ተጠንቀቅ ኃይሉ የጥምር ተልዕኮ ድጋፍ አሰጣጥ ስልጠና ሰጠ

 

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ከአባል ሃገሪቱ ለተወጣጡ የመከላከያ፣ ፖሊስና ሲቪሎች በተልዕኮ ወቅት የጥምር የሎጅስቲክ አሰጣጥ ዙሪያ ለሁለት ሳምንት ስልጠና ሰጠ።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የአፍሪካ ህብረትን በመወከል በክብር እንግድነት የተገኙት ሚስተር ሞርሚቦሙ ለሰልጣኞች ሰርተፍኬት በመስጠት ንግግር አድርገዋል።

የክብር እንግዳው አፍሪካ የራሷን ችግር መፍታት ትችል ዘንድ ለቀጣናው ተጠንቀቅ ኃይል ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል አዛዥ ሱዳናዊው ብርጋዲየር ጄኔራል አልመድን ዑስማን በበኩላቸው የተሰጠው ስልጠና ተጠንቀቅ ኃይል ብቃቱን ለማሳደግ ከሚሰራቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው ጥምር ተልዕኮን በጋራ ከመደገፍ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

ለስልጠናው መሳካት አስተዋፅኦ ያበረከትን አባል ሃገራት፣ የስልጠና አስተባባሪዎችና መምህራን በተለይም የኢፌዴሪ  መከላከያን ያመሰገኑት አዛዡ፣ የዕለቱ የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በተልዕኳቸው የየሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በብቃት ተቀናጅተው የሚጠበቅባቸውን ተግባራት ለማከናወን መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የተጠንቀቅ ኃይሉ ሎጀስቲክ ቤዝ ኃላፊ ኮሎኔል ጉዲዊን ካኒጋካ ባቀረቡት የስልጠና ሪፖርት ከአባል ሃገራቱ የተወጣጡ 34 ሲቪሎች፣ የሠራዊትና ፖሊስ አባላት በጥምር የሎጀስቲክ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ ተልዕኮውን የሚያግዝ ስልጠና መውሰዳቸውን አስረድቷል።

የተሰጠው ስልጠና በተከታታይ ተጠንቀቅ ኃይል የሚካሄደው የአቅም ግንባታ ስራ አካል መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በጥምረት ሃገሪቱ ለሚያከናውኑት ተልዕኮ የሎጀስቲክ ስራ ወሳኝ በመሆኑ የጋራ አረዳድና ዕውቀት ይዘው ወደ ስራ ለመሰማራት ስልጠናው መሰጠቱን አውስቷል።

ከአህጉሪቱ አምስት ተጠንቀቅ ኃይሎች አንዱ የሆነው የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል 10 ሃገራትን በአባልነት የያዘ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን አሳድጎ ለስምሪት ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል።

 

ሠራዊቱ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ ተገለፀ

በሱዳን ዳርፉር የተሰማራው የ22ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ ግዳጁን በብቃትና በኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ተገለፀ።

የሻለቃው ዋና አዛዥ ኮሎኔል ናስር አባዲ እንደገለፁት፣ ሃገራችን በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ በመሰማራት ለአለም ሰላም መትጋት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በግዳጅ አፈፃፀም በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝታለች። ሞተራይዝድ ሬጅመንቱ የዚህ አንድ አካል ሆኖ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሃገሩንና የቀድሞ ተቋሙን ወክሎ ወደ ሰሜን ሱዳን በማምራት ግዳጅን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኮሎኔሉ አያይዘው ሠራዊቱ የተሰጠውን ዘመናዊ ስልጠና ስንቅ አድርጎ ወደ ተግባር በመቀየር የሱዳን መሬት ሳይገድበው በርካታ ክሎሜትሮችን በማቋረጥ ረሀብና ጥማቱን ተቋቁሞ ድካምና እንግልቱ ሳይበግረው እርስ በእርስ ግጭት ምክኒያት ከቤት ቀያቸው የተፈናቀሉ ሱዳናዊያን ወገኖች ሰላማቸው ተረጋግጦ በነፃነት እንዲኖሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በሌላ በኩል የሰላም ማስከበር ሻለቃ የመገናኛ ክፍል ሠራዊቱን የመደገፍ የተሟላ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር በማስቻል በኩል ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ።

የመገናኛ ክፍል ኃላፊ ሻለቃ ይገዙ አብሸ፣ መገናኛ ክፍሉ ሠራዊቱ የተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና አለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጅ በስኬት እንዲወጣ በታቀደ እና በተደራጀ መንገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን ያልተቋረጠ የ24 ሰዓት የመረጃ ፍሰት እንዲኖር በማስቻል በኩል ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም በመገናኛ ክፍሉ ስራውን የሚያከናውነው የዕውቀት እና የረጅም ጊዜ ልምድ ባላቸው ሙያተኞች በመሆኑ፣ ወጭ ቆጣቢ አሰራሮችን የበለጠ በማዳበር እና ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ የግንኙነት ስርአትን ወደ ላቀ መረጃ በማሸጋገር ለሻለቃው የግዳጅ አፈፃም ስኬታማነት የሚደረገው ያልተቋረጠ ጥረት በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ሪፖርተራችን መቶ አለቃ አደም አሊ ዘግቧል።

በተመሳሳይ ዜና በዩኒስፍ ጥላ ስር የሚገኙ የ17ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ 3ኛ ሻምበል የሠራዊቱ አባላት ለአሚት የገቢያ ሰላም ማረጋገጥ እያበረከቱት  ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ።

የሻምበሉ ዋና አዛዥ ሻለቃ ወዳጅ ቸኮል እንደገለፁት፣ በአቢዬ ተከስቶ የነበረውን ሰላም እጦት የኢትዮጵያ ሠራዊት በብቸኝነት ተልዕኮውን ከተቀበለ ጊዜ ጀምሮ ቀጣናውን በአስተማማኝ በመጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

የሻምበል ምክትል አዛዥ ሻምበል ሃጎስ አሰፋ በበኩላቸው “ሰላም ምንጊዜም ዋጋ የማይተመንለት የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ ነው” ያሉ ሲሆን በቀጣናው የሚገኙ የሁለቱ ጎሳ ማህበረሰቦች በነፃነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ማስቻላቸውን ገልፀዋል። የዘገበው የሞተራይዝድ ሻለቃ ሪፖርተር መቶ አለቃ ቀለሙወርቅ አዳነ ነው።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!