መከላከያ የምህረት አዋጁን አፈፃፀም በተመለከተ መግለጫ ሰጠ

 

በሀገራችን ያለውን የለውጥ ሂደት ለማፋጠንና የፖለቲካ ምህዳርን ለማስፋት እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች አንዱ በሆነው  የምህረት አዋጅ በመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን የአፈፃፀም ሁኔታ አስመልክቶ የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማና የመከላከያ ህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ብርጋዲየር ጄኔራል ኪዱ አለሙ በጋራ መግለጫ ሰጡ።

በመግለጫው ከሠራዊቱ በልዩ ልዩ ጊዜያት የከዱ፣ የኮበለሉ እና ወታደራዊ የዲሲፕሊን ጥፋተኛ ተብለው ፍርዳቸው በሂደት ላይ ያሉና ተፈርዶባቸው በመከላከያ ማረሚያ ቤትና በፌዴራል ማረሚያ ቤት የሚገኙ የሠራዊት አባላት እንዲሁም በተለያዩ ወቅቶች የዲስፕሊን ችግር ኖሮባቸው ከሠራዊቱ የተሰናበቱ አባላት የዚህ አዋጅ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

አፈጻጸሙን አስመልክቶም ከሠራዊቱ የከዱ አባላት ከሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የመከላከያ ህግ ዳይሬክቶሬት በመቅረብ ሪፖርት እንዲያደርጉ እንዲሁም በክልል ከተሞችና በዞኖች የሚገኙ ደግሞ ከነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢያቸው በሚገኘው የብሄራዊ ተጠባባቂ ኃይል ጽ/ቤት በመቅረብ እንዲያመለክቱ በመግለጫው ተብራርቷል።

በዲስፕሊን ጥፋት ከሠራዊቱ ተሰናብተው የነበሩ አባላት አዲስ አበባ በሚገኘው በመከላከያ የሰው ሀብት ልማት ዋና መምሪያ ቢሮ እና በክልል የሚገኙ ደግሞ በአካባቢያቸው በሚገኙ የብሄራዊ ተጠባባቂ ኃይል ጽህፈት ቤት ቀርበው ማመልከት እንደሚገባቸው ተገልጿል።

ይህ አፈጻጸም ለ6 ወር የሚቆይ ሲሆን ከዛ ጊዜ አሳልፎ የሚመጣ ግን በራሱ ፍቃድ የአዋጁ ተጠቃሚ መሆን ያልፈለገ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።

የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ የሚሆኑት ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት ያሉት ብቻ  መሆናቸው ተገልጿል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!