የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የሎጀስቲክስ ድጋፍ ያጠናክራል

 

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የሎጀስቲክስ  አቅርቦትን ለማሳደግ የሚረዳ ወርክ ሾፕ አካሄደ።

በወርክ ሾፑ ላይ የተገኙት ብ/ጄኔራል ከበደ ረጋሳ የመከላከያ ሰላም ማስከበር  መምሪያ የሎጀስቲክስ ዝግጅት ስምሪት መምሪያ ኃላፊ እንደተናገሩት፤ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ለሠራዊቱ እንዴት ሎጀስቲካዊ ድጋፍ መስጠት እንዳለበት ገለፃ  አድርገዋል። ሀገራችን ከምስራቅ አፍሪካ ሃገሮች ጎን በመሰለፍ ከፍተኛ ስራ እየሰራች ትገኛለች። በኢኮኖሚ ፣ በዲፕሎማሲ፣ ሃብት በማዋጣትና የሚዋጣውን ሃብት በህግና በመመሪያ መሰረት በመጠቀም ትልቅ ስራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ጄኔራል መኮንኑ አክለውም፣ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ትልቅ ሚና ያላት ሃገር ናት።  ለስኬቱና ለቀደምትነቷ መሰረቱ ህዝቧና አይበገሬው ሠራዊቷ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዶክተር ኮሎኔል አቻሜለሽ ክፍሌ በአፍሪካ ህብረት ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ዲፓርትመንት የሜዲካል ፕላነርነት ባለሙያ በበኩላቸው፣ ሎጀስቲክስ ለአንድ ሃገር መከላከያ የጀርባ አጥንት ነው። ስለሆነም አቅርቦቱ ተመጣጣኝና ውጤት የሚያስገኝ መሆን አለበት። በአፍሪካ ህብረት እየተሰሩ ላሉ ስራዎች በሎጀስቲክስ ግዳጅ አሰጣጥ፣ በሰላም ማስከበር ዙሪያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሻምበል አለማየሁ ደምሴ የሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ እቅድና ሪፖርት ክፍል ኃላፊ በበኩላቸው ከምስራቅ አፍሪካ ሃገሮች ጋር ውይይት በማካሄድ የስራ ልምድ  ልውውጥ መገኘቱን በሎጀስቲክስ ደረጃ ልምድ ያላቸው አመራሮች የተሳተፉበት  በመሆኑ የስራ ፖሊሲ አካሄድና ለቀጣይ ስራ አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር በእቅዳችን መሰረት ውጤታማ ስራ እንሰራለን ብለዋል።

ግንዛቤ የሚፈጥሩ ውይይቶች ተካሄዱ

 

በሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ዘውዱ በላይ የተመራው ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ልዑክ ቡድን ከፈንቅል ክፍለ ጦር የሠራዊት አባላት ጋር ውይይት አደረገ።

ውይይቱ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሠላም ስምምነትን መነሻ ያደረገ ነው። ከዚህም በመነሳት የሠራዊቱ የድንበር ጥበቃና ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በውይይቱ በሰፊው ማየት ተችሏል።

የዕዙ ዋና አዛዥ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ በኢትዮ-ኤርትራ መካከል የተጀመረው የሠላም፣ የአንድነትና የዕድገት ስምምነት ለሠራዊቱም ያለው ጠቀሜታ የጎላና ለሀገርም ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ስምምነቱን በመደገፍ እንደ ሠራዊት የሚጠበቅብንን ሥራ በጋራ እንሰራለን ብለዋል ሲል የዘገበልን የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ፲አለቃ መላኩ ገብሬ ነው።

በተመሳሳይ ዜና የደቡብ ምሥራቅ ዕዝ የስታፍ አባላትና አመራሮች የዕዙ  የሀገር ውስጥና የሀገር ውጭ ግዳጅ አፈጻጸም ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የዕዙ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል በላይ ስዩም፤ “ዕዙ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በሚወጣው ግዳጅ የላቀ ውጤት በማምጣት የሚያስመሰግን ሥራ ሰርቷል። ይህም ለቀጣይ ሥራ ትልቅ አቅም ነው። አመራሩና አባሉ በመቀራረብ ከዚህ የበለጠ ጠንክሮ መስራት ይገባዋል” ብለዋል።

ጄኔራል መኮንኑ አክለውም፤ ሠራዊቱ ውስጣዊ ደህንነቱንና የአስተሳሰብ ጤንነቱን አስጠብቆ ከህዝብ ጎን በመሆን ህዝቡን ማገዝና ማገልገል ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል። ዘገባው የዕዙ ሪፖርተር ፶አለቃ አወል መሀመድ ነው።

በተያያዘ ዜና በአየር ኃይል ሲኒማ አዳራሽ በቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኙ ከሠራዊቱ በልዩ ልዩ ምክንያት ከተሰናበቱ አባላት ጋር ውይይት ተደረገ።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ናቸው።

ጄኔራል መኮንኑም በዕለቱ ባደረጉት ንግግር አባላቱ ከተቋሙ ሲቀነሱ  በታማኝነት የቻሉትን ሁሉ ከአገለገሉ በኋላ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት ላለው ለውጥም አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል። ችግሮችን በጋራ በመነጋገርና በመፍታት ለሀገር ሠላምና ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።  አባላቱ ላነሷቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል ስትል የዘገበችልን ም/፲ አለቃ ባንቺ ኃይሉ የአየር ኃይል ሪፖርተር ነች።

በተመሳሳይ ዜና በሰሜን ዕዝ  የ20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ላይም በመገኘት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የዕዙ ምክትል አዛዥ ለሰው ሀብት ብርጋዲየር ጄኔራል ከድር አራርሳ ናቸው። ጄኔራል መኮንኑም በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ሰዓት ሠራዊቱ ለሀገሪቱ ለውጥ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ የተሰጠውን ህገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ ብቻ መነሻ በማድረግ ለሚናፈሱት አሉባልታዎች ተገዥ ሳይሆን ህዝባዊነቱን ጠብቆ ግዳጅን መወጣት ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል። ዘገባውን ያደረሰን የክፍለ ጦሩ ሪፖርተር ም/መ/አለቃ ስንታየሁ ግዛው ነው።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!