ሠራዊቱ ተልዕኮውን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ መፈጸም ይኖርበታል ተባለ

 

የኢፌዴሪ መከላከያ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ተልዕኮውን መፈጸም እንደሚገባው የኢፌዴሪ  ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን አሳሰቡ።

ጄኔራል መኮንኑ ይህንን ያሳሰቡት የመከላከያ አመራርነት የአቅም ግንባታ ማዕከል ለ3ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን መኮንኖች በአስመረቀበት ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት የሥራ መመሪያ ንግግራቸው ነው።

ጄኔራል ሰዓረ አያይዘውም የኢፌዴሪ መከላከያ ከመላው የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተውጣጣና በህገ-መንግሥቱ የተቋቋመ በመሆኑ፣ ወገንተኝነቱም ለህገ-መንግሥቱ ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል።

በሀገራችን እየታየ ያለው ሠላምና የለውጥ ሂደት የማይዋጥላቸው ኃይሎች የሚፈጥሩትን ሠላም የማደፍረስ ሂደት ሠራዊቱ ህገ-መንግሥታዊ መርሆውን በተከተለ መንገድ ሊከላከል እንደሚገባው እና ሠራዊቱ ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሳይወግን ሀገሩን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን ችግሮች ለመፍታት ከመንግሥት የተሰጠውን ግዳጅ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል።

ተመራቂዎችም በረጅም ጊዜ በሠራዊት ቆይታቸው ያገኙትን ልምድ ከማዕከሉ ሥልጠና ጋር በመደመር ለተሻለ ሥራ መነሳሳት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የመከላከያ አመራር አቅም ግንባታ ማዕከል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ፍስሃ ኪዳነ ማርያም በበኩላቸው፤ የሥልጠናው አካሄድ በተግባር ላይ ትኩረት ያደረገ እንደነበር ገልጸው፤ ከተመደበው የሥልጠና ሰዓት ውስጥ ለዋና አቅራቢዎች አነስተኛ ጊዜ እና ለሠልጣኝ መኮንኖች ከፍተኛ ጊዜ በመመደብ የልምድ ልውውጣቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ዕድል የሰጠ ነበር ብለዋል።

ካነጋገርናቸው ሠልጣኝ መኮንኖች መካከል ሻለቃ ኤርሚያስ ኤቼ በሰጡት አስተያየት፤ “በዚህ የአመራርነት ሥልጠና ላይ ከሥልጠናው ያገኘነው ግንዛቤ እጅግ ከፍተኛ ነው። በተለይም በህገ-መንግሥቱ ዙሪያ ሰፋ ያለ ዕውቀት እግኝተናል። በምንሄድበት አሀድም ያገኘነውን ዕውቀት ለማካፈል ዝግጁ ነን” ብለዋል።

ሌላው ተመራቂ መኮንን ሻለቃ ቴዎድሮስ ግዛው በበኩላቸው፤ የአቅም ግንባታ ትምህርትና ሥልጠና በማግኘታቸው ከፍተኛ የሆነ አቅም መፍጠራቸውን ገልፀዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!