አባላት አንደኛ ዓመት የምሥረታ በዓላቸውን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበሩ።

በዓሉ ሰሞኑን በተከበረበት ወቅት በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር ያደረጉት የሬጅመንቷ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሰፋ ብርሃኔ ሬጅመንቷ ህዝብና መንግሥት የሰጧትን ህገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በአስተማማኝ ብቃት ስትወጣ መቆየቷን ገልጸዋል።

ሬጅመንቷ በቀጣይነትለሚሰጧት ተልዕኮ ወታደራዊና ሥነ-ልቦና ዝግጁነት እንዳላት የጠቆሙት ዋና አዛዡ ለዚህም የሠራዊቱን ዝግጁነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በወታደራዊም ሆነ በተቋሙ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች የዝግጁነት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ከሬጅመንቱ አባላት መካከል በሰጡት ተመሳሳይ አስተያየት የምስረታ በዓል መከበሩ የተሻለ ታሪክ ለመስራት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል። በበዓሉ ላይ በቀረበው የጥያቄና መልስ ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ አባላት ሽልማት ተሰጥቷል።

 

የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጠ

 

በልዩ ልዩ የሠራዊቱ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።

በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ የ22ኛ ንስር ክፍለ ጦር ደረጃ ሁለት ሆስፒታል ከስታፍ ለተውጣጡ አባላት ለተከታታይ አራት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአቻ ለአቻ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናቀቀ።

በዕለቱ የተገኙት የ22ኛ ክፍለ ጦር ደረጃ ሁለት ሆስፒታል ጤና ማበልፀግና በሽታ መከላከል ኃላፊ ተወካይ መቶ አለቃ ገብረመስቀል እንደገለፁት፣ ስልጠናው እየጨመረ የመጣውን የኤች አይቪ ስርጭት ለመቆጣጠር ያለመ ነው ማለታቸውን የክፍለ ጦር ሪፖርተር ፲ አለቃ አብረሃም ጥላሁን ዘግቧል።

በተመሳሳይ ዜና በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ የ8ኛ ማዕበል ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ሆስፒታል ከሁሉም ሬጅመንቶችና ክፍለ ጦሮች እስታፍ ለተውጣጡ የሠራዊት አባላት በኤች አይቪ እና አባላዘር በሽታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ የአቻ ለአቻ ትምህርት ሰጠ።

በዕለቱ የተገኙት የ8ኛ ማዕበል ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ደረጃ ሁለት ሆስፒታል በሽታ መከላከል ኃላፊ ተወካይ መጋቢ ፶ አለቃ አብረሃም ማቲዎስ እንደገለፁት የኤች አይቪ እና የአባላዘር በሽታ በሃገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣና በተለይም አምራች ዜጋ የሆነውን ወጣት በማጥቃት ሠራዊታችን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየተፈጠሩ ይገኛል ብለዋል።

የቫይረሱ መስፋፋት ዋነኛው መንስኤ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት የመፈፀምና ለበሽታው ትልቅ ትኩረት ባለመስጠት መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ሰልጣኝ የሠራዊት አባላት ስለ በሽታው አስከፊነት ያገኙትን እውቀት ለሠራዊቱ ማስተማር ይኖርባቸዋል  ማለታቸውን የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ሻለቃ መጋቢ ባሻ ባየ ወርቅነህ ዘግቧል።

በተያያዘ ዜና በማዕከላዊ ዕዝ በ332ኛ ሬጅመንት ለግማሽ ቀን ያህል በአጠቃላይ በመመሪያና ደንብ፣ በህገ- መንግስት ዙሪያ ትምህርት ተሰጠ።

የሬጅመንቷ ህግ አገልገሎት ኃላፊ ፶ አለቃ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ መድህን እንደገለፀው የህግ ትምህቱ በሬጅመንቱ ከወንጀል እና ወንጀል ነክ ጉዳዮች ላይ የፀዳ ሠራዊት ለመገንባት እና የተሰጠውን ህገ- መንግስታዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ያስችላል ብለዋል።

ማንኛውም የሠራዊት አባላት ከህግ ተላልፎ እንዳይገኝ እና ተላልፎ ከተገኘም በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን መገንዘብ የሚያስችል ትምህርት በወር አንድ ጊዜ ይሰጣል በማለት መግለፃቸውን የሬጅመንቱ ሪፖርተር ም/፲አለቃ ፍቅር ተገኝ ዘግቧል።

በተያያዘ ዜና በባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ የ8ኛ ማዕበል ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የህግ አገልግሎት የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ ባለ ሌላ ማዕረግተኞች የሠራዊት አባላት በህገ- መንግስቱና በወንጀል ህጎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጠ።

ትምህርቱን የሰጡት የህግ አገልገሎት ኃላፊ ተወካይ ፶ አለቃ ተስፋሁን ደያስ እንደተናገሩት ህገ- መንግስታችን የሃገራችንን ብሄር- ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዕኩልነትና የመፈቃቀድ አብሮ የመኖር መብትን ያስከበረ የሃይማኖት፣ የመቻቻል ብዛሃነትን ያሰፈነ ህገ- መንግስት መሆኑን ጠቅሰው፣ የህገ- መንግስቱንና ሃገሩን ሉአላዊነትና ዳር ድንበሩን ለማስከበር የተሰለፈው ሠራዊታችን ህጎችን ጠንቅቆ በማወቅ ወንጀሎች እንዳይከሰቱ የቅድመ መከላከል ሥራዎች በመስራት ጤናማና በዲሲፒሊን የታነፀ ዘመናዊ ሠራዊት በመገንባት ሁሉም አመራርና አባላት የተሰጠውን ሃገራዊና ተቋማዊ ተልዕኮ በተገቢው መንገድ መወጣት አለበት። ከአካባቢው ሲቪል ማህበረሰብ ጋር ጠንካራ የሆነ ግንኙነት በመፍጠር ወትሮ ዝግጁነቱን በማጠናከርም የሚሰጠንን ግዳጅ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመወጣት ዝግጁ መሆን አለበት ማለታቸውን የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ሻለቃ ባሻ ባየ ወርቅነህ ዘግቧል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!