የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የተቋሙን የሰው ኃይል ፍላጎት እያሟላ እንደሚገኝ ተገለጸ

 

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ለህገ- መንግሥቱና ለህገ- መንግሥታዊ ሥርዓቱ ታማኝ የሆኑ መሃንዲሶችንና የጤና ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ የተቋሙን የሰው ኃይል ፍላጎት እያሟላ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ።

ክቡር ፕሬዚዳንቱ ይህን የገለፁት የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢንጂነሪንግና በጤና መስክ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በቢሾፍቱ ባስመረቀበት ወቅት ተገኝተው ብልጫ ላመጡ ተማሪዎች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ከሰጡ በኋላ ባሰሙት የመመሪያ ንግግር ነው። በምረቃ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ክቡር ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ለተመራቂዎች ዲግሪና ዲፕሎማ ሰጥተዋል።

ክቡር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በዚሁ ንግግራቸው፤ የተቋሙ ምሩቃን የመከላከያ ኃይሉን ከማዘመንና የሠራዊቱን ጤንነት ከማረጋገጥ ባለፈ በሀገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ታላቅ ተስፋ በተጣለባቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ያላቸው ወሳኝ ሚና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ተመራቂዎች ወደ ሥራ አለም ሲሰማሩ የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ለወግ ማዕረግ ያበቃቸውን ህዝብ አደራ ጭምር የሚቀበሉበት እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ሜ/ጄኔራል ሀለፎም እጅጉ በበኩላቸው የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የተቋሙን የሰው ኃይል ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር እንደ አንድ ሀገራዊ የአቅም ግንባታ ማዕከል በመሆን በቴክኖሎጂና በጤና የዳበረ ዕውቀት ያለው ልማታዊ ኃይል በመፍጠር ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ጉዞ የበኩሉን ድርሻ በመጫወት አወንታዊ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ሠራዊታችን ህገ- መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ አሻራቸውን ማስቀመጥ የቻሉ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው በርካታ ወታደር መሃንዲሶችን ማፍራት እንደተቻለ ሜ/ጄኔራል ሀለፎም ተናግረዋል።

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ካስመረቃቸው 682 ተመራቂዎች መካከል ከሩዋንዳ 5፣ ከደቡብ ሱዳን 2፣ ከፌዴራል ፖሊስ 7 እና ከሲቪል 13 ተመራቂዎች መሆናቸው ታውቋል።

በዕለቱም ሚኒስትሮች፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ ወታደራዊ አታሼዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦችና የኮሌጁ ማህበረሰብ የተገኙ ሲሆን፤ ተመራቂዎች የሰሯቸው የምርምር ሥራዎች  በክብር እንግዳው ተጎብኝቷል።

በተመሳሳይ ዜና በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ  የጤና ሣይንስ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርምር ሥራዎች አውደ ጥናት አካሄደ።

ለሁለት ቀናት የተካሄደው አውደ ጥናት ሲጠናቀቅ በክብር እንግድነት ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት ሜ/ጄኔራል  ጥጋቡ ይልማ የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኃላፊ ናቸው።

ጄኔራል መኮንኑ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና በቀጣይም የሁሉም አቅም ማረፍ እንዳለበት ገልጸዋል።

“ጥናት አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል” ያሉት ሜ/ጄኔራል ጥጋቡ የጤና ሣይንስ ኮሌጅ የመማር ማስተማሩን ሥራ በምርምር መደገፉና በአውደ ጥናት ደረጃ የተለያዩ ሙያተኞችን በማሳተፍ ግብዓት እንዲገኝ ማድረጉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የጤና ሣይንስ ኮሌጅ ኮማንዳንት ብ/ጄኔራል ዳዊት ወልደሰንበት በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የምርምር ሥራዎች የሠራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ገልጸዋል።

“በጤናው ዘርፍ ሁለንተናዊ ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና የምርምር ሥራዎች መሥራት ተገቢ ነው” ያሉት የኮሌጁ ኮማንዳንት የሚሊኒየሙን የጤና ግብ ማሳካት እንደሚገባም አስረድተዋል።

ኮሌጁ የጤና ሙያተኛና ተመ ራማሪ መምህራንን ለማፍራት ላለፉት ዓመታትተከታታይ  ሥራዎች መሥራታቸውንና በአውደ ጥናቱም ወቅታዊና ሣይንሳዊ ጥናቶች መቅረባቸውንም አስረድተዋል።

በምርምር አውደ ጥናት ጉባኤው ላይ ምሁራን፣ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል። የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎችም የፎቶ ኤግዚቢሽንና በኮሌጁ ቅጥር ግቢ እየተገነባ ያለውን ሪፈራል ሆስፒታልና የመማር ማስተማር ሂደቱን ጎብኝተዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!