የመከላከያ ሠራዊቱ ቀን ተሞክሮ መቀመሪያ መሆን ይገባዋል

ርዕሰ አንቀጽ

የመከላከያ ሠራዊቱ ቀን ተሞክሮ መቀመሪያ  መሆን ይገባዋል

 

የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት በአዋጅ መሠረት የራሱን ሀገር አቀፍ ቀን ያከብራል። ይህም ባለፉት ዓመታት ለአምስት ጊዜ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ታሰቦ ውሏል። በያዝነው የ2010 ዓ.ም ደግሞ ህዝባዊ ባህሪያችንን እያጎለበትን ህገ- መንግሥታዊ ሥርዓታችንን በመጠበቅ የሀገራችን ህዳሴ ዋስትና ሆነን እንቀጥላል! በሚል መሪ ቃል ለ6ኛ ጊዜ ሠራዊቱ ከራሱ ተልዕኮ ጋር በተጣጣመ መልኩ ከህዝብ ጋር እያከበረው ነው።

ይህ ልዩ ቀን ሲከበር በዋነኛነት የመከላከያ ሠራዊታችንን ገጽታ የመገንባት ግብ አንግቦ ነው። የገጽታ ግንባታው በአግባቡ ሲፈጸም የሚያረጋግጣቸው ዝርዝር ግቦች አሉት።  የገጽታ ግንባታው በዋነኛነት ህገ-መንግሥታዊ፣ ህዝባዊና ዘመናዊ ሠራዊት መሆኑን በዚህም መሠረት የሀገራችንን ህዝቦች የሠላም ጥማት በአስተማማኝ የማረጋገጥ ተልዕኮ እያሳካ መሆኑን በማመላከት ይጀምራል።

ዕለቱ ሲከበር ህገ-መንግሥታዊ ተልዕኮውን በቁርጠኝነት ለማሳካት የተላበሳቸውን እሴቶች እና ወታደራዊ ዲስፕሊኑን በአግባቡ ለህዝባችንና ለወዳጆቻችን ለማስተዋወቅ መልካም ዕድል ይፈጥራል።

ከዚህ አኳያ የመከላከያ ሠራዊታችን ይህን ዕለት ለ6ኛ ሲያከብረው በገጽታ ግንባታ ሚናው የተገኘውን ግብዓት በተደራጀ ሁኔታ መቀመር ይኖርበታል። የሠራዊቱ ቀን በልዩ ልዩ ግዳጅ ያለውን ሠራዊት ተሞክሮ በመቀባበልና በመወራረስ ሂደት ያስገኘውን ፋይዳ መተንተን ይኖርበታል። በተለይም ሠራዊታችን አኩሪ ተልዕኮዎችን በማሳካት ሂደት የተከተላቸውን አሰራሮች እንዲሁም የገጠሙትን ችግሮች የፈታበትን ሳይንስና የአመራር ጥበብ በተሞክሮነት ተዘጋጅተው ልምድ ልውውጥ ሊደረግባቸው ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪ ሠራዊቱ በተሰማራበት ግዳጅ ህዝብ ዋነኛ አቅሙና ደጀኑ ነው። ስለዚህ ባለፉት የሠራዊቱ ቀን ዝግጅቶች ከህዝባችን ያገኘናቸው አስተያየቶች ተቀምረው አዲሱ የሠራዊት አባል የሚማርበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት። ይህን ህዝባዊነት አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችሉ ገንቢ ሃሳቦችም በአግባቡ ተጠንተው በውይይት መድረኮች መዳበር ይኖርባቸዋል።

እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊታችን ዕለቱን ከወዳጆቻችን እና የሌሎች ሀገሮች ወታደራዊ ኃይሎች ጋር ስለሚያከብረው እነዚህ አካላት የሚሰጡት አስተያየት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ስለሆነም ተመሳሳይ ቀኖችን የሚያከብሩበትን ልምድ፣ ከራሳችን ሁኔታ ጋር በማጣጣምና በመጠቀም ለወደፊት የሚከበሩ ቀኖችን ግብ ስኬታማ ማድረግ እንችላለን። በተለይም የሠራዊቱ ቀን በጋራ ሲታሰብ ድንበር ሳይገድበን ለሠላም በጋራ የምንጠራባቸው ዕድሎች ሰፊ ስለሆኑ የተጠናቀረ ሃሳብ መፍጠር ይችላል። በመሆኑም ባለፉት ዓመታት ከእነዚህ አካላት የተገኙ ልምዶች በአግባቡ የሚጠኑበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል።

በተጨማሪ የሠራዊቱን ቀን በድምቀት ማክበራችን የሠራዊታችንን ወታደራዊ ዲስፕሊን፣ ዝግጁነትና አኩሪ ግዳጅ አፈጻጸም ለማጉላት አግዞናል። ያልተነገሩ የሠራዊቱ ስኬቶችና ህዝባዊነትም በይፋ እንዲታወቁ አድርጓል። ከዚህ አኳያ ቀኑን በጋራ ማክበራችን ለሠላም ያለንን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ያረጋግጣል። በዚህ መሠረት የተገነባው ገጽታችን ጠላትን ዲተር የማድረግ ኃይል አለው።

በመሆኑም የመከላከያ ሠራዊት ቀን ለ6ኛ ጊዜ ሲከበር መልካም ገጽታችንን በማጉላት ዲተረንስ የመፍጠር ኃይሉ በጥናት ተደግፎ መረጋገጥ ይኖርበታል፤ ከዚህ ተሞክሮ በመማርም ሌሎች የጠላትን ፍላጎት የመግታት አቅማችንን የሚገነቡ ግብዓቶችን ማካተት ይቻላል።

በአጠቃላይ የመከላከያ ሠራዊቱ ቀንን ከህዝብና ከወዳጆቻችን ጋር ስናከብር በሚፈጥረው መልካም ገጽታ ምክንያት በየዓመቱ የሚናፈቅ ፕሮግራም እንዲሆን መስራት ይገባል። ወጣቱ ሠራዊት፣ ተማሪዎች፣ ምሁራንና መላው ህዝብ ይህ ዕለት ስሜታቸውን የሚያረካ ተሞክሮ ለማግኘት የሚጓጉለት መድረክ መሆን አለበት። አዳዲስ ሀገር በቀልና ችግር ፈቺ የምርምርና የፈጠራ ውጤቶችም መውጣት አለባቸው። ይህ ሲሆን የሠራዊቱ ቀን በህዝብ ድጋፍ ታጅቦ  ተሞክሮ መቀመሪያና ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ እመርታ ፋይዳ ያለው ይሆናል። ስለሆነም የሠራዊቱ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚከበሩ ቀኖች ውስጥ ጉልህ ቦታ ያለው እንዲሆን በጋራ መስራት ይገባል።

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!