የመከላከያ ሚኒስትሯ ትውውቅና ውይይት አደረጉ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፣ ከመከላከያ ልዩ ልዩ ክፍሎችና ከኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክቶሬት አመራሮች ጋር ትውውቅና ውይይት አደረጉ።

ሰሞኑን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የዋና ዳይሬክቶሬቱ አደረጃጀት፣ ተልዕኮና ዕቅድ አፈጻጸም የሚከናወኑ ተግባራት፣ ጠንካራ ጎኖችና የሚታዩ ውስንነቶችን አስመልክቶ ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን፤ ክብርት ሚኒስትርም የተቋሙን ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ አመላክተዋል።

መከላከያ በቀጣይ የሠራዊቱን የመፈጸም አቅም፣ ሞራልና የግዳጅ ተነሳሽነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ያመለከቱት ሚኒስትሯ ለውጡን ለመደገፍና ለማስቀጠል ወቅቱን የሚመጥኑ የግንባታ ሥራዎች እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

ግልጽ ተልዕኮ፣ አመቺ አደረጃጀት፣ የአባላትን አቅም ማሳደግና ህገ-መንግሥቱን ጨምሮ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን የማስረጽ ሥራ ሁሉም የግንባታ አደረጃጀቶች ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ወሳኝ ተቋማዊ ጉዳይ መሆኑንም ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሃመድ አሳስበዋል።

የግንባታ ሠራተኛው ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎችንና በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ በሚገባ በመረዳት ለሌሎች ለማስረጽ መትጋት እንዳለበትም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።

ክብርት ሚኒስትር በዕለቱ በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ፣ ህግ ዋና ዳይሬከቶሬትና በሥነ-ምግበር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ጋር ውይይትና ትውውቅ አድገረዋል።