በመከላከያ ሚኒስትር የተመራ ቡድን የልማት ሥራዎችን ጎበኘ

 

በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ የተመራ የተቋሙ ከፍተኛ  ኃላፊዎች ቡድን በመከላከያ መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ  በኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የሚገነቡ ታላላቅ ሀገራዊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን  ጎበኘ፡፡

የልዑክ ቡድኑ አዲስና ነባር የመንገድ ግንባታዎችን ፣  የሪፈራል ሆስፒታልና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን  የጎበኘ ሲሆን፣  በስራ ሂደቱ የነበሩ ጥንካሬዎችን ይበልጥ ለማሳደግና እጥረቶችን መቅረፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች  ከባለድርሻ አካላቱ ጋር ተወያይቷል ፡፡

   የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ቡድን ባደረገው ጉብኝት አዲስና ነባር የመንገድ ግንባታዎችን፣ እንዲሁም የሪፈራል ሆስፒታልና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የደረሱበትን ደረጃና የስራ ሂደታቸውን ተመልክቷል፡፡

ከዲቼኤቶ ጋላፊ መገንጠያ ኤሊዳር በልሆ የሚደርሰውና በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ እየተገነባ ያለው 78 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት የመንገድ ስራ ሀገራችን የታጁራ ወደብን በአማራጭነት ለመጠቅም የያዘችውን እቅድ የሚያሳካ  ታላቅ የልማት ውጥን ሲሆን ግንባታው በአሁኑ ጊዜ 44 በመቶ ስራው ተጠናቋል።

የኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዙ እየገነባቸው ካሉ አዳዲስ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች መሃከል 41 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የዳሎል ሙስሊ የመንገድ ስራ ፣ 55 ኪሎሜትር የሚጠጋው የኤርታሌ አህመድ ኢላ የመንገድ ዝርጋታና፣  94 ኪሎሜትር የሚረዝመው የመቀሌ ደንጎላት ሳምረ ፈነርዋ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት በቡድኑ ተጎብኝቷል ፣

92 ኪሎሜትር የሚሸፍነው የአዲጉዶም መቀሌ ውቅሮ 1ኛ ደረጃ የመንገድ ጥገና፣ የመቀሌ ሪፈራል ሆስፒታልና የሠራዊት የጋራ መኖሪያ ግንባታዎች  የደረሱበትን ደረጃ የጎበኘው ቡድኑ  በስራ ሂደቱ ያሉ ጥንካሬዎችንና የተስተዋሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተም ከባለ ድርሻ አካላቱ ጋር ተወያይቷል፡፡

ሁሉም አካላት በችግሮቻቸው ዙርያ በመነጋገርና የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን በወቅቱ በመፍታት ስራዎቻቸውን የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ መትጋትና የተጣለባቸውን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ አሳስበዋል፡፡

ለሀገራዊ ልማታችን መጎልበት ጉልህ ድርሻ ባላቸው በነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረጉ  ተመሳሳይ የመስክ ምልከታዎችና ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ጠቁመዋል፡ 

የሠራዊቱን  የዓላማ ፅናትና  የግዳጅ አፈፃፀም ጥንካሬን በመውረሳችን የግሉ ባለሃብት ብዙም በማይደፍራቸው አካባቢዎች፣ አስቸጋሪ የመሬት ገጽታና የአየር ፀባይን ተቋቁመን እንድንሰራ አስችሎናል በማለት የፕሮጀክቱ ሙያተኞች ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሠላማዊ ሠልፍ  ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ

 

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ህገ- መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን እንደዚሁም በህዝቡ እየተመዘገቡ ያሉትን ድሎች በኃይል ለመቀልበስ የሚሞክሩ ማንኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች የህዝቡን ሠላም ከማደፍረስ እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሳሰበ፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየሰፈነ ያለውን ሠላምና መረጋጋት በህዝቡ ውስጥ እየፈነጠቀ ያለውን ብሩህ ተስፋ ምክንያት በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶ/ር አብይ አህመድ ምስጋናውንና ድጋፉን ለመግለጽ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በተሳተፈበት ሰላማዊ ሰልፍ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት  በጥብቅ አውግዟል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ  ቤቱ በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት የህዝቡንና የሀገሪቱን አንድነትና ሠላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎችን  ከመንግስትና ከህዝብ ጋር በመሆን በጽናት ለመመከት ሁሌ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ኃይል ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም በህዝቡ እየተመዘገቡ ያሉትን ድሎች በኃይል ለመ ቀልበስ የሚሞክሩ ማንኛውንም የውጥስም ሆነ የውጭ ኃይሎች የሕዝቡን ሠላም ከማደፍረስ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ እያሳሰበ በትላትናው ዕለት በተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ጥቃት ጉዳት በደረሰባቸው ሰላማዊ ዜጎች የተሰማውን ጥቅል ሃዘን ይገልጻል፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን ተመኝቷል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!