የኢትዮ- ኤርትራ የሠላም ስምምነት በአህጉሩ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው

 

የኢትዮጵያና ኤርትራ ወንድማማች ህዝቦች ያሏቸው ተመሳሳይ እሴቶች ከጦርነት ይልቅ ሠላም፣ ከመራራቅ ይልቅ ተቀራርቦ በመልካም ጉርብትና ለመኖር ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ምክንያት ሆነዋል።

ሀገራቱ የጠብ ግድግዳ አፍርሰው የሠላምና ፍቅር ድልድይ ለመገንባት በየትኛውም ዓለም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ልዩነታቸውን ለማጥበብ ፍላጎት ወስነዋል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠላም የሌለበት የሁለቱን ሀገራት ፍጥጫ እንዲያበቃ የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል ለኤርትራም የሠላም ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል።

የኤርትራ መንግሥት ለሠላም ጥሪው በጎ ምላሽ በመስጠት ከፍተኛ ልዑኩን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ዶክተር አብይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ሠላም የማስፈን ሂደቱ ቀጥሏል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ወደ ኤርትራ ተጉዞ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ተፈራርሞ ከመጣ በኋላ ሰሞኑን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ጉብኝት አድርገዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በመካከላቸው የፈጠሩትን ሠላም የተባበሩት መንግሥታት ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የሚዲያ ተቋማት አድናቆታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

የሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች ለጠቅላይ ሚኒስትራችን በአስመራ፣ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ደግሞ በአዲስ አበባና ሃዋሳ ባደረጉት ደማቅ አቀባበል ለሠላም ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት አረጋግጠዋል።

ከ25 ሺህ የሚልቁ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ስምምነቱን ለማብሰር በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ሥነ- ሥርዓት ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር የሁለቱ ሀገራት የሠላም ስምምነት ለምሥራቅ አፍሪካ ብሎም ለአፍሪካ አህጉር በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱ ሀገራት ለጋራ ሠላምና ልማት እንደሚሰሩና በመካከላቸው የተፈጠረውን ሠላም ማንም ሊያደፈርሰው እንደማይችል አረጋግጠዋል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው የባከኑ ጊዜያትን ለማካካስና በጋራ ለመልማት በደማቁ የታየውን የህዝቦች መፈላለግ ለማስቀጠልና ለሁለቱ ሀገራት ሠላም በጋራ እንደሚሰሩ ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ከልብ መደሰታቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ “የታየውን የሠላም ተስፋ ማንም እንዲያጨናግፍብን አንፈቅድም “ ብለዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!