የሰራዊት ቀንን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ

                            

የሰራዊት ቀንን ለማክበር ዝግጅትመጠናቀቁ ተገለፀ

 

       የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክትሬት ዳይሬክተር ሌተናል ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም ገለፁ።

       ጄኔራል መኮንኑ እንደገለጹት ለስድስተኛ ጊዜ የሚከበረው የሰራዊት ቀንን በተለያዩ ሲምፖዚየሞች፤ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በሚደረግ የፓናል ውይይት፤ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በመረከብና በሌሎችም ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል።

 በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር “የኢፌዴሪ ሰራዊትና ፕሮፌሽናሊዚም ”በሚል ርዕስ ውይይት እንደሚደረግና “ሰራዊቱ በአስተሳሰብ፤ በአሰራርና በትጥቁ ከዘመኑ  ጋር እየዘመነ በመሄድ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ለህዝቡ ያሳያል” ያሉት ጄኔራል መኮንኑ ሲምፖዚየሙ ህዝብ ስለሰራዊቱ ያለውን አስተያየት ለመቀበል እንደሚረዳና የሰራዊቱንም ሞራልና ክብር እንደሚጨምር ”ገልፀዋል።

       ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር “ኪነ-ጥበብና ሰራዊት” በሚል ርዕስ የሀገራችን የተለያዩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከሰራዊቱ አባላት ጋርም የፓናል ውይይትም እንደሚካሄድና የፓናል ውይይቱ ዋና ዓላማም የሰራዊቱን በጎ ገፅታና ሞራል ለመገንባት መሆኑ ተጠቅሷል።

 የሰራዊት ቀንን ለማክበር ከተዘጋጁት ፕሮግራሞች ውስጥ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የፀጥታ አካላት እያደረጉት ላለው እንቅስቃሴ የማነቃቃትና የምስጋና ዝግጅት አንዱ መሆኑን የገለጹት ጄኔራል መኮንኑ የካቲት አራት በሁሉም የሰራዊትና የፖሊስ ክፍሎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የእግር ጉዞ እንደሚካሄድም ገልፀዋል።

      በዕለቱም የመከላከያ ሚኒስቴር የህዳሴ ግድብ ዋንጫን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ፅ/ቤት በአዲስ አበባ የሚረከብ ሲሆን ዋንጫው በተመደበለት ጊዜ ወደ ሁሉም ዕዞችና አየር ሀይል እየተዘዋወረ እስከ ግንቦት 20 እንደሚቆይም ገልፀዋል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!