“ሠራዊቱ የሀገር ኩራት መሆኑን ማረጋገጥ    ይጠበቅበታል”

 

ሠራዊቱ የሀገር ኩራት መሆኑን ማረጋገጥ    ይጠበቅበታል

-የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

ሠራዊቱ መመሪያውን ተቀብሎ ተልዕኮውን እየፈጸመ መሆኑ ተገልጿል

 

ፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን በወታደራዊ ሙያው በመታገዝ ተጨማሪ ኪሳራ ሳይደርስ ሠላም በማረጋጋት የሀገር ኩራት መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ከሸኙ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ዛሬም በቀደመው፣ ባረጀው እና በማያስፈልገው ፋሽን በሚጓዙ ቡድኖችና ግለሰቦች ሳቢያ ህዝቦች ግጭት ውስጥ እየገቡ የሰው ህይወት እየጠፋ ይገኛል። ለእነዚህ ንጹሃን ዜጎች ህይወት መርገፍ በቀጥታ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ራቅ ብለው ክብሪት፣ ነዳጅ እና እንጨት የሚያቀብሉ ቡድኖችና ግለሰቦች ሚናቸው የጎላ እንደሆነ አሰታውቀዋል።

በየትኛውም የሀገራችን ቀጣና እያጋጠመ ያለውን የሠላም ችግር ለመቆጣጠር፤ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጣልቃ በመግባት ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ እና የሚያጠፋፋ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፍ ቡድንና ግለሰቦችን ለህግ በማቅረብ ሀገራዊ እና ህገ-መንግሥታዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ዶክተር አብይ አዘዋል።

“ሠራዊቱ ተልዕኮውን ሲፈጽም በተቻለ መጠን ተጨማሪ ኪሳራ እንዳይደርስ፣ ሙያዊ፣ ጥበባዊና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሥራ በመስራት፣ ህዝብ ሳይሞት፣ አካል ሳይጎድልና ንብረት ሳይወድም ሠላም የሚሰፍንበትን መንገድ በመፍጠር ሙያዊ ብቃቱን እንዲያሳይና ዳግም የሀገር ኩራት መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

“በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ብቻ ሳይሆን በተቀሩት የሀገራችን አካባቢዎች ህዝቦችን ከህዝቦች የሚያጋጩ ሁኔታዎች አሁን ለያዝነው የለውጥ ጉዞ የሚጠቅም አይደለም” ያሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ፤ ህዝቦች ተደምረው ታላቅ ሀገር መፍጠር እንጂ ወደ አናሳ ሃሳብ እየገቡ ህዝብን ማጋጨት ከታሪክ ፊት ከተጠያቂነት አያድንም” ብለዋል። አያይዘውም “የጥቂቶችን ክፉ ሃሳብ በርካቶች ካልሸመቱት የጥቂቶች ሆኖ ይቀራል” ያሉ ሲሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ግጭቶችን መከላከል ባይችል እንኳን ተባባሪ ሆኖ ባለመገኘት ለሠላም መቆም እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ፤ ሠራዊቱ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የተላለፈለትን መመሪያ ተቀብሎ ግጭት በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሠላም የማረጋጋት ተልዕኮውን እየፈጸመ መሆኑን አስታወቁ።

ሚኒስትሩ ከመከላከያ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት የመከላከያ ሠራዊቱ ፍጹም ገለልተኛና ሁሉንም ህዝቦች በሚያረካ መልኩ ከፖለቲካ ድርጅት ውግንና በፀዳ የኢትዮጵያ ህዝቦቿ አለኝታ ሆኖ ነው ተልዕኮውን እየተወጣ የሚገኘው።

“በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይቀለበስ የኢትዮጵያ ህዝቦች እየደገፉት ነው” ያሉት አቶ ሞቱማ በልዩ ልዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን እየፈጠሩ ያሉት፤ ለውጡን የማይደግፉ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች መሆናቸውንም ጠቁመዋል። የህዝብን ፍላጎትና ጥቅምን በኃይል ለመገደብ የሚደረግ ጥረትን በፅናት መከላከል የኢፌዴሪ መከላከያ ህገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በአጭር ጊዜ የተሰማራበትን ቀጣና በማረጋጋት ሠላም ለማንገስ ብቃት ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።

የሠራዊታችን ጣልቃ መግባት ጊዜያዊ መፍትሄ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው ዘላቂ መፍትሄው በህዝቦችና በክልሎች መካከል የሚካሄዱ የፖለቲካ ሥራዎች እና ውይይቶች ወደ መተማመን ተለውጠው ህዝቡ ራሱ የሠላሙ ጠባቂ እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!