በጤና ሙያ የሠለጠኑ አባላት ተመረቁ

 

በደቡብ ምሥራቅ ዕዝ የ2ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ሆስፒታል ለአራት ወራት ያሰለጠናቸውን የመጀመሪያ ደረጃ ጤና  ሙያተኞችን አስመረቀ።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች ሰርተፍኬት በመስጠት የሥራ መመሪያ ንግግር ያደረጉት የ2ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ኃይለሥላሴ አሰፋ እንደተናገሩት፤ ሆስፒታሉ እነዚህ ሠልጣኞች ተቀብሎ ጤና መከላከልን መሠረት ያደረገ ሥልጠና የሰጠበት ዋና ዓላማው በክፍሉ ውስጥ ያለውን የሙያተኞች ክፍተት ለመሙላት መሆኑን አውስተው ሠልጣኞቹ በገቡት ቃለ መሃላ መሠረት አሃዳቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የ2ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ተወካይ ም/መ/አለቃ እልፋለም ሱራፌል እንደገለጹት፤ በዕዝ ጤና ዳይሬክቶሬት ባወጣው የመመልመያ መስፈርት መሠረት ከሁሉም ሬጅመንቶችና ከስታፍ ክፍሎች የተውጣጡ  የጤና ሙያተኞችን በመቀበል ለአራት ወራት ሥልጠናውን ብቁ በሆኑ በሆስፒታሉ ሲኒየር ሙያተኞች አማካኝነት ትምህርቱን በንድፈ ሀሳብና በተግባር ተከታትለዋል ካሉ በኋላ ተመራቂዎቹ የመጀመሪያ የጤና  ሙያ ትምህርት ብቻ ሣይሆን መሠረታዊ የማከምና በሽታን የመከላከል፣ የመጀመሪያ ህክምና አሰጣጥና ለአደጋ ጊዜ አፋጣኝ እርዳታ እንዲሰጡ ተደርጎ የሰለጠኑ መሆኑን ገልፀዋል።

ከተመራቂዎች መካከል አንደኛ የወጣው መ/ወ/ር ሳሙኤል ሽፈራውና ሁለተኛ ደረጃ የወጣችው ም/!አለቃ ሲሳይነሽ አይቸው በሰጡት ተመሳሳይ አስተያየት፤ ትምህርቱን የተከታተልነው ጥሩ ልምድ ባላቸው ሲኒየር ነርሶች በመሆኑ በንድፈ ሀሳብም ይሁን በተግባር የተሰጠንን ሥልጠና ወደ ተግባር በመቀየር ለወደፊት በክፍላችን ለሚሰጠን ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።

ሠራዊቱ ለማህበረሰቡ ድጋፍ አደረገ

 

የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሃገራችንን ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር ከወር ደመወዛቸው በማውጣት ለአካባቢውን ነዋሪዎችና አሳዳጊ ለሌላቸው ተማሪዎች  ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለፀ።

የ333ኛ ሬጅመንት የሠራዊቱ አባላት በአካባቢው ለሚገኙ አቅመ ደካማ ቤተሰቦች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

የ333ኛ ሬጅመንት ዘመቻ ዴስክ አስተባባሪ ሻለቃ ሀብቱ ካሳ እንደተናገሩት፣ “ከራስ በፊት ለህዝብና ለሃገር” የሚለውን የተቋሙን እሴት በመላበስ የተደረገ በጎ ተግባር ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንዳለ ማሳያ መሆኑን ገልፀው እንዲህ አይነቱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

እገዛ ከተደረገለላቸው ግለሰቦች መካከል አቶ አለምነው መኮንን እና ወ/ሮ ጉለቴ ገ/ስላሴ በሰጡት ተመሳሳይ አስተያየት፣ ሠራዊቱ ከዚህ በፊትም ከጎናቸው እንደነበሩ ጠቁመው በተደረገላቸው ድጋፍ ለሠራዊቱ ታላቅ ክብር እንዳላቸው ገልፀዋል። ዘገባውን ያደረሰን የሬጅመንት ሪፖርተር ፲አለቃ ቃኘው ካሳሁን ነው።

በተመሳሳይ ዜና የ20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር የሠራዊት አባላት በግዳጅ ቀጣናው ለሚገኙ አሳዳጊ ለሌላቸው ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተገለፀ።

በዕለቱ የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ገብረ እግዛአብሔር ገብረ ሊባኖስ ባሰሙት ንግግር፣ ወላጆቻቸውን በልዩ ልዩ አውደ ውጊያዎች በማጣታቸው ምክንያት እንግልት እንዳይደርስባቸው በማሰብ ለ11 ተማሪዎች በጥሬ ገንዘብና በቁሳቁስ ከ19 ሺህ ብር በላይ በበጀት ዓመቱ ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ታዳጊዎች መካከል ተማሪ ሠላም መስፍን እና ምህረት ሾሌ በሰጡት ተመሳሳይ አስተያየት፣ ሠራዊቱን እንደ ወላጆቻችን የምናየው ስለሆነ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል ካሉ በኋላ አሁንም ትብብራቸው ስላልተለየን እናመሰግናለን  ማለታቸውን የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ም/መ/አለቃ ስንታየሁ ግዛው ዘግቧል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!