ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ የቃኚ ሙያተኞች ተመረቁ

 

የባሩድ ማዕከላዊ ዕዝ ፋና ማሠልጠኛ ማዕከል በዕዙ ሥር ከሚገኙ ክፍለ ጦሮች የተውጣጡ የቃኚ ሙያተኞችን አሰልጥኖ አስመረቀ።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ገብረመስቀል ገብረእግዚአብሄር ለተመራቂዎቹ የተዘጋጀላቸውን የምሥክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት የሥራ መመሪያ ንግግር፤ “ጠንካራ የመረጃ ደህንነት ያለው የሠራዊት ክፍል አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው ሠላም መገንባት ያስችላል፤ የዛሬ ተመራቂ ሙያተኞች ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ፈጣን ጉዞ ላይ ሙያዊ አቅማቸውን በመጠቀም መሥራት ይገባቸዋል” ብለዋል።

የማዕከላዊ ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ ባቀረቡት የሥልጠና ሪፖርት ማዕከሉ በዕዙ ስር የሚገኙ የተዋጊ ክፍሎችን እና ልዩ ልዩ ሙያተኞችን በማሠልጠን የዕዙ የማድረግ አቅም ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ተመራቂ  የቃኚ ሙያተኞቹን በክህሎት፣ በዕውቀት፣ በባህሪና በአስተሳሰብ የዘመኑ ሆነው እንዲቀረጹ ሁለገብ ትምህርት መውሰዳቸው አዲስ እና ነባሩን ሙያተኞች ለማዋሃድ  መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው ብለዋል።

ጄኔራል መኮንኑ አያይዘውም በሥልጠና ቆይታም በወታደራዊ አካል ብቃት፣ በሙያዊ ትምህርቶች እና በልዩ ልዩ የአቅም ግንባታ ትምህርቶች ላይ በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የታገዘ የ3 ወር ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ከተመራቂዎች መካከል መ/አለቃ ሀብቶም ካህሳይ እና መ/ወ/ር ያለምወርቅ ስማቸው በሰጡት ተመሳሳይ አስተያየት ሥልጠናው በሠራዊቱ ግዳጅ አፈጻጸም ውስጥ  ሊከተሉት ስለሚገባቸው ሙያዊ ከህሎት ጥሩ ግንዛቤ መጨበጣቸውን በሚሰማሩበት ግዳጅ ላይም ስኬታማ ለመሆን እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!