“ለዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ትምህርትና ሥልጠና የማይተካ ሚና አላቸው”

 

ለዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ትምህርትና ሥልጠና የማይተካ ሚና አላቸው

- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

ለህገ- መንግሥቱ ፍፁም ታማኝ የሆነ፣ የጠንካራ ዲሲፕሊን ባለቤት፣ በአሰራርና መመሪያ ብቻ የሚሰራ፣ ቁልፍ እሴቶቹን የተላበሰ ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባት ትምህርትና ሥልጠና ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው የኢፌዴሪ መከላከያ ምክትል ኤታማዦር ሹም ለኦፕሬሽናል ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።

ጄኔራሉ ይህንን የገለፁት ሰሞኑን የሜጀር ጄኔራል ኃየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ 11ኛ ዙር የአብዲሳ አጋ ኮርስ ዕጩ መኮንኖችን የጀግናው ሌተና ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ቤተሰቦች በተገኙበት በዲፕሎማ መርሃ ግብር ባስመረቀበት ወቅት ነው። መከላከያ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን በመክፈት በአመራርነትና በተለያዩ ሙያዎች ሲያስተምርና ሲያሰለጥን መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል ኤታማዦር ሹሙ ከነዚህ ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነው የሜጀር ጄኔራል ኃየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ በተከታታይ በሰጠው የዕጩ መኮንን ኮርስ በርካታ ጀማሪ መኮንኖችን አፍርቷል። መኮንኖቹም መስራት በሚችሉበት የአመራር እርከንና በድጋፍ ሰጪ ክፍሎች ተቋሙን በብቃት በማገልገል ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ተመራቂዎቹ ከአካዳሚው ባገኙት ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም በሠራዊት ክፍሎች በነበሩበት ወቅት በቀሰሙት ልምድ ትልቅ አቅም ስለመፍጠራቸው ያላቸውን ፅኑ እምነት የገለፁት ጄኔራል ብርሃኑ በቀጣይነትም የሚፈለገው የብቃት ደረጃ ላይ ለመድረስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቀባቸው አሳስበዋል።

የሜጀር ጄኔራል ኃየሎም አርአያ ወታደራዊ አካዳሚ ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ክንዱ ገዙ በበኩላቸው፤ ውትድርና የከበረ ሙያ ከመሆኑ ባሻገር በሙያው ውስጥ መኮንን ሆኖ ማገልገል ደግሞ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና ብቃት የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን የተረዱት የአብዲሳ አጋ ዲፕሎማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች አካዳሚው የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልተው፣ ትምህርትና ሥልጠናውን በብቃት ፈጽመው በኮሌጁ ሴኔት በተረጋገጠ ብቃት ለምርቃት መብቃታቸውን አስረድተዋል።

በተፈላጊ እውቀት፣ ክህሎት፣ አስተሳሰብና ባህሪያት የተገነቡ ሙያውን የሚወዱና የሚያከብሩ በደንቦች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች የሚመሩና የሚሰሩ መኮንኖች ከማፍራት አኳያ አካዳሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዋና አዛዡ የዲፕሎማ መርሃ ግብሩን ማጠናቀቁንና ካሁን በኋላ በዲግሪ መርሃ ግብር ብቻ ትምህርትና ሥልጠና እንደሚሰጥ አሳውቀዋል። ይህም የአካዳሚውን ብቃት ማደግ የሚያረጋግጥ ሽግግር መሆኑን በመጠቆም።

በዕለቱ ስለተመራቂዎቹ የሁለት ዓመታት ቆይታ ዝርዝር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በምርቃት ሥነ- ሥርዓቱ ላይ ጄኔራል መኮንኖች፣ የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጀግናው ሌተና ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ቤተሰቦች፣ የግቢው ማህበረሰብና የተመራቂ ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን፤ ተመራቂዎቹ ለጀግናው ሌተና ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ቤተሰቦች የማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል።

ማሠልጠኛ ማዕከሉ ሠልጣኞችን አስመረቀ

በደስታ ተረፈ(ወ/ር

የጋዜጣው ሪፖርተር

 

 

 የብር ሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና እና የበታች ሹም ማሠልጠኛ ማዕከል ትምህርት ቤት የ27ኛ ዙር ሠልጣኞችን አስመረቀ።

በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት በኢፌዴሪ መከላከያ  የአቅም ግንባታ ማዕከል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍሰሃ ኪዳነማርያም እንደተናገሩት፤ ውትድርና በባሀሪው ጽናትን፣ ዲሲፕሊንን፣ ቆራጥነትን፣ ታታሪነትን፣ ታማኝነትንና በራስ መተማመን የሚጠይቅ ሙያ ነው። ተመራቂዎች በማሰልጠኛ ማዕከሉ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በሚሰማሩበትግዳጅ መተግበር እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ሜጀር ጄኔራሉ አያይዘውም ሠልጣኞች የወሰዱት የመሠረታዊ ውትድርና ሥልጠና በሚሰማሩበት ግዳጃቸውን በስኬት ለመወጣት በቂ ቢሆንም ሥልጠናው የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የብር ሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ፍሰሃ በየነ በበኩላቸው ሠልጣኞች በሥልጠና ቆይታቸው በቂ የሆነ ግንዛቤ እና እውቀት እንዲያገኙ የአሰልጣኞች ሚና ከፍተኛ እንደ ነበረ ገልፀው፣ ሠልጣኞቹ ለመሠረታዊ ውትድርና የሚያበቃቸውን ወታደራዊና የግንባታ ትምህርቶች በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ሥልጠና በመውሰድ በቂ የሆነ ዕውቀት እንዲገበዩ ተደርጓል ብለዋል።