የሰራዊታችን ጀግንነት ደምቆ የታየበት ገድል

ትውልድ ከትውልድ የሚቀባበለው የጀግንነት ተጋድሎ ታሪካችን የቅኝ ገዥ ተስፋፊዎችን የሃፍረት ካባ በማልበስ ለአህጉራችን የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ በመሆን በምሳሌነቱ የሚጠቀስ የማንነታችን መገለጫ ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በአድዋ፤መተማ፤ወልወል እና በሌሎቹም የተጋድሎ ታሪካችን የሠለጠነ የሰው ኃይልና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቀው የመጡትን ወራሪዎች ያሰቡትን ቀርቶ ያልጠበቁትን የሽንፈት ፅዋን እንዲጎነጩ ያደረገ ነው፡፡ይህን የኢትዮጵያ ህዝቦች ተጋድሎና አይበገሬነት የውጭ ሃገር የታሪክ ፀሓፍት ጭምር ምስክርነት ሰጥተውበታል፡፡ ኢትዮጵያ በኢጣሊያን ጦር ላይ የተጎናፀፈችውን ድል አስመልክቶ በርክሌይ የተባለ ፀሃፊ እንዲህ ሲል ፅፎቷል ‘’ኢትዮጵያዊያን ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው፤ ጠመንጃና ጦር ይዘው ጎራዴ ታጥቀው፤ የነብርና የአንበሳ ቆዳ ለብሰው፤ አዝማሪዎች እየዘፈኑ ቄሶች ህፃናትና ሴቶች ሳይቀሩ ፀሓይ ፍንጥቅ ስትል በተራራው ላይ በታዩ ጊዜ የጣሊያንን  ጦር አሸበሩት’’ በማለት የዓይን ምስክርነቱን ሰጥቷል ፡፡

ኢትዮጵያዊያን የራሳችን የሆነ ማንነትና ታሪክ አለን ሲባል የበርካቶችን ህይወትና ንብረት የጠየቀው የአልደፈርም ባይነት ክብር ፅናትና ጀግንነትን ከማጉላቱም በላይ የሃገርን ክብር አስጠብቆ በማቆየት ረገድም ትርጉሙ ከድል በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሞት በላይ ሌላ ሞት ባይኖርም የጀግኖች ሞት ግን ዘላለማዊ ክብር በመሆኑ ዘመናቶችን እየተሸጋገረ በመጓዝ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያዊነትና ጀግንነት ተነጣጥለው የማይታዩ መለያ ማንነታችንና ኩራታችን ሆነው በአዲሱ ትውልድ ባላደራም ታሪክ እየተደገመና እየታደሰ ቀጥሏል፡፡ ይህ ከቀደምት አያቶቻችን የተወረሰው ጀግንነት የተላበሰው ባለአደራው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ወረራ ያካሄዱትን እና ጅሃድ ያወጁትን ኃይሎች ካሉበት ቦታ ፈጥኖ በመድረስ የግንኙነት ሠንሠለታቸውን በመበጣጠስና በመደምሰስ የሃገሩን ሰላምና ልማት በመስዋዕትነቱ እውን አድርጓል፡፡ 

በሱማሊያ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ከአልቃይዳ እስከ አልሸባብ ያሉ አለም አቀፍ አሸባሪዎች ምሽግ እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡ እነዚህ ፅንፈኞችና አክራሪዎች ለእስልምና እምነት መጠናከር ቁመናል እያሉ ግን ደግሞ እምነቱ ከሚፈቅደው ውጭ ህዝቡ እንዳይማር ለፈጣሪው ፀሎት እንዳያደርግ እና ወጣቶች በስፖርትና በተለያዩ የመዝናኛ መስኮች እንዳይሳተፉ በማፈን ሃገሪቱ ከጎረቤት ሃገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳትፈጥር በማድረግ የህዝቡን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

ይህን የሱማሊያን ውስጣዊ ውጥረት ለማርገብ ህዝባዊ ውክልና የተሰጠው የሃገሪቱ መንግስት እና የአፍርካ ህብረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው እንዲገባ ይጠይቃሉ፡፡ የሃገራችን መንግስትም ጎረቤት ለሆነው የሱማሊያ ወንድም ህዝብ የክፉ ቀን ደራሽ በመሆን ሱማሊያ ከነበረችበት ያልተረጋጋ ህይወት ወደ አንፃራዊ ሰላም እንድትሸጋገር ጥረት አድርጓል፡፡እያደረገም ይገኛል፡፡ በዚህ የሱማሊያ ተልዕኮ በአሚሶም ሰላም ማስከበር አስተባባሪ ከተያዘው ቀጣና ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከ60 በመቶ በላይ የሆነውን የሃገሪቱ ቦታ ሸፍኗል፡፡ ቀጠናውን መሸፈን ብቻ ሳይሆን በስጋት ውስጥ የነበሩትን ሱማሊያዊያን ከሞት አፋፍ ነፃ ከማውጣት በተጓዳኝ ህብረተሰቡን በቀበሌ፤ በወረዳና ዞን በማደራጀት መንግስታዊ መዋቅር ተፈጥሮ የፀጥታና የመስተዳደር አካላትን አቅም የማጠናከር ተግባር እንዲከናወን አድርጓል፡፡ በዚህም የሰራዊታችን የመፈፀም አቅምና ህዝባዊነት በተግባር እንዲታይ ሆኗል፡፡ ይህን ውጤታማ ተግባር ከሚያከናውኑት የጦር ክፍሎች አንዷ ደግሞ የ134ኛ ሬጅመንት ተጠቃሽ ናት፡፡

በደቡብ ምስራቅ ዕዝ ስር የምትገኘው 134ኛ ሬጅመንት ወደ ሱማሊያ ግዳጅ ተሰጥቷት ስትገባ ለሃገራችን ብሄራዊ ጥቅም መረጋገጥ እንቅፋት የሆነውን የአልሸባብ ሃይል ለመደምሰስ ነው፡፡ ስለሆነም የክፍሉ አባሎች ወደ ሱማሊያ ከመግባታቸው በፊት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ቢያከናውኑም የአልሸባብን ተለዋዋጭ ስልትና ባህሪ መሰረት በማድረግ አጫጭር የተኩስ፤የአካል ብቃት፤ የስልትና ሌሎችንም ከአካባቢው መልከዓምድር የአየር ፀባይ ጋር በተያያዘ ስልጠናዎችን በማድረግ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህ በኃላ ነው ሐምሌ 24/2007 ዓ/ም ግልፅ ተልዕኮ የተሰጣቸው፡፡ ቀጥሎም ከሽላቦ ወደ በለደወይኒ እንዲቀሳቀሱ የተደረገው፡፡ ሐምሌ 26/2007 ዓ/ም በለደወይኒ በመግባት በሃልጌን ዙሪያ ያለውን የአልሸባብ ሃይልና የመንገዱን ሁኔታ በተገቢው መንገድ በማጥናት በየደረጃው ያሉ የሬጅመንቷ አመራሮችና አባላት ስለጉዞአቸው እና ምን ሊገጥማቸው እንዲሚችል ከነመፍትሄው ጭምር ተወያይተው የጋራ ግንዛቤ እንዲይዙ የተደረገው፡፡ ሐምሌ 28/2007ዓ/ም ከበለደወይኒ ወደ ሃልጌን የ85 ኪ/ሜ የእግር ጉዞ ጀመሩ፡፡ ከበለደወይኒ 20ኪ/ሜ እንደተጓዙ አልሸባብ ከጉዞአቸው ለመግታት ደፈጣ አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ ነገር ግን የበርሃዎቹ ተወርዋሪ ክዋክብቶች አሰላለፋቸውን ጠብቀው በጥንቃቄ ይጓዙ ስለነበር አልሸባብ ሁኔታውን ተገንዝቦ በርቀት ተኩስ ሸሸ፡፡ የሬጅመንቷ አናብስቶች የሂራን ዞን በርሃማ ቦታዎችን በፈጣን እግራቸው እያቆራረጡት ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ከበለደወይኒ 70ኪ/ሜ እንደተጓዙ የወጣቱ ክንፍ ነኝ የሚለው አሸባሪ ቡድን በአነስተኛ የሰው ኃይል ጥቃት አድርሶ ለማምለጥ አስቦ በተለመደው ተግባሩ በርቀት ተኩስ ሽሽቱን ቀጠለ፡፡

134ኛ ሬጅመንት ወደ ሃልጌን ከተማ እየተጠጉ በሄዱ ቁጥር አልሸባብ የህልውናው መጨረሻ መሆኑን ተገነዘበ፡፡ ምክንያቱም ሃልጌንን እንደ መነሻ ስትራቴጂክ በማድረግ የሰው ኃይልና የኢኮኖሚ ምንጭ ያገኝበት ስለነበር ነው፡፡ ስለሆነም አልሸባብ በሁለተኛው ቀን ጉዞ በርከት ያለ ኃይሉን ከተለያዩ አካባቢዎች በማሰባሰብ 9 የተሸከርካሪ ፈንጂ ቀብሮ ጠበቃቸው፡፡ የሬጅመንቷ አባላት ግን አሰላለፋቸውን አስተካክለው ግራ ቀኙን እያዩ ይጓዙ ስለነበር አልሸባብ ብዙ ርቀት በእግራቸው እየተጓዙ በሄዱ ቁጥር እየተዳከሙ ስለሚሄዱ አዘናግቼ ከፍተኛ ኪሳራ አደርሳለው ብሎ ነበር፡፡ ጀግኖቹ ግን ዳገቱንም ሆነ ቁልቁለቱን እንደ ሻማ በሚያቀልጠው ሞቃታማ በርሃ ወጥተው መውረድ አይሳናቸውምና ጫካውን ማቆራረጥ ያውቁበታልና የአሸባሪው ግምት ከግምት የዘለለ አልሆነም፡፡ እንዳውም ለጥፋት ያዘጋጀው 12 ታጣቂዎቹ ሲገደሉበት 8 የፀረ-ተሸርካሪ ፈንጂዎችም ከተቀበሩበት ቦታ በጥበበኞቹ የሬጅመንቷ መሃንዲስ ተፈልፍለው ወጡ፡፡ በአሸባሪው ቡድን ላይ ከፍተኛ ሰብኣዊና ማቴሪያላዊ ኪሳራ እንዲደርስበት በማድረግ ከ2ቀን ጉዞ በኃላ ሃልጌን ከተማ በጀግኖቹ የ134ኛ ሬጅመንት ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡

የ134ኛ ሬጅመንት ቦታውን ከተረከቡ በኃላ ግን ነዋሪዎቿ “ከፈጣሪ በታች እናንተ ደረሳችሁልን “ እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡

ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ/ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ አልሸባብ የተነጠቀውን የኢኮኖሚ ምንጭ ለማስመለስና ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲል ለድል ያበቃኛል ያለውን ሁሉ በማዘጋጀት ሌሊቱን አጓጉዞ ጨለማን ተገን በማድረግ ወደ ሬጅመንቷ ካምፕ ተጠጋ፡፡ነገር ግን እንኳንስ ካምፑን ለመቆጣጠር ወደ ምሽጉም መጠጋት አልቻለም፡፡

 የጀግኖቹን ምሽግ ለመድፈር አጥፍቶ ጠፊ ፈንጂ የጫነች ኮብራ መኪና ከወገን ካምፕ በስተሰሜን አቅጣጫ በመላክ የሬጅመንቷን አባላት አዛብቶ ለመደምሰስ ተንቀሳቀሰ፡፡ ነገር ግን”አያ በሬ ሆይ ሳሩን አየህ እንጂ ገደሉን አታይ “ሆኖ ነገሩ በካምፕ ወጥተው ደፈጣ ላይ የነበሩትን የሬጅመንቷ ጀግኖች አላያቸውምና አሸባሪዎች ከጫኑት እሳት ጋር በዝቅተኛ ድምፅና ፍጥነት ወደ ካምፑ ተጠጉ፡፡ ሁኔታውን በጥንቃቄ ይከታተሉት የነበሩት የሬጅመንቷ አባላት በዚህ ሰዓት ጤናማ መኪና መምጣት እንደማይችል ተገንዝበዋል፡፡ ደፈጣ የወጣችው ጋንታ ሁሉም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መከታተል ጀመሩ፡፡ የጥፋት መልዕክተኞች ጉዞአቸውን በመቀጠል ደፈጣ ላይ ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ደፈጣ ላይ ፊት ለፊት ከነበሩት የመቶዋ አባላት አንድ ጓድ አቀባብሎ ቁም ሲለው የአልሸባብ አጥፍቶ ጠፊ መኪና ፍጥነቷን ጨምራ ወደ ካምፑ ለመግባት ሞከረች፡፡ አልሸባብ የሬጅመንቷን ክንድ ቢያውቅ ኖሮ አይሞክርም ነበር፡፡ ነገር ግን ለማዛባት የላከው ፈንጂ የጫነ ኮብራ መኪና ቀይ መስመሩን ለማለፍ ሲሞክር ጀግናው የሬጅመንቷ ስናይፐር ተኳሽ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን አልሞ አከታትሎ በተኮሰው ጥይት ሹፌሩ ተገደለ፡፡ ከዚያም የመኪናው መሪ የካምፑን አቅጣጫ ትቶ ወደ ከተማዋ በመሄድ ከወገን ከ250 እስከ 300ሜትር በሚሆን እርቀት ላይ በመፈንዳት መኪናው ከተሸከርካሪነት ወደ ቁርጥራጭ ብረትነትና ላስቲክነት ተቀየረ፡፡ ከዚያም አልሸባብ በታጠቀው መሳሪያ ልክ አዛብቶ ለመደምሰስ ያሰበውን ውጥን ራሱ ተዛብቶ መልዕክተኞቹ በጫኑት እሳት ራሳቸው ነደዱበት፡፡ ወደ ካምፑ የተላኩ ጭፍሮቹም በጀግኖቹ የሬጅመንቷ አባላት ጠንካራ ምት እንደ ቅጠል ረገፉ በሁኔታው የተደናገጠው አልሸባብ በምሽግም ሆነ በሳተላይት በነበሩት የሬጅመንቷ አባሎች ላይ ያለውን አቅም አሟጦ ተጠቀመ፡፡ ጀግኖቹ የ134ኛ ሬጅመንት አባላትም በአልሸባብ ተኩስ ጋጋታ ሳይደናገጡ በፍፁም ጀግንነትና ፅናት ከወታደሩ እስከ መሪው በመናበብ ጠላት ሲጠጋ በቦንብ ሲርቅ በየመሳሪያ እርቀቱ ረፈረፉት፡፡

የሬጅመንቷ አባላት አሁንም በተለመደው ጀግንነታቸው በየመጣበት አቅጣጫ ተገቢውን ቅጣት ለመስጠት ኢትዮጵያዊነት ስሜታቸው ተቆጣ በዚህ ወቅት ነው የሬጅመንቷ አመራሮች ጠላትን በመቁረጥ መደምሰስ እንዳለባቸው ወስነው ከተኩስ ጫና ውጪ የነበረችውን አንድ ሻምበል በስተጀርባ በመላክ በቆረጣ እንድትደመስስ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ሻምበሏ የተሰጣትን ግዳጅ ተቀብላ በመጓዝ የአልሸባብን አመራርና የቡድን መሳሪያ በመደምሰስ እና የሚሸሸውንም እየተከተለች በመደምሰስ የመጨረሻ ቀብሩን አበሰረች፡፡

የአሸባሪዎችን የተኩስ ሁኔታ በመገምገም የሬጅመንቷ አባላት ቀደም ብለው በገነቡት ምሽግ ላይ ሆነው የጠላትን ምርጥ ኢላማ እየለዩ አፀፋዊ ምላሽ መስጠት ጀመሩ፡፡ ወደ ካምፑ ተጠግቶ የነበረው የአልሸባብ ኃይል ሰፊ ቀጣና የሸፈነ ረድፍ በመስራት በከፍተኛ ተኩስ ታጅቦ ለሰበራ ተረባረበ፡፡ የጠላት ሞርተር፤ አርፒጂ፤ ቢቲኤንና ብሬን በጀገኖቹ የወገን ካናል ምሽግ ላይ ዘነበ፡፡ በጨለማ ተውጦ የነበረው አካባቢም በተኩስ ልውውጥ ብልጭታ በብርሃን ተተካ፡፡

የሬጅመንቷን ጠንካራ ምት መቋቋም ያቃተው አልሸባብ ሬሳውንና ቁስለኛውን እንዲሁም ንብረቱን ጭምር እያንጠባጠበ እግሩ እንደመራው ሸሸ፡፡ አልሸባብ በሌሎች ሃገሮች የአሚሶም ወታደሮች ላይ የጊዜያዊ ድል ቢያገኝም በጀግኖቹ ጠንካራ ምት አንገቱን ለመድፋት ተገዷል፡፡ ውጊያውን  ጋዜጠኞችና የአክራሪ ሃገሮች ሚዲያዎችም ሳይወዱ በግድ የአልሸባብን ውርደት ዘገቡ፡፡ በዚህ ውጊያ ከ305 በላይ ታጣቂዎቹ የተገደሉበት ሲሆን በአሸባሪው ቡድን ላይ የደረሰው ማቴሪያላዊ ኪሳራ ደግሞ ሞርተር 4፤ ቪቲዜን፤ አርፒጂ/ላውንቸር/ 13፤ ብሬን/መትረየስ/ 15፤ ክላሽ 128፤ ሽጉጥ 4፤ ቦንብ 23፤የአርፒጂ ቁምቡላ 31፤አይኮም መገናኛ ሬዲዮ 7፤ ቪዲዮ ካሜራ 1፤ ጂፒኤስ 2 እንዲሁም በርከት ያለ የክላሽ የብሬን ጥይቶች በሰዓታት ውስጥ ጀግኖቹ በቁጥጥራቸው ስር አውለውታል፡፡ ጀግኖቹ በአትንኩኝ ባይነታቸውና ባልደፈር ባይነታቸው ኢትዮጵያዊነት የጀግንነት ታሪክ ሰርተዋል፡፡  የ134ኛ ሬጅመንት አለምን ያስደመመ እና የአሸባሪዎችን አንገት ያስደፋ አኩሪ የጀግንነት ገድል በመፈፀም ለሌላው የመከላከያ ሰራዊታችን የሞራል ስንቅ የሚሆን ተግባር ፈፅማለች፡፡ በሬጅመንቷ ውጤታማ ስራም ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ኩራት በዓለምም ህብረተሰብም አድናቆትን አግኝቷል፡፡ በዚህ አኩሪ ተግባሯም እንደ ሻለቃ የሃገሪቱን ሁለተኛ ደረጃ ሜዳይ ተሸላሚ ለመሆን ብቅታለች፡፡ ይህም ለተቋማችን ትልቅ ኩራት ለቀሪው የሰራዊታችን ክፍሎችም ታላቅ ተምሳሌት ለመሆን ችላለች፡፡

በብዛት የተነበቡ በዩኒስፋ የበላይ ጠባቂና የሃይል አዛዠ ሜ/ጄ ከፍያለው አምዴ በሱዳን አብየ ሰሜን ቀጠና የሚገኘውን የ23ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የሃይል አሰፋፈርና የግዳጅ ቀጠና ተዘዋውረው ጎበኙ፡፡
በዩኒስፋ የበላይ ጠባቂና የሃይል አዛዠ ሜ/ጄ ከፍያለው አምዴ በሱዳን አብየ ሰሜን ቀጠና የሚገኘውን የ23ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የሃይል አሰፋፈርና የግዳጅ ቀጠና ተዘዋውረው ጎበኙ፡፡
በዩኒስፋ የበላይ ጠባቂና የሃይል አዛዠ ሜ/ጄ ከፍያለው አምዴ በሱዳን አብየ ሰሜን ቀጠና የሚገኘውን የ23ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የሃይል አሰፋፈርና...
ነሐሴ 26 12 2012 መከላከያ ሬዲዮ ዜና
ነሐሴ 17 12 2012 መከላከያ ቴሌቪዥን ዜና
Video poster
የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለ14ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች በወታደራዊ አመራርነት ዛሬ ረፋድ አስመርቋል
የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለ14ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች በወታደራዊ አመራርነት ዛሬ ረፋድ አስመርቋል
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የአቅም ግንባታ ግብ ፣ በሁሉም አውዶች መፋለም የሚችል...
የመከላከያ ኢንዶክትሬኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ሴቶች ጉዳይ ከመቶ ሀምሳ ሺ ብር በላይ የሚገመቱ የምግብ ፍጆታዎችን ለየካ ክ/ከተማ ወረዳ 3 እና 4 በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎች ማዕድ አጋሩ
የመከላከያ ኢንዶክትሬኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ሴቶች ጉዳይ ከመቶ ሀምሳ ሺ ብር በላይ የሚገመቱ የምግብ ፍጆታዎችን ለየካ ክ/ከተማ ወረዳ 3 እና 4 በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎች ማዕድ አጋሩ
በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ የመከላከያ ሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሪት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ ፤ የመከላከያ ኢንዶክትሬኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር...